ሙዚቃ የዘመን ሥራ ነው፡፡ ዘመኑን ይመስላል፡፡ በድምፆቹ ዘመን
ን ያሳያል፡፡ በግጥም ሐሳቦቹ ጊዜ የወለደውን እሳቦት ይናገራል፡፡ የ1960ዎቹን የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች የምንለየው በቅንብር መንገዳቸው (Orchestration) ነው፡፡ የ1970ዎቹንም እንዲሁ ከ60ዎቹ ከወሰዷቸው በጎ እሴቶች ጋር የራሳቸውን ደምረው (የተዉአቸው/ያልወሰዷቸው ታሳቢ ተደርገው) የበርካታ መሳሪያዎችን ድምፅ ማስደመጥ የሚያስችል የሙሉ ባንድ(Natural) የቅንብር ዘዬን በመከተላቸው ነው፡፡ እነ ሮሐ እነ ዋልያስ ባንዶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ን ያሳያል፡፡ በግጥም ሐሳቦቹ ጊዜ የወለደውን እሳቦት ይናገራል፡፡ የ1960ዎቹን የኢትዮጵያን ሙዚቃዎች የምንለየው በቅንብር መንገዳቸው (Orchestration) ነው፡፡ የ1970ዎቹንም እንዲሁ ከ60ዎቹ ከወሰዷቸው በጎ እሴቶች ጋር የራሳቸውን ደምረው (የተዉአቸው/ያልወሰዷቸው ታሳቢ ተደርገው) የበርካታ መሳሪያዎችን ድምፅ ማስደመጥ የሚያስችል የሙሉ ባንድ(Natural) የቅንብር ዘዬን በመከተላቸው ነው፡፡ እነ ሮሐ እነ ዋልያስ ባንዶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የ1990ዎቹ ደግሞ ዘመን የወለደውን የራሱን አስተሳሰብ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በ’ሚዲ ቴክኖሎጂ’ በመታገዝ በአንድ ሰው
በጠባብ ስቱዲዮ ውስጥ የሚሰሩ የቅንብር መንገዶችን ይከተላል፡፡ እነ ሙሉኔታ አባተ እነ ኤልያስ መልካ የመጡበት ዘመን
አሁን አሁን ደግሞ የኤሌክትሮኒክስ ሙዚቃ ዘመን ይመስላል፡፡ ሔለን በርሔ በቅርብ ባወጣችው አልበም ላይ ተሞክሮ እንዳደመጥነው
ቀጣይ ባለተራ የመሆን እድል አለው፡፡
እያንዳንዱ ዘመን የየራሱን በጎም አፍራሽም ተፅእኖዎችን ኖሮ ያልፋል፡፡ ከ1990ዎቹ በኋላ የመጣው የ/Individual
seek/ በኮንፒውተር ፕሮግራሞች አጋዥነት የሚሰራው ሙዚቃ የድምጻዊያንን ችሎታ ስለመግደሉ አብዝቶ ይነገርለታል፡፡ በጥቂቱ የሚሞክሩ
ድምፃዊያንን ብርቱ ችሎታ ከታደሉት እኩል አሰልፏል ተብሎ ይታማል፡፡ ጃዝ፡- የማይችል ሙዚቀኛ፣ አብስትራክት፡- የደካማ ሰዓሊ መሸሸጊያዎች
ናቸው ብለው እስከማመን እና በአደባባይ እስከመናገር የደረሱ ነበሩ፡፡
እጅጋየሁ ሽባባው በሙዚቃ ሥራዋ የተከሰተችው በ1980ዎቹ መጨረሻ እና በ1990 ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው፡፡ ጊዜው
የሽግግር ነበር፡፡ የሙሉ ባንድ ቅንብሮች ወደ ሚዲ ቴክኖሎጂ በመቀየር ላይ ባሉበት ጊዜ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ‹‹ፀሐይ›› የተሰኘው
እና አዲስ አበባ ላይ ያስቀረፀችው የመጀመሪያ አልበሟ ብዙም ተደማጭነት ያላገኘው፡፡
‹‹ፀሐይ ውጪ ውጪ
ፀሐይ ውጪ ውጪ
ደማቅ ብርሐንሽን ለምድሪቷ
ስጪ››
’’ፀሐይ’’ የተሰኘውን አልበሟን
ባስቀረጸችበት ወቅት
‹‹ሕዝቡ የስክስታ ዘፈን እንጂ
አንቺ እንደምትዘፍኚው ያለ ዘፈን አይፈልግም፡፡ አይቀበልሽም፡፡ ብለውኝ ብዙ ተከራክረናል፡፡››
ትላለች፡፡ የውስጧ ግፊት፣ የህሊናዋ
