Saturday, April 22, 2017

ተናጋሪ ፖስተሮች

ማስታወቂያ ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በርካታ ዘርፎችም አሉት፡፡ የራሱ የክዋኔ ስርዓት እና ብልሃትም እንዲሁ…ከዚህ ሰፊ ባህር አንዲት ቀጭን ሰበዝ መዘን ለዛሬ ጨዋታችን የሃሳብ ምህዋር መሽከርከሪያነት ልንፈቅድ ነው፡፡
 
በአንድ ወገን አድጓል በሌላው አላደገም፤ በአንዱ ጎጥ ኢንዱስትሪ ነው በሌላው አይደለም፤ በአንዱ ጎራ ባህል አጥፍቷል በሌላው ይገነባል . . .  እያስባለ በማከራከር ላይ ስላለው የኢትዮጵያ ፊልም ከፊልምም ስለ ፖስተሮች /የስዕል ማስታወቂያዎች/ እናውጋ
ማሳወቅ፣ ለተጠቃሚነት መገፋፋት (ማጓጓት)፣ ዘላቂ ደንበኛ ማድረግ -ዋና ዋናዎቹ የማስታወቂያ ዓላማዎች ናቸው፡፡ በርግጥ በማስታወቂያ ዙሪያ ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች አሁንም አሉ፡፡ ማስታወቂያ ሳይንስ ነው ወይስ ጥበብ፤ ዓላማው ማታለል፣ ማሳመን፣ ወይስ ማስገደድ . . .ሌሎችም ቁርጥ ያለ ምላሽ ያልተሰጣቸው ሃሳቦችን ከነክርክራቸው አሁንም እንደተሸከመ ነው፡፡
 የተባለው እንዳለ ሆኖ ለፊልሞች ማስታወቂያነት የሚሰራው ፖስተር ከተራ ሸቀጥ የሚለየው እንዴት ነው? ጥበባዊ አሻራውን እንደያዘ፡- ሰዎች እንዲመለከቱት መጋበዝ፣ እነማን እንደተወኑበት ማሳወቅ እና ደጋግመው እንዲመከቱት መገፋፋት የሚችል ማስታወቂያ መሆን የሚችለው እንዴት ነው? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ መመለስ ብቻ አይበቃውም፡፡ የተሰራው የምስል /የፎቶ/ ማስታወቂያ ከፊልሙ ታሪክ ጋር ምን ዓይነት ተዛማዶ አለው? ፖስተሩ የነገረን እና ፊልሙ የሚነግረን ነገሮች አልጣረሱምን? የሚለው ጥያቄም በአግባቡ መመለስ አለበት፡፡
በፊልሙ ውስጥ ምን ያህል ፐርሰንት የሚታዩ ተዋንያን፤ ወይም ስንት ስንተኛው የፊልሙን ታሪክ የሚሸፍኑ ገጸ-ባህሪዎች ናቸው በፖስተር ማስታወቂያ ላይ መካተት ያለባቸው? ማስታወቂያው የሚወሰደው ቀጥታ ከፊልሙ ትዕይንቶች ውስጥ ከሆነ ከላይ የተዘረዘሩትን ሃላፊነቶት የሚሸከመው ትእይንት የቱ ነው? 
የሚሉት ጥያቄዎች የፊልሞችን የምስል ማስታወቂያ ፈታኝ እንዲሆን የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በአንድ ምስል ላይ እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች መመለስ ፖስተሩን ከሚያሰናዳው ባለሙያ ይጠበቃል፡፡
ከተነሳንበት ነጥብ አንፃር ለማሳያነት የሚያግዙንን እያነሳን እንቀጥል
የመጨረሻዋ ቀሚስ፡- በአንድ የህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ እያደጉ ስለሚገኙ እና ከ HIV ጋር ስለሚኖሩ ወጣቶች የሚተርክ አስተማሪ ፊልም ነው፡፡ በፊልም ውስጥ ግዙፍ ቁምነገርን እንዴት ማስተላለፍ እንደሚቻል ያሳየም ነው፡፡ በእይታ ላይ በነበረበት ወቅት ሽልማቶችን ለማግኘትም በቅቷል፡፡ ፖስተሩ ይህንን ይመስላል፡፡
የመጨረሻዋ ቀሚስ
ሦስት አስፋልት የሚሻገሩ ሴቶች፡፡ ከአንድ የመንገድ ምእራፍ ወደ ሌላ ምእራፍ ህጉን ጠብቀው በመሻገር ላይ ያሉ ሴቶች በምስሉ ላይ ይታያሉ፡፡ ዜብራው ከለመድነው የመሻገሪያ ዜብራ ጋር የተዛመደ እይታ ይኑረው እንጂ ልዩነትም አለው፡፡ ቁጥሮች አሉት 16፣ 17፣ 18፣ እያሉ የሚያድጉ ግን 21 ላይ የሚቆሙ፡፡ ሰልፍ በሚመስል ተራ ከቆሙት ሴቶች መሐል አንዷ 21 ላይ ቆማለች፡፡ ከፊትለፊት አንድ መነጋገሪያ አለ፡፡ የዘፋኝ የመሰለ ማይክራፎን፡፡ ድባቡ ጨለም ያለ ነው፡፡ የበራ፣ የፈካ፣ የደመቀ ነገር አይታይበትም፡፡ በምስል ማስታወቂያ /ፖስተሩ/ ላይ ያለው አጠቃላይ ትእይንት ይህ ነው፡፡


