በአንድ ወቅት ማህተመ ጋንዲ ‹‹የሐሳብ መለያየት ጠላትነት አይደለም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ዋነኛ ጠላቴ ሚስቴ ትሆን ነበር፡፡›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በሐሳብ መለያየት አለመዋደድ አይደለም፡፡ በአንድ ርእሰ ጉዳይ የተለያየ አቋም መያዝ የጠላትነት ምልክት አይደለም፡፡ አንዱ የስልጣኔ መለኪያ የማይጥምህን ሐሳብ ታግሶ ማድመጥ መቻል ነው፡፡
ያለፉትን
ዓመታት የሐገራችንን ክራሞት ስንታዘብ የሥህተቱ መጀመሪያ ልዩነትን መጥላት ነው፡፡ ተቃውሞን አለመሻት ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ የሥልጣን
መንበሩ ላይ በንግስና ካሉት መኻል መቶ በመቶ ህዝቡን ያስደሰተ መንግስት የለም፡፡ አልነበረም፡፡ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ሥርአቱን
የማይደግፍ ሊኖር ይችላል፡፡ እንኳን መጥፎ የሚባለውን ድርጊት ጥሩ ነገሮችም የማይዋጡለት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን የአጠቃላይ
ስዕሉ አንድ ቀለም ነውና አይጣልም፡፡ የግዙፉ ምስል ትንሽ ክፍል ነውና ከጨዋታ ሜዳው አይባረርም፡፡