እንጉርጉሮ፣ የልብ ፍላጎቷ . . . ከነጋዴዎቹ ሐሳብ ጋር ቢጣረስባት፤ ንግግራቸው አቋሟን ለመሸርሸር ሲዳዳው መላ ዘየደች፡፡ በአዲስ
አበባ የሚገኙ ግዙፍ የጥበብ ሰዎችን ጠርታ ጠባቧ ስቱዲዮ እየወሰደች ሥራዋን አስደመጠች፡፡ አስገመገመች፡፡
እዚህ ላይ ልጅቷ ምን ያህል ተራማጅ እንደነበረች ልብ ይሏል፡፡ እጅጋየሁ
ከ20 ዓመታት በፊት የከወነችው ተግባር ዛሬም ድረስ የሚዘወተር አይደለም፡፡ ሙከራዋን ካስደመጠቻቸው ልዩ ልዩ ባለሙያዎች - ሐሳብ
ወስዳ፣ አስተያየት ተቀብላ፣ ተግሳፅ ሰምታ፣ በይበልጥ ከራሷ ተማክራ የሠራችውን ሙዚቃ በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት በኩል አደረሰችን፡፡
አልበሙ ታትሞ ከመውጣቱ በፊት ጂጂ ከሐገር ወጣች፡፡
ሰማዩ ጠቆረ በዳመና
ውረጅ የኔ ፀሐይ እንደ መና
ዓለምን በብርሐንሽ ሙላት ጋርጃት
ውጪና ታይባት
ደማቅ ሆነሽ ትወጫለሽ የኔፀሐይ
እናፍቃለሁ እኔ አንቺን ላይ
የኑሮ ውጣውረዷን፤
የአጭር እድሜዋን ረጅም ታሪክ በአንክሮ ከተመለከትን ይህ ዘፈን የሚያወሳው ሁላችንም ስለምናውቃት ፀሐይ አይደለም፡፡ የማንም ይሁንታ
ሳያስፈልጋት በራሷ የተፈጥሮ ኡደት ገብታ ስለምትወጣው ፀሐይ አይደለም፡፡ ነይልኝ ብትባልም ሒጂ ቢሏትም በዑደቷ ላይ ለውጥ ስለማታሳየው
ፀሐይ ዓይደለም፡፡
ለኪነ-ጥበብ ፍቅር ከትውልድ ስፍራዋ ቻግኒ እስከ አዲስ አበባ የተጓዘችባት፤
የወላጅ አባቷን ፍቅር ሳይቀር የለወጠችባት፤ በስደት እንግልት ያየችባት፤ ብዙ ብዙ የሆነችላት፤ ጥበብ ተገቢ ስፍራዋን ስላልሰጠቻት
የተዘረፈ ቅኔ ነው፡፡
በፍቅሯ ጠፍራ፤ አለኝ የምትለውን ጊዜ ሁሉ በልታ፤ ከሴንትሜሪ ትምህርትቤት
በቀሪ ብዛት ያስባረረቻትን፤ በማታው የትምህርት ክፍለጊዜ የጀመረችውንም ትምህርት አስጥላ ከቤተሰቦቿ ጠፍታ ኬንያ የከተመችላት ጥበብ
ብርሃኗን ስለሸሸገችባት የተሰነዘረ ጥሪ ነው፡፡
በሸገር FM 102.1 ለመአዛ ብሩ
‹‹ኬንያ የሔድኩት ከቤተሰቦቼ ጠፍቼ ነው፡፡ በጣም አስቸጋሪ ልጅ ነበርኩ፡፡››
ስትል አጫውታታለች፡፡ ለሙዚቃ የነበራትን ፍቅር በተመለከተ ስታስረዳ
‹‹ማንም ሐይል ሊገዳደረው የማይችል ፍቅር ነበረኝ፡፡ ምንም ነገር
ሊያስቆመኝ አይችልም ነበር፡፡›› በማለት ነው፡፡
‘ስንት ያየሁብሽ ሙዚቃ ሕይወቴ’ እንዲል ቴዎድሮስ - ስንት ያየችባት
ጥበብ ያቆናጠጠቻት እርካብ ከላቧና ከከፈለቻቸው ነገሮች ጋር ሲናጸር ያልተመጣጠነ ሲሆን
ደማቅ ሆነሽ ትወጫለሽ የኔ ፀሐይ
እናፍቃለሁ እኔ አንቺን ላይ . . .
ስትል አዜመች፡፡ ፀሐይ የኔ በማለት የምትገለጽ የግል ንብረት አለመሆኗ፤ የሁሉም መሆኗ ጂጂን አልጠፋትም፡፡ ለሁሉም
ስትል የምትወጣ መሆኑ ከገጣሚዋ የተሰወረ እውነት አይደለም፡፡ ይልቁንም ‹የኔ› የምትለው ቃል የገጣሚዋን ውስጣዊ ሐሳብ ቁልጭ አድርጋ
ታሳያለች፡፡ ለእንስሳቱም፣ ለአራዊቱም፣ ለዕፅዋቱም በእኩል ጊዜ ስለማትወጣ ፀሐይ እየተሞዘቀ እንዳለ ታሳብቃለች፡፡
በጥረት፣ በእድል፣ በሁኔታዎች ምክንያት ልክ እንደ ተፈጥሮዋ ፀሐይ በተመሳሳይ ፈረቃ ስለማትወጣው የስኬት ፀሐይ እንደሚወራ
ታረጋግጣለች፡፡ ‹ፀሐይ› የተሰኘው ዘፈን የህይቀቷ ግልባጭ ነው፡፡ የምኞቷ ትንፋሽ ነው፡፡ በሙዚቃዋ ብርሐን የዓለምን ጨለማ የመግለጥ፤
በዘፈኗ ሙቀት የዓለምን ቆፈን የማሳደድ፤ . . . ሐያል የወጣትነት እምቅ ፍላጎት የወለደው እንጉርጉሮ ነው፡፡ ፀሐይ . . .