ፊልሙን ከማየቱ በፊት ይህንን ፖስተር የተመለከተ ታዳሚ በውስጡ ጥያቄዎችን ይፈጥራል፡፡ ዜብራው ምንድነው? ወዴት እየተሻገሩ ነው? አልፈዋቸው የመጡት ቁጥሮች ለምን 21 ላይ ቆሙ? ማይክራፎኑ ምንድነው? ርዕሱ የመጨረሻዋ ቀሚስ ለምን ሆነ? 

ፊልሙ ካልታየ በስተቀር ምንም መልስ የለም፡፡ ‹‹ይህ የሁሉም ፖስተር ባህሪ አይደል እንዴ ምን አዲስ ታምር ተፈጥሮ ነው ይህን ማለትህ?›› የሚል ሞጋች ካለ ምላሹ እዚህ ጋር ጀምራል፡፡ የዚህ ፊልም ፖስተር ከፖስተርነት አልፎ የሚገዝፍብን  እና ፖስተሩ የታሪኩ ስእላዊ መግለጫ መሆኑን የምንረዳው ከፊልሙ እይታ በኋላ ነው፡፡
ቀደም ብለን እንዳነሳነው ታሪኩ የሚያወሳው ማሳደጊያ ውስጥ ስላሉ ወጣቶች ነው፡፡
ዜብራው፡- ዜብራው እድሜአቸው ነው፡፡ መድሃኒቶች እንደልብ ባልነበሩበት እና ወቅቱ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ምርምር 21ዓመትን በህይወት መሻገር የማይችሉ የነዛ ተስፈኞች እድሜ፣ ያለጥፋታቸው ህይወት ያደረሰችባቸውን ክፉ እጣ የተጋፈጡ ምስኪኖች እድሜ ነው፡፡ 22 ብለው ለመቁጠር ያልታደሉት ለጋ ወጣቶች እድሜ. . .እዛች እድሜ ላይ ሽግግር አለ፡፡ ከአንድ ምእራፍ ወደ ሌላ ምእራፍ፡፡ ከመኖር ወደ አለመኖር፡፡ ህግ ጠብቀው ስርአት አክብረው እየተሻገሩ ነው፡፡ ግን ይሞታሉ፡፡ መሞት ህግ በማፍረሳቸው፣ ስህተት በመፈጸማቸው ምክንያት የመጣባቸው ስላልሆነ በተፈቀደ ክልል ሲሻገሩ እናያለን፡፡ በውልደት አገኙት አንጂ በሌላ አላመጡትምና

