Showing posts with label አጫጭር ጨዋታዎች. Show all posts
Showing posts with label አጫጭር ጨዋታዎች. Show all posts

Monday, December 7, 2015

ያለመግባባታችን ምንጭ በጣም መግባባታችን ነው!

አየሽ እኔ እና አንቺ በጣም ተግባብተናል፡፡ ተገባብተናል፡፡ እኔ አንቺ ውስጥ. . . አንቺም እኔ ውስጥ. . . አሳምረሽ ገብተሸኛል፡፡ በትክክል ገብቼሻለሁ፡፡ ዘላቂ መግባባታችን የወለደው አለመግባባት እዚህ ጋር ይፀነሳል፡፡

ሀሳቤን ብቻ ሳይሆን የሀሳብ መንገዴን አግኝሽዋል፡፡ የውሸቴን መነሾ እስከ መድረሻና ውጤቱ መናገር ሳልጀምር አውቀሽዋል፡፡ ፊቴ ላይ የሚሯሯጠው ደም ካዘለው ስሜት በላቀ በልቦናዬ
ያፈንኩትን ሀቅ መገንዘብ ችለሻል፡፡

Monday, August 4, 2014

አየህ ወዳጄ . . .



እንደ ዕድል ሆኖ ዛሬ ከማይክራፎኑ ጅርባ ነህ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ብዕርህ የብዙዎችን አትኩሮት ስቧል፡፡ወደውም ሳይወዱም ይሰሙሀል፡፡ ምርጫ ያጣም አማራጭ የፈለገም ያነብሀል፡፡

 እዚህ ጋር ቆም ብለህ አስብ . . .

ይህ ውድ መዓድ፣ በርካቶች ፈልገው ያጡት፤ በርካቶች ከኔ የተሻለ ይጠቀምበት ብለውበትህትና ያለፉት መድረክ የተከበረ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ነገር ተበላሽቶ ማንም ፈነጨበት እንጂ . . .

Friday, April 11, 2014

መናጆ


በርካታ በጎች ያሉት ሰው አለ እንበል። ካሉት በጎች መካከል አንዷን ነጥሎ መሸጥ ፈልጓል። ለመሸጥ ያሰባትን በግ ከመንጋዋ ነጥሎ ለመውሰድ ግን አይቻለውም፤የበግ ተፈጥሮ እንዲያ አይደለማ . . .በግ ተከታትሎ ነው መንገድ የሚወጣው - በግ በደቦ ነው የሚጓዘው። በግን በአዲስ ጎዳና ለማራመድ የከጀለ ማንም ሰው የሚጠበቅበት ከመካከላቸው አንዷን ጎተት አድርጎ በታቀደው ቦታ እንድታልፍ ማድረግ በቂ ነው። ከዚያ የተቀሩት ተግተልትለው ያልፋሉ። ተከታትለው ያዘግማሉ። 

ስለዚህ ያ ሰው  - ያ በግ ነጋዴው ግለሰብ - የሚሸጠው አንዷን በግ ብቻ እንደሆነ እያወቀ . . .  ቀሪዎቹን ይዞ እንደሚመለስ እያወቀ . . . ሌሎች ሶስት አራት አጃቢዎችን (መናጆ) ይዞ ገበያ ይወጣል።  የምትሸጠው በግ የታለመላትን ተግባር እስክታከናውን የተቀረው ጀሌ የገባችበት ሲገባ የወረደች የወጣችውን ሲመላለስ ይውላል። ተሻጯ ፈላጊ እስክታገኝ ይከተላል። ይህ ተግባር የሚያቆመው መናጆ አስከታይዋ አላማዋን ከግብ እስክታደርስ ነው። ሌላ ተሻጭ - ሌላ መናጆ አስከታይ እስኪፈጠር የተቀረው በግ ወደ በረቱ ይመለሳል።

Wednesday, April 9, 2014

ለሚመለከተው ሁሉ

አዎ አንተ የተማርክ ነህ!  ከአንድም ሁለት ሶስት ተቋማት ውስጥ ገብተህ አንደኛ ፣ ሁለተኛ ፣ እያልክ ዲግሪዎችን ደርድረሀል። ‘አንቱ’’ ተብለሀል። ሀገርህ ካሏት ’ ምሁራን’ መካከል ቀዳሚዎቹ ረድፍ ላይ አለህበት።

አዎ አንተ አንባቢ ነህ! ከትምህርት ቤት ከወጣህ ማግስት ጀምሮ በአዲስ ሀሳብ ውስጥህን ለመሙላት፤ የያዝከውን ጅምር እውቀት ለማስፋት፤ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦችን ለመገንዘብ ቀን ከሌት ትታትራለህ።

Tuesday, December 3, 2013

ሰው ዋጋው ስንት ነው?