ለአጠቃላይ የአልበሙ ርዕስ (ራስ) እንዲሆን የመረጠችውም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ደመናው ይገለጥ ድመቂ
ብሪ ተንቦግቦጊ አንጸባርቂ
የሐገሬ ፀሐይ አይኖቼን በተስፋሽ አንቂ
‹የሐገሬ ፀሐይ› ስትል፤ ስለምታውቀው ዓለም እያወራች እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ዋርካ አቅሟ በወገኖቿ ሚዛን የሰንበሌጥ
ደረጃን መያዙ አስቆጭቷታል፡፡ ተስፋዋን አደብዝዞታል፡፡ ‹የሐገሬ ፀሐይ አነቃቂ ተስፋሽ ከወዴት አለ?› አለች በዜማዋ
ያልተረዳናት አርቲስት የናፈቀቻትን ፀሐይ ፍለጋ፤ የሚረዷትን ሙዚቀኞች
ለማሰስ ሩቅ ተጓዘች፡፡ ፀሐይዋን ወደሷ መሳብ ስላልቻለች አድማሱን አቋርጣ ወደ ፀሐይዋ ጋለበች፡፡
የራሷን ዘፈን መጻፍ ስለጀመረችበት ሁኔታ ተጠይቃ፡-
‹‹እስከመቼ ነው የአስቴርን ዘፈን እምዘፍነው የራሴን ዘፈን መጻፍ
አለብኝ ብዬ መጻፍ ጀመርኩ፡፡ ሁሉም ነገር እንደቀልድ ነው የሆነው›› ትላለች፡፡
አሜሪካ እንደገባች - የስካሁኑ እንግልቷ የተቆጠረላት ይመስል ተከታታይ
የስኬት ዜናዎቿ በዓለም ዜና ማሰራጫዎች ናኙ፡፡
ልጅነቷን በተመለከተ ‹‹ተወልጄ ያደኩት ቻግኒ ነው፡፡›› ትላለች፡፡
‹‹በቦታው ምንም መዝናኛ የለም፡፡ እናቴ የኳስ ቡድን መስርታልን ከመንደሩ
ልጆች ጋር እንጫወት ነበር፡፡ ‹ኦቴሎ› የተሰኘውን ቲያትር ብቻዬን አጥንቼ፤ የሁሉንም ተዋንያን ባህሪ እያስመሰልኩ ለቤተሰቡ አቀርብ
ነበር፡፡ እናቴም የበርካታ ገጣሚያንን ሥራ ታነብልን ነበር፡፡ እኛ ቤት ሰበብ እየተፈለገ ነው የሚዘፈነው›› በማለት ታስረዳለች፡፡
የኪነጥበብ ፍቅር የአጠቃላይ ቤተሰቡ ነው ማለት ያስደፍራል፡፡ ከ10
ወንድምና እህቶቿ መሐከል - ራሔል እና ሶፊያ የተባሉት እህቶቿ ዘማሪያን ናቸው፡፡ ትግስት (ነፍስ ይማር) Bole to
Harlem የተባለ አልበም ላይ በድምጻዊነት ተሳትፋለች፡፡ ወላጅ እናቷ ወ/ሮ ተናኜ ስዩም ‹የፍቅር ድንግልና› የሚል የረጅም ልቦለድ
መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ እጅጋየሁም ከድምፃዊነቷ፣ ዜማና ግጥም ደራሲነቷ ውጪ ተዋናይት እና ሰዓሊ ናት፡፡
በ2003ዓ.ም ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጠችው ቃለመጠይቅ
‹‹ስእሉ እንኳን በቅርብ ጊዜ የተጀመረ ነው፡፡ ፊልሙን ግን ትምህርትቤት ገብቼ የመማር ፍላጎት ነበረኝ፤ ጊዜ አጥቼ
ተውኩት እንጂ›› ብላለች፡፡
ከኬንያ ወደ ሐገሯ ተመልሳ የኑሮ መልሕቋን አሜሪካ ላይ ከመጣሏ በፊት አዲስ አበባ ነበረች፡፡ በነዚህ ጥቂት ዓመታት
‹ፀሐይ› ከተሰኘ ሥራዋ በተጨማሪ ከአርቲስት ፋንታሁን ሸዋንቆጨው ጋር በመሆን በክራር እና በማሲንቆ ብቻ የታጀበ አልበም በጋራ
አስቀርፃለች፡፡ በሙዚቃ ቤት ደረጃ ለህዝብ ስለመውጣቱ ግን እጠራጠራለሁ፡፡ ‹‹የጊዜያችን ሰዎች›› (1987ዓ.ም) ከ 70 በላይ
ተዋንያን የተሳተፉበት እና ‹‹የሞት ፍቅር›› የተሰኙ ፊልሞች ላይ ተውናለች፡፡ ‹ዮኒ ብሬ ፊልም ማምረቻ ማዕከል› በተባለ እና
በዮናስ ብርሐነ መዋ እና በብርሐኑ ሽብሩ በሚመራ ድርጅት ከተሰሩት ፊልሞች ውስጥ ‹የጊዜያችን ሰዎች› ለህዝብ እይታ አልበቃም፡፡
‹‹ፊልሞቹ ከቀደምት የኢትዮጵያዊያን የቪድዮ ፊልሞች መሐከል የሚመደቡ ናቸው›› የሚለው የፊልሙ ዳይሬክተር ብርሐኑ
ሽብሩ
‹‹ጊዜው እንዲህ እንደ አሁኑ ፊልሞች በብዛት መመረት ያልጀመሩበት ነው፡፡ በተለይ ሴቶች ፊልም እንዲሰሩ ቤተሰቦቻቸው
አይፈቅዱላቸውም፡፡›› በማለት ወቅቱን ይተርካል፡፡
‹የሞት ፍቅር› በHIV ስርጭት ላይ ለወጣቶች ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንዲቻል ታስቦ የተሰራ ሲሆን፤ የፊልሙን ወጪ በበጎ
አድራጎት ድርጅቶች እንዲሸፈን በማድረግ በነፃ ለህዝብ እይታ እንዲበቃ ማስቻል የአዘጋጆቹ ሐሳብ ነበር፡፡ ፊልሙ አስቴር በዳኔ፣