ማይክራፎኑ፡- ከዚህ በፊት በእውኑ አለም የምናውቃቸው ድምጻዊያን ዘፈኖች ለፊልሙ በሚሆን መልኩ ተካተዋል፡፡ በአንዲት ዘፋኝ ገጸባህሪ አማካኝነት፤ ማይክራፎኑ ያንን ለማሳየት የገባ ነው፡፡
ርዕሱ፡- ለመጨረሻ ጊዜ የሚከበረው የልደት ቀን ላይ የመጨሻዋ ሟች የምትለበሰውን ቀሚስ ለማመልከት እና በፊልሙ ውስጥ አንድ አንድ እያሉ ከህይወት መዝገብ የሚቀጠፉትን እንስቶች ለማመልከት የተሰየመ ሳቢ እና ተገቢ ርዕስ ነው፡፡
የድባቡ መጨፍገግ፡- አስቂኝ ወይም ሌላ ዘና ያለ ታሪክን የሚያሳይ አለመሆኑን በማሰብ የገባ ነው፡፡ በሌላ አካል ስህተት በመጣባቸው መከራ ተስፋቸውን እንዳነገቡ፣ ለመኖር እንዳነቡ ህይወታቸውን ስለሚያጡ ወጣቶች ይተርካልና ፍዝ ድባብ ኖረው፡፡
የሴቶቹ አመጣጥ ወደፊትለፊት ነው፡፡ ወደተመልካቹ፡፡ ባለሙያው ሁሉንም አቅጣጫዎች መጠቀም ሲችል ማስተኛት፣ በጎን ማሳለፍ፣ ወደታች ማውረድ …ሲችል ፊትለፊትን መረጠ፡፡ ወደታዳሚው፡፡ ወደኛ፡፡ ይህ ታሪክ የሁላችን መሆኑን ላይደርስብን የሚችልበት ምንም አግባብ አለመኖሩን ሊያስረግጥልን ነው፡፡ 
ባጠቃላይ አንዳችም ነጥብ ያለምክንያት ያልገባበት ፖስተር ነው፡፡ ሁሉም ነገሮች ፍቺ፣ ሰበብ እና በፊልሙ ታሪክ ውስጥ ድርሻ አላቸው፡፡ ቀድመን እንድንጠይቅ እንጂ ቀድመን እንድናውቅ የሚፈቅድልን አንዳች ነገር የለበትም፡፡ ከፊልሙ እይታ በኋላ ደግሞ ልብ ካልነው አለማድነቅ አይቻልም፡፡ ፖስተሩ የፊልሙ አጭር መግለጫ ነው፡፡
የባህር በር፡- ‹‹ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል!›› ብሎ የተነሳን ተመራማሪ ታሪክ የሚተርክ ፊልም ነው፡፡ አለቶችን በድማሚት በማፍረስ ሰው ሰራሽ ወደብ መስራት ይቻላል ብሎ የሚተጋን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የስራ እና የምርምር እንዲሁም የቤተሰብ ታሪክ ያስቃኛል፡፡ 
 
የባህር በር

ጥቁር የለበሱ ሁለት ሰዎች በፖስተሩ ላይ ይታያሉ፡፡ ፊት ተነሳስተው፣ ጀርባ ተሰጣጥተው፣ ሳቅ ርቋቸው፣ … የቆሙ ወንድ እና ሴት፡፡ መላቀቅ ቢፈልጉ እንኳን የማይችሉ፡፡ በወርቃማ ገመድ የተሳሰሩ ሰዎች፡፡ የቆሙት ባህር ዳርቻ ላይ ነው፡፡ ከጀርባቸው መርከብ ይታያል፡፡ መርከቡ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ይውለበለባል፡፡
 
እንደቀደመው ሁሉ አመራማሪ ክስተቶችን የያዘ ፖስተር ነው፡፡ ሁለቱም ለምን ጥቁር ለበሱ? በወርቃማ ገመድ መታሰርስ ለምን? ከገመዱ ጋር የተያያዘችው ቁልፍ መሰል ነገር ምንድናት?
ፊልሙን ማየት ስንጀምር በፖስተሩ ላይ የምናያቸው ገጸባህሪዎች ባል እና ሚስት መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ በትዳር የኖሩ፣ ወልደው የሳሙ፣ ባልና ሚስት፡፡ ነገር ግን ሚስጥር የሚደባበቁ . . . ባል አንገቱ ላይ በወርቅ አሰርቶ ስላንጠለጠላት ጌጥ መሰል ነገር ለልጁ እናት እንኳን የማይናገር ድብቅ ነው፡፡ ሀገሩ የባህር በሯን ስለምታገኝበት መንገድ የተመራመረበትን ሰነድ የት እንደሚያስቀምጥ ለማንም ትንፍሽ የማይል ሃይለኛ ሚስጥረኛ፡፡