አንድ ወዳጅ ነበረኝእግዚአብሄር የሚወድህ ከሆነ ገንዘብ አይሰጥህም !” የሚለኝ። ዝና አይሰጥህም፤ ስልጣን አይሰጥህም፤ ይላል። እነዚህ ሁሉ ሲመነዘሩ ሰውን አይተኩማ፣ ሰውን ከማግኘት ጋር አይተካከሉማ፣ እግዚአብሄር የሚወድህ ከሆነ ሰው ይሰጥሀል። በጎደለ የምትሞላው፣ ክፍተትህን የምትዘጋበት፣ ዕውቀትም ገንዘብም የሆነ . . . ስልጣንም ዝናም የሚሰጥህ ሰው።

ዲዮጋንን በጠራራ ፀሀይ ፋኖስ አስይዞ ያስፈለገው ሰው። ባለቅኔውየሰው ያለህ የሰውብሎ እንዲቀኝ ያስገደደው ሰው። ለዘመናት ድሮ ቀረ . . .ድሮ አልቀረ እያስባለ እልባት አልባ ክርክር ያከራከረው ሰው። ኢየሱስ፣ ቡድሀ፣ መሀመድ ያላቸውን ነገር ሁሉ የከፈሉለት ሰው።

እኔም እናንተ አላችሁኝ እላለሁ። የድክመቴ አበርቺ፣ የጥንካሬዬ ጠቋሚ፣ የሽንፈቴ አፅናኝ፣ የሀሴቴ አድማቂ፣ የጉዳቴ ተሟጋች . . . የሁለ ነገሬ ሁሉም ነገሮች አላችሁኝ እላለሁ። ኑሩልኝ። እደግመዋለሁ ኑሩልኝ።

Thursday, July 18, 2013

ክር ባጭር

በድሮ ጊዜ ነው። በሀገር ወግ በህግና በስርዓትያሳደጓትን ልጃቸውን ላግባ ባይ ጠያቂ የበዛባቸው አባወራ ማንን ከማን ለይተው ለማን እነደሚድሯት ግራ ቢገባቸው ፈተና አዘጋጁ

ፈተናው ጋቢ መስፋት ነው። አስፈላጊው መሳሪያ ሁሉ ተሟልቷል። ጋቢ፣ ክር. መርፌ ሁሉም ቀርቧል።

ያፈቀራትን ሴት በእጁ ለማስገባት የጓጓው የአዳም ዘር ውድድሩን ጀመረ። ሁሉም ጥድፊያ ላይ ነው። ማንም ማንንም አያይም። አባት እና ልጅ ብቻ ሁኔታውን ያታዘባሉ።

Monday, April 29, 2013

ሰስፔንድድ ኮፊ



"ሰስፔንድድ ኮፊ" ስለሚባል ነገር ሰምቼ እንዴት ደስ አለኝ መሰላችሁ። ነገርየው የአውሮፓውያን ባህል ነው፡፡ ወደአንድ ካፌ ቡና ለመጠጣት የገባ ገንዘብ ያለው ዓንድ ሰው ቡናውን አጣጥሞ የተጠቀመበትን ሂሳብ ሲከፍል ትርፍ ክፍያ ይፈፅማል። ማለትም አንድ ቡና ይጠጣና የሁለት ቡና የከፍላል የህንን የሚያደርገው ማንም ገንዘብ የሌለው ነገር ግን ቡና መጠጣት የፈለገ ሰው እንዲጠጣበት ነው። ሲከፍል የሚሰጠው ማረጋገጫ የለም። እርሱም አይጠይቅም። ሁሉም ነገር በእምነት ይከናወናል። ይህንን ሰስፔንድድ ኮፊ የተባለ አገልግሎት ለመጠቀም የፈለገ ሰውም "ዛሬ ሰስፔንድድ ኮፊየከፈለ አለ?" ብሎ በመጠየቅ መኖሩ ከተነገረው ከማያውቀው ሰው የተጋበዘውን ቡና ጠጥቆ አመስግኖ ይወጣል። አሪፍ አይደለች እነ ክሬዚዴይን እና አፕሪል ዘፉልን ከመኮረጅ እንደዚህ አይነቱን መኮረጅ በምድርም በሰማይም አይበጀንም ትላላችሁ? እስኪ እንወያይበት