የወይንሸት አስፋው፣ እጅጋየሁ ሽባባውን ጨምሮ በርካታ ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡ ‹የሞት ፍቅር› በ1988ዓ.ም በሒልተን
ሆቴል አዲስ አበባ ሲመረቅ ጂጂ ምርጥ ተዋናይት የሚለውን ዘርፍ አሸነፈች፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡- ፊልሙን እንዲመርቁ ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች የተበተነው መጥሪያ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ለተመልካችነት
የሚጋብዝ እና የፊልሙን አጠቃላይ ሁኔታ አንዲገመግሙ የሚጠይቅ፤ በሁለተኛው ዝርዝር ውስጥ ፀጋዬ ገ/መድሕን፣ ሐይማኖት ዓለሙ፣ ደበበ
እሸቱ ከተገኙት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ኤንባሲ አታሼ የክብር እንግዳ የነበሩበት ይህ ታላቅ ዝግጅት ታሪኩ የህክምና ጉዳዮችን
ስለሚያነሳ ታዋቂ ዶክተሮችንም ጋብዟል፡፡
ለሁሉም ተመልካች የታደለ አንድ ወረቀት አለ፡፡ ያወረቀት ሲተጣጠፍ ፖስታ ይሆናል፡፡ ከጀርባው ቴምብር ተለጥፎበታል፡፡
ያቺን ወረቀት የያዘው ታዳሚ ተጋብዞ የተመለከተውን ፊልም አንዴት እንዳገኘው እና የሚሰማውን አስተያየት ጽፎ፤ ጥሩም መጥፎም የሚለውን
የፊልሙን ጎኖች አስፍሮ፤ ምርጥ የትወና ብቃት አሳይተዋል የሚላቸውን ሰዎች መርጦ፤ ወረቀቱን በፖስታቤት ይልከዋል፡፡ /ይህንን በጎ
ተሞኩሮ የአሁኖቹ ፊልመኞች ቢኮርጁት ጠቃሚ ነው/
የዳኞቹ እና የክብር እንግዶቹ ምርጫ ከፊልሙ እይታ በኋላ ጥቂት የፊልሙ ቤተሰቦች በተገኙበት ይፋ ይደረጋል፡፡ ለማን
እንደሚሰጥ ሳይታወቅ የተዘጋጀው ሽልማት በዳኞች ምርጫ መሠረት ለአሸናፊው ይበረከታል፡፡ በዚህ ፕሮግራም መሰረት መጓዝ እንዲቻል
ታቅዶ ፊልሙ መታየት ጀመረ፡፡ እይታው ሲጠናቀቅ ዳኛው አርቲስት ሐይማኖት ዓለሙ(ነፍስ ይማር) ፕሮግራም አፋለሰ፡፡
በአዘጋጆቹ ዕቅድ መሠረት ከህዝብ እይታ ውጪ እንዲደረግ ታስቦ የነበረውን የዕውቅና እና የሽልማት ስነ-ስርዓት አደባባይ
አወጣው፡፡ አድናቆቱን እና ክብሩን መላው ታዳሚ ባለበት በጭብጨባ ታጅቦ ገለጸ፡፡ በህዝብ ፊት መሪ ተዋናይዋ እጅጋየሁ ሽባባው ሽልማቷን
ተቀበለች፡፡ የሁሉንም ትኩረት እና አድናቆት ማግኘት ቻለች፡፡ ክስተቱን ‘The Ethiopian Herald’ ጋዜጣ April
26/1996 እንዲሁም ‘አዲስ ትሪቡን’ ግንቦት 4/1988ዓ.ም እትሞች ላይ ዘግበውታል፡፡
ፊልሙ በጊዜው አሜሪካን ሐገር ታትሞ አንዱ ካሴት በ15ዶላር የተሸጠ ሲሆን የኢትዮጵያ ተመልካቾችም በአጭር ጊዜ ውስጥ
ተሻምተው የገዙት ተወዳጅ ፊልም ነበር፡፡
እጅጋየሁ በብሔራዊ ቲያትር ቤት በፍሪላንሰርነት ስትሰራ የገጠማትን የፊልም ባለሙያና መምህር ብርሐኑ ሽብሩ እንዲህ
ያስታውሳል፡፡
‹‹ብሔራዊ ቲያትር ይቀርብ የነበረን የበዓል ዝግጅት እንዳይ ነበር የጋበዘችኝ፡፡ በዕለቱ ትዘፍን ነበር፡፡›› ይላል
ጋሽ ብርሐኑ
‹‹በርካታ ሰዎች የታደሙበት ዝግጅት ላይ ድምጻዊያኑ በአስተዋዋቂ ስማቸው እየተጠራ፣ ችሎታቸው እተወደሰ፤ ታዋቂ የሆኑም
ያልሆኑም አቀንቃኞች ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ጂጂ ፀሐይ የተባለ ሥራዋን ነበር ያቀረበችው ተቀባይነቷ ግን ብዙ አልነበረም፡፡
ከዝግጅቱ በኋላ አንድ የገረመኝን ነገር ጠየኳት፡፡ መድረክ ላይ የወጣችው ስሟ ሳይጠራ በመሆኑ፤ ምክንያቱ ምንድነው አልኳት፡፡ ያኔ
ባስታወስኩት ቁጥር የሚገርመኝን ነገር ነገረችኝ፡፡ ታዋቂ ስላልሆንኩ ስሜን አይጠሩትም፡፡ ያለ አጋፋሪ ነው መድረክ ላይ የምወጣው፡፡››
የፊልምና የሙዚቃ ጅማሬዎቿን አስመልቶ የኖረቻቸውን ገጠመኞች ተንተርሰን ተሸላሚዋ ተዋናይት እና ስሟ የማይጠራው ዘፋኝ
ብንላት ተሳስተን ይሆን?