ፊልሙን ስናጋምስ ሚስትም ከባሏ የሸሸገቻቸው በርካታ የሚስጥር ቋጠሮዎች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ ተራቸውን ጠብቀው ይዘረገፉልናል፡፡ የተመራማሪው ሚስት ባልዋ የሚያጠናውን ጥናት ለመዝረፍ ካሴሩ የውጪ ሃይሎች ጋር ግንኙነት አላት፡፡ ባልዋን እየሰለለች መረጃ ታቀብላለች፡፡ 




እዚህ ጋር የፖስተሩ ምስጢር ይፈታል ለባሏ ጀርባዋን የሰጠች ሚስት፡፡ ለሚስቱ ሚስጥሩን የማያካፍል ባል… በቀለም ሳይንስ ጥቁር ድብቅ ቀለም ነው፡፡ ሁሉም ቀለማት በውስጡ ሸሽጓል፡፡ የብርሃን እርዳታ ካልታከለ በቀር በጨለማ መተያየት አዳጋች ነው፡፡ ለነዚህ ለማይተያዩ ጥንዶች፤ በሚስጥር ትብትብ ለታሰሩ ጥንዶች፤ ከጥቁር ውጪ ገላጭ ቀለም ከየት ይመጣ ይሆን? የወርቃማ ቀለም ትርጓሜ ደግሞ ሚስጥር ነው፡፡ ተፈላጊ ሚስጥር፡፡ 

የአጭር አጭር ተደርጎ ሲገለጽ ኢትዮጵያዊ ርዕሰ ጉዳይ ባለው አንድ ከባድ ሚስጥር የተሳሰሩ ሰዎችን ታሪክ የሚያሳይ ፊልም መሆኑን የሚናገር ፖስተር ነው የባህር በር ፖስተር፡፡

በፖስተሩ ላይ የምናያት ቁልፍ ሚስጥርም በስተመጨረሻ ይፈታል፡፡ ተመራማሪው  የምርምር ውጤቱን እናቴ የሰጠችኝ የአደራ እቃ ነው እያለ ያወራለት በነበረውና ዘወትር ከአንገቱ በማይለየው ጌጥ መሰል የወርቅ ጋን ላይ በሚሞሪ ካርድ እንደሚያስቀምጠው እናውቃለን፡፡ 

ሚስቱም ወዳው ሳትሆን ለዚሁ ጣጠኛ ምስጢር ብላ ያገባቸው የሌላ ሀገር ሰላይ ሆና ታርፈዋለች፡፡ ጀርባ የተሰጣጡበት ምክንያትም ይገለጣል፡፡ አበቃ፡፡ ይሆነኝ ተብሎ ታሪኩን በደንብ በማሰብ የተሰራ እና ስራውም የተዋጣለት ፖስተር አያስብልም ታዲያ? እያንዳንዷን ቅንጣት ልቅም አድርጎ በጥንቃቄ የከተበ ጠሪ፣ አመራማሪ፣ ገላጭ ፖስተር


የወንዶች ጉዳይ፡- እንጨት ሙያ ያላቸው እና አንድ ጎልማሳ ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ ወጣት ጓደኛሞችን የፍቅር ታሪክ የሚያሳይ አስቂኝ ፊልም ነው፡፡
የወንዶች ጉዳይ
እስካሁን ካወራንላቸው በተለየ በፊልሙ ውስጥ ያሉት ሁሉም ተዋንያን ሊባል በሚችል ሁኔታ የሚታዩበት ፖስተር ነው፡፡ ቱታ የለበሱ ሰዎች አንድን ሰው እጃቸው ላይ ተሸክመውታል፡፡ የጀርባ ቀለሙ /Background/ ነጭ ነው፡፡ ነጭ የሳቅ የደስታ የንጽህና መገለጫ በመሆኑ ከኮመዲነቱ ጋር ሰምሯል፡፡ ጫማው አካባቢ ያለው ገጸባህሪም አፍንጫውን በመያዝ የኮመዲነቱን ነገር ያሎላዋል፡፡ ውስጥ ያሉትን ትረባዎች ቀድሞ ያመላክታል፡፡ ቀብረር ያለች የምትመስለው ሴትም በጓደኞቹ ድጋፍ ሊይዛት የሚንጠራራውን ሰው ጀርባዋን ብትሰጠውም ዞራ ታየዋለች፡፡ ፊልሙን ስናይም ይህንኑ እናገኛለን ብትሄድም አትጨክንበትም፡፡ የቱታው፣ የሸክሙ የሌላውም ትርጉም በተገቢው መንገድ የተቀመጠ ጥሩ ፖስተር ነው፡፡