***
በዓለማቀፍ ደረጃ እውቅናን እና ታዋቂነትን፣ አድናቆትን ያተረፉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ በቅድሚያ
የወገናቸውን ጭብጨባና አድናቆት አግኝተዋል፡፡ በሐገርቤት ሰዎች ምርቃት ታጅበው ነው ዓለማቀፉን ጎራ የተቀላቀሉት፡፡ ለነዚህም አስቴር
አወቀን (ካቡ በሚሰኝ አልበሟ ባገኘቸው ስኬት)፣ መሐሙድ አሕመድን እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ የእጅጋየሁ ግን ተገላቢጦሹን
ነው፡፡ ተደናቂነቷ የጀመረው ከባህር ማዶ ነው፡፡ በወቅቱ CNN ቴሌቪዥን ‹‹New talented Ethiopian singer Gigi››
ብሎ ሰፋ ያለ ዘገባ ሰርቶላታል፡፡
ጂጂ እስካሁን 7 አልበሞችን ሰርታለች፡፡ ፀሐይ በ1997፣ One Ethiopia በ1998፣ ጂጂ(ጉራማይሌ) በ2001፣
illuminated Audio (laswell’s remix of the 2001 album ‘Gigi’) በ2003፣ Abyssinia
infinite: Zion Roots, በ2003፣ ሰምና ወርቅ በ2006፣ ምስጋና ኢትዮጵያ በ2010፣ (ሁሉም ዓመተምህረቶች በአውሮፓውያን
የዘመን አቆጣጠር ናቸው፡፡) ከፋንታሁን ሸዋንቆጨው ጋር በጋራ ያስቀረጹትን አልበም ስንጨምርበት 8 ይደርሳል ማለት ነው፡፡ ይህን
ቁጥር ፀሐይ ከወጣበት 1990ዓ.ም ጀምሮ ቢሰላ በ2.5 ዓመታት ልዩነት አንድ አልበም ሰርታለች ማለት ነው፡፡
ከአልበሞቹ መሐከል በኢትዮጵያ ውስጥ በይፋ የተከፋፈሉት ጂጂ/ጉራማይሌ፣ ጂጂ ሪሚክስ እና ሰምና ወርቅ የተሰኙት አልበሞች
ናቸው፡፡ One Ethiopia ኢትዮጵያ ውስጥ ባይከፋፈልም በጎረቤት ሐገራት በኩል ገብቶ በስፋት የተደመጠ አልበሟ ነው፡፡
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሥራ ውስጥ አስተሳሰባቸው ይንጸባረቃል፡፡ በነባራዊው ዓለም የሚያንገበግባቸው፣ የሚከነክናቸው፣
የሚቆጫቸው፣ ወይም በተቃራኒው የሚያስደስታቸው፣ የሚያጓጓቸው፣ ቢሆን ብለው ሚመኙት አንዳች ተመሳስሎ በሚሠሩት ውስጥ ይኖራል፡፡
ደራሲያን በድርሰቶቻቸው የሚያነሷቸው ሐሳቦች በሙሉ እውነተኛ እምነቶቻቸው ናቸው! ብሎ መደምደም ባይቻልም፤ ደጋግሞ
የሚመላለስ የሐሳብ ክር - ከአንድ በላይ በሆኑ ሥራዎቻቸው ላይ ሲስተዋል ‹ነው!› ብሎ ለመፈረጅ ድፍረትን ያድላል፡፡ ደራሲው ሆነ
ብሎም ይሁን ባገጣጣሚ በልዩ ልዩ ቀለም እና ማእዘን የገለጠው፣ የነካካው፣ የዘመረለት፣ ቁምነገር - የአብይ ሐሳቡ አቀንቃኝ መሆኑን
ያሳያል፡፡ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ፣ የፍቅር ወይም የጥላቻ፣ የናፍቆት ወይም የዝንጋኤ ክልል ውስጥ ነው ብሎ ለማሔስ በር ይከፍታል፡፡
ይህንን የመሰለ ከባድ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መታለፍ የሚገባቸው ሒደቶች አሉ፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸውን የደራሲውን ሥራዎች
በአግባቡ መርምሮ የነገሩን ተደጋጋሚነት ማስተዋል ብቻ ግን አይበቃም፡፡ በግልጽ እንዲታዩ ተደርገው ከተቀመጡት በተጨማሪ ስውር መመሳሰሎችንም
ማሰስ ያስፈልጋል፡፡ ሆነ ተብሎም ይሁን በደራሲው ደመነፍሳዊ እሳቦት(Unconscious mind) የተወለዱ ሐሳብቦችን፣ ገለጻዎችን፣
የቋንቋ አጠቃቀምን . . . ምስስሎሻቸውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡
አንዳንድ ግዜም ከዋናው ፈጠራ(creativity) እና ከአብይ ጭብጡ(Content)፣ በተጓዳኝ አቀራረቡ(Performance)
ድምዳሜውን ለማጠናከር የሚያግዙ ግብአቶች ይሆናሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚዘወተር ባይሆንም፤ የቀረበበት ቀን ለፍረጃ እና ለድምዳሜ
የሚያበቃ ሰበብ ነው፡፡ ለምሳሌ የካቲት 23 ስንል - ግንቦት 20 ስንል - የሚመጡልን ስዕሎች ስለሚኖሩ . . .
የዚህ መጣጥፍ ርዕስ ‹ኢትዮጵያዊነትን የምታስተጋባ አርቲስት› የሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ጂጂ መሥፈርቶቹን በሙሉ በሥራዎቿ
ታሟላለች፡፡ የግጥሞቿን የሐሳብ ጥልቀት፣ የምናቧን ምጥቀት፣ የቋንቋዋን ውበት . . . አድንቀን እና ተደንቀን ስናበቃ - ስንኞቹ
የሚጋልቡበት የሐሳብ ፈረስ ላይ ተፈናጠን ለመገንዘብ ስንሞክር፡- የሐገር እና የሐገር ሰው ፍቅር፣ የሕዝቦች አንድነትና መከባበር፣
ማንነትን መውደድና ማክበር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የሐገር ሰው ፍቅር
የእጅጋየሁ የፍቅር
ግጥሞች ሐገራዊ ርዕሰ ጉዳይን ከምታነሳባቸው ግጥሞች ጋር ሲነፃፀሩ ያነሰ ደረጃ አላቸው፡፡ ሐገራዊ አጀንዳዎች ስታነሳ ሐሳቧ ይሰላል፡፡
ቋንቋና ዘይቤዋም ይበረታል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የምታስተጋባ አርቲስት የሚል ድምዳሜ ላይ ካደረሱን ምክንያቶች መሐከልም አንዱ ሰበብ
ይህ ነው፡፡
የጂጂ የፍቅር ግጥሞች
ሌላው ባህሪ ተሸናፊነታቸው ነው፡፡ ሁሌም ለፍቅር ይንበረካኩ፡፡ ሁሌም ለውበት ይሸነፋሉ፡፡ ነገር ግን አያለቅሱም፡፡ ጣልከኝ፣ ከዳኸኝ፣
በደልከኝ አይሉም፡፡ የበዛ አካላዊ ገለጻም አይስተዋልባቸውም፡፡
ሐሳቦች አለማቀፋዊ
ናቸው፡፡ ፍቅር፣ ረገብ፣ ጥጋብ፣ ንዴት . . . በሁሉም የዓለም ክፍል ላይ አሉ፡፡ የሰውልጅ ባለበት ሁሉ ይገኛሉ፡፡ የተነሳው
ሐሳብ ኢትዮጵያዊ ነው እንድንል የሚያስገድደን ግን የሔደበት መንገድ ነው፡፡ የተገለጸበት ሁኔታ ነው፡፡
የጂጂን የፍቅር ዘፈኖች
የሚለያቸው ለሐገር ሰው የተሰጡ መሆናቸው ነው፡፡ አንዳች ሰበብ ፈልጋ ተፈቃሪውን ሐበሻ ታደርገዋለች፡፡ ኢትዮጵያዊ ቀለም ትቀባዋለች፡፡
ለምን ለምን ትቀራለህ
ልቤ አንተን ተርቦ አይኔ እየናፈቀህ
የፈረሱን ዱካ አየሁት
ኮቴውን ሰማሁት
ለካስ ጋልቦ ሔዷል እንደፈራሁት
ከላይ ለመጠቃቀስ እንደሞከርነው
የተሸናፊ ድምጽ ነው፡፡ ናልኝ ጥለኸኝ አትሂድ የሚል የአፍቃሪ ጥሪ
ጓዜን ጠቅልሉልኝ እሔዳለሁ ፍለጋ
አይናማ ሰው ሎጋ
ሎጋ፣ አይናማ፣ ቆንጆ፣
ደማም፣ . . . የተባሉ የውበት መስፈሪያዎች በበርካታ ዘፈኖቿ ላይ ይዘወተራሉ፡፡ ይህ አይናማ ይህ ተወዳጅ ሎጋ ወንድ ሐበሻ ነው፡፡
‹የባቲን ልጅ ጥሩት
የራያ የቆቦን› ተብሎ ልዩ ሥፍራው ይነገራል፡፡
ጨረቃ ባትወጣ ደምቃ ባትታይ
አንተ ትበቃለህ ላገሬ ሰማይ . . .
ከ ሰም እና ወርቅ አልበም ‹የማነህ ቆንጆ› ከተሰኘው
ዘፈን ፡-
ና ውሰደው ፍቅርህን እጄ ተዘርግቷል
ትላንትናም ዛሬም ልቤ ላንተ ተንበርክኳል
‹ደማምዬ› በተሰኘው ዘፈን ደግሞ
ከበሮውን ምቱት በገናም ይደርደር
ምንም አይለየኝም ካገሬ ልጅ ፍቅር
ይባልለታል፡፡ .
. . . . . ወደ ሌላ ዜማ እናምራ ‹‹ሳላየው››
ሳላየው አላድርም አይነጋም ሌሊቱ
ጀንበሯን ቀድሜ እደርሳለሁ ቤቱ
.
በካህን ሺብሻቦ በሊቅ በዲያቆኖች ዜማ
ቢወደስ ቢመለክ በታላቅ ጉባይ ቢሰማ
ሺ ቃላት የሚያንሰው የወንድ የቆንጆዎች አውራ
የታተምከው ፈሳሽ በልቤ የገነት አዝመራ
ከንጋት በፊት ልታየው
የምትጓጓለት ጉብል፤ ልቧ ከሱጋር ሊኖር የገሰገሰላት ተፈቃሪ፤ ግርማው እንደ አንበሳ፤ ውበቱ እንደ ጸሐይ የሆነለት ሰው ከወዴት
ነው?
ፀሐይ ብልጭ አለች ጠራ ፈካ ገመገሙ
ክፈት ዓይንህን ልይ ውዴ የሐገር ልጅ ደማሙ
ሆነ ብላም ይሁን ሳይታወቃት
የሐገር ብቻ ሳይሆን የሐገርሰው፤ የትውፊት እና ባህሉ ፍቅር ውስጥ በብርቱ መውደቋን በስራዎቿ ውስጥ ደጋግማ አሳይታለች፡፡ በኑሮዋስ?