የወንዶች ጉዳይ ቁጥር ሁለትም በዚህኛው ክፍል ዋናው የታሪኩ አጠንጣኝ ማን እንደሆነ እና የተከሰተውን አዲስ ነገር ማለትም እርግዝናን አካቶ ያቀረበ ይበል ከሚያስብሉት መሃል ልንመድበው የምንችል ነው፡፡ 





አንድ ስልክ የሚደውል ወንድ ደወለ አልደወለ እያሉ በሚጠባበቁ ወጣት ሴት ጓደኛሞች ላይ የሚያጠነጥነው የፍቅር ፊልም ‹‹አልደወለም››










አንድ ስልክ የሚደውል ወንድ ደወለ አልደወለ እያሉ በሚጠባበቁ ወጣት ሴት ጓደኛሞች ላይ የሚያጠነጥነው የፍቅር ፊልም ‹‹አልደወለም››







ራሱን ወደሴት ቀይሮ መረጃዎችን ለማግኘት የሚጥርን ጋዜጠኛ ውሎ የሚያስቃኘን ‹‹ዱካ››









በይሉኝታ ምክንያት የራሱን ሃሳብና መሆን የሚገባውን ትቶ ያልሆነ ምስቅልቅል ውስጥ ስለሚገባው ሰው የሚተርከው ‹‹ይሉኝታ››




ከመቀመጫችን ተነስተን የምናጨበጭብላቸው ውብ ፖስተሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ለናሙና ያህል አነሳን እንጂ የፊልሞቹን ብዛት ያህል ባይሆንም ሌሎች ያላነሳናቸው ጥሩ ጥሩ ፖስተሮችም አሉ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የፊልም ፖስተሮችን ዲዛይን ያደረገው ማን እደሆነ የሚገልጽ ፅሁፍ በስራዎቹ ላይ የለም፡፡ ማንም አስተዋጽኦ ያለው ሰው ስሙ አለመካተቱ ተገቢ አሰራር ባይሆንም፤ . . . በዚህች አጭር ዳሰሳ ላይ እንኳን ስም ጠርተን ለማመስገን የነበረን ፍላጎት በማስረጃ እጥረት ምክንያት ከሽፏል፡፡
ፊልሙ አጋማሽ ላይ ከገጠር እንደመጣ የምናውቀውን ከተሜ ቀድመው ደበሎ በማልበስ ፖስተር ላይ የለጠፉትን፤ ለ2 ደቂቃ የሚታየውን ተዋናይ ሳይቀር ፖስተር ላይ ደርድረው የፎቶ ኢንዴክስ ያስመሰሉትን፤ ከሃሳቡ ጋር ምንም የማይገናኝ ፎቶ በመሰለኝ እና በደሳለኝ የደነቀሩትን፤ የ5 ደቂቃውን ትእይንት የሙሉ ፊልሙ ሃሳብ በማስመሰል ያቀረቡትን፣ከፊልሙ ዋና ጭብጥ ጋር የተቃረኑ ቀለማት የተጠቀሙትን፤. . .ቤት ይቁጠራቸው ብለን ብንሰነባበትስ? በርከት ስለሚሉ እንዳይሰለቸው እንጂ ይቁጠር!

© ዘመን እና ጥበብ መፅሔት ሚያዝያ 2009 ዓ.ም ላይ የወጣ

No comments:

Post a Comment