ብርቱ የሐገር ፍቅር
እንዳላቸው የሚነገርላቸው፤ በስራዎቻቸው በተደጋጋሚ የሐገር ፍቅርን የዘመሩ፤ ከባድ ውለታ ለሐገርና ለወገን የዋሉ . . . ጥቂት
የማይባሉ ሐበሾች የውጪ ዜጋ አግብተዋል፡፡ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ፣ አክሊሉ ኀ/ወልድ፣ ሐይሌ ገሪማ (ፕሮፌሰር)፣ ተወልደ ገ/እግዚአብሔር
(ዶ/ር) የእነዚህ ሁሉ የትዳር አጋሮች ኢትዮጵያዊያን አይደሉም፡፡ እጅጋየሁም እንዲሁ አብዝታ የዘፈነችለትን ሐበሻ አላገባችም፡፡
ልጁ መንገደኛ የሰውሐገር ሰው
ምን ሊፈይድልኝ ዓይን ዓይኑን ባየው
ብላ አንድ ጊዜ ያዜመችለትን
ሌላ ዜጋ አገባች እንጂ፤ ይህንን ወግ በአንድ ወቅት ከወዳጄ (የሁሉም ወዳጅ መሆን ይችልበታል) ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ጋር የተጨዋወትነው
ነው፡፡ ‹ማዕቀብ› የተሰኘ መፅሐፉ ላይ ስላሰፈረው ገራሚ ቁምነገር ስናወሳ በእግረመንገድ የነገረኝ ነው፡፡ እውቁ አርበኛ ጃገማ
ኬሎ ሴት ልጆቻቸውን የዳሩት ለጣሊያናዊያን ነው፡፡ ማዕቀብ ገፅ 189 ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡ ለኢትዮጵያ ስነጽሁፍ ብዙ ካበረከቱ
የብዕር ሰዎች መሐል በዓሉ ግርማ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ መስፍን ሐብተማርያም ክልሶች ናቸው፡፡ ተስፋዬ ገሰሰም ክልስ አህያ
መልስ እየተባሉ ካደጉት መሐል ነው፡፡
ለሐገር ተቆርቋራቹ
የውጪ ዜጋ የማግባትን፤ የክልሶቹ በፅሁፍ ስል የመሆንን፤ ነገር ምላሽ ካልተገኘላቸው
ጥያቄዎች ውስጥ እንደምረውና ጂጂን ይዘን ወደፊት አንጓዝ፡፡ የእጅጋየሁ ባለቤት ቢል ላስዌል ይባላል፡፡ አንድ ልጅ አላቸው፡፡
የባህል እና የትውፊት ፍቅር
‹‹ዘፈን ስፅፍ የማውቀውን
ነገር ነው እምጽፈው ሌላውንማ ከየት አባቴ ላምጣው? ህልም ሳይ እንኳን ሳይ እሱን ነው እማየው›› ምትለው ጂጂ ያደገችበትን፣ የኖረችበትን
እና ጠንቅቃ የምታውቀውን ኢትዮጵያዊ ትውፊት በዘፈን ግጥሞኖቿ ጣል ጣል አድርጋ ታቀርባቸዋለች
‹‹እንግጫ ጎንጉኜ ባደይ በሶሪት
እንቁጣጣሽ ብዬ ቤቱ ላኩለት
እሰይ መስቀል ጠባ ቅዱስ ዮሐንስ
ብዎድ እኖራለሁ ብጠላ መሰስ››
የኔ
ነው በሚለው ዘፈኗ ደግሞ
በዚች በማተቤ አምልልሐለሁ
ፍቅርን ካልሰጠኸኝ እሞትብሐለሁ
ሌላ ምሳሌ፡-
ሌላ ምሳሌ፡-
ሸጌ ኩታህን ልበስና
በቀዩ ጃኖ ተውበህ ና
አውዳመት ይሁን ከተማው
ነጭ በነጩን ልበሰው
ከዚህ ለሚበዙት ማሳያዎች
ደግሞ ለአድማጩ የቤት ሥራ ሰጥተን እንለፍ፡፡
***
አንድ የጥበብ ሥራ
በበርካታ መስፈሪያዎች እየተለካ ደረጃው ሊመዘን፣ ርቀቱ(መርቀቁ) ሊመተር ይችላል፡፡ በአንዱ መስፈሪያ ገለባ የተሰኘው፤ በሌላኛው
መስፈሪያ አድናቆቶች ሊያስተናግድ ይችላል፡፡ በሁሉም ምርጥ ከሚባሉት ጥቂቶች መሐከል ጂጂ አንዷ ነች፡፡ የጂጂ ዜማ መሰረቶች የቤተክርስቲያን
ቅዳሴ፣ (አባ አለም
ለምኔ) የላሊበላዎች እንጉርጉሮ፣ ( ናፈቀኝ ) ባህላዊ የደቦ ዘፈኖች (አንተን
ያመነ ሁሉ ዳነ፣ የሆንኩትን አልሰማ፣ ዓለም አለፈኝ ) ናቸው፡፡
ብርሐኑ ገበየሁ- የአማርኛ
ሥነግጥም በተሰኘው የንድፈ- ሃሳብ፣ ማብራሪያና ትንታኔ መጽሐፉ እንዳስቀመጠው፤ የአገጣጠም ዘዬዋ ተናጋሪ ስዕል (Philip
Sydney) የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ግጥሞቿ እንደ ተንቀሳቃሽ ምስል ቃላቶቹ የተሸከሙት ድርጊት ቁልጭ ብለው እንዲታዩን የማድረግ
ብቃታቸው ሐያል ነው፡፡ የተመረጡ ቃላትን በተመረጠ ቦታቸው ብቻ ትጠቀማለች እንጂ አትደርትም፡፡
ጋዜጠኛ ወንድሙ ሐይሉ
‹‹በግጥም ስራዋ ታግዣታለሽ?›› ብሎ ለጠየቃት እናቷ ተናኜ ስዩም ስትመልስ
‹‹ራስዋ ናት የምትሰራው፡፡
ምንም ሳትጨነቅ ነው የምትሰራው፡፡ በጣም ጎበዝ ናት፡፡ እንደቤተሰብ እንዲህ ቢሆን እንዲህ ብታደርጊ የሚል አስተያየት ሊኖር ይችላል
እንጂ ራስዋ ናት እምትሰራው›› የሚል መልስ ሰጥታለች፡፡
ጂጂ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ
እድገት የተጫወተችው ሚና ቀላል አይደለም የሚሉ ምሁራን አሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እድገት አንጻራዊ ነው፤ የእድገቱ መለኪያ ከምን
የጀመረ ነው? ከየትኛው ዘመን ጋር ሲናጸር ነው እድገት የሚለው ደረጃ ላይ ሊደርስ የሚችለው? ብለው የሚጠይቁ ተሟጋቾች አሉ፡፡
የምሁራኑን ተዋስዖ (intellectual discourse) ወደጎን ብለን አንድ እርግጠኛ ጉዳይ እናንሳ፡፡ ሙዚቃችን በዓለማቀፍ
ወረጃ እንዲደመጥ በቋንቋችን መዝፈን አለመዝፈናችን ለውጥ እንደማያመጣ አሳይታናለች፡፡
የሐገር ፍቅር
ከላይ የሐገር ሰው ፍቅር በሚል አርእስት ውስጥ የተመለከትናቸው ዘፈኖች ዋና መልእክታቸው ፆታዊ ፍቅርን ማዕከል ያደረገ
ነው፡፡ የገለፃው ሒደት ግን የሰውየውን ከየትነት እንዲናገር በማድረግ የተሰራ ነው፡፡ የሐገር ፍቅር በሚለው ውስጥ የተካተቱት ዘፈኖች
ቀዳሚ አጀንዳ ሐገር ነው፡፡ በዚያ ውስጥ ባለውለታዎች ይጠራሉ ይወደሳሉ፡፡
እህህ እስከመቼ ያዘላልቀናል
ገና ብዙ መንገድ ብዙ ይቀረናል
ሲል ይጀምራል፡፡ ይህ ዘፈን በስፋት የመደመጥ እድል ከገጠማቸው ስራዎቿ መሐከል
የሚመደብ ነው፡፡
‹‹እህህን ለፈረስ ያስተማርኩ እኔ ነኝ
እሱ ድርቆሽ ሲያጣ እኔ ሲቸግረኝ››
በሚል
ማህበረሰብ ውስጥ እንደማደጓ የቸገራትን፤ ያሳሰባትን ነገር ልትገልጥ ስትነሳ ‹‹እስከመቼ ነው›› ብላ በመጠየቅ ነው፡፡ ‹‹ምኑ
ተነካና›› ብላ ራሷን በማጀገን ነው፡፡
እህህ እስከመቼ ያዘላልቀናል
ገና ብዙ መንገድ ብዙ ይቀረናል
እስኪ ፈጠን ይበል እግር ተራውን
ምን ያኳትንሐል አመድ ለአመድ
ከሚል ተግሳጽ በመለስ
‹‹አይ አይ አይ›› በሚል ምሬት አዘል ንግግር ይጀምራል፡፡ የምንገኘው የግጥሙ የዕውቂያ ክፍል ላይ ነው፡፡ ዋናውን ርዕሰጉዳይ
ለመጨበጥ የምንንደረደርበት፤ ባደመጥናቸው 4መስመር ሰንኞች - አይሆኑ የሆነን ተግባር የምትገስጽ በክፋቱ የምትማረር ገራገር እናት
ወይም እህት ምስል ሊከሰትልን ይችላል፡፡ አያዛልቅም የተባለለት ችግር ምን ይሆን?
ልቤ በፍርሐት እጅግ ተበክሏል
በረሐብ በጥማት ሰውነቴ ዝሏል
እግሬ አልንቀሳቀስ እጄ አልሰራ ብሏል
ጆሮዬም አልሰማ አይኔም አላይ ብሏል
ቀደም ብለን ባለሳናቸው
ስንኞች እግር ‹እስኪ ፈጠን በል!› የሚል ተግሳጽ ለምን እንዳስተናገደ አሁን እንረዳለን፡፡ በረሐብ በጥማት ሰውተቱ የዛለበት ሰው
የሰውነት አካላቱ የስሜት ህዋሳቱ አለመታዘዛቸው ብርቅ አይደለም፡፡ ተለምዷዊ ነው፡፡ ግምታችንን የሚያፈርሰው ቀጣዩ ስንኝ ነው፡፡
የራበኝ እንጀራው ወይኑ መስሏቸው
የጠማኝ ወተቱ ወይ ጠጁ መስሏቸው
ችግሬ ጭንቀቴ ምንጩ ያልገባቸው
ያቺ ሰው ተራበች ሲሉኝ ሰማኋቸው
ረሐቡ የምግብ እና
የመጠጥ ረሐብ አይደለም፡፡ ጥያቄው የመጥገብ እና የመርካት አይደለም እንድንል የሚያስገድዱ ስንኞች ናቸው፡፡ ከላይ እዳነሳነው ረሐብ
ዓለማቀፋዊ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ቦታ ለዚህ አካባቢ ሳይባል ሊገለጽ ይችላል፡፡ ‹የራበኝ እንጀራው› ከሚለው በፊት ያሉት ስንኞች
በሙሉ የወል ናቸው፡፡ የትኛውም የዓለም ጥግ ያለ ፍጡር የኔ ሊላቸው ይችላል፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥ ‹እንጀራ እና ጠጅ› ቦታን አመልካቾች
ሆነው ይመጣሉ፡፡ በእንጀራ ፋንታ ዳቦ (በአብዛኛው የዓለም ክፍል ስለሚገኝ)፤ በጠጅ ፋንታ ውሃ ቢባል ኖሮ ግምታችንን ባከሸፈብን
ነበር፡፡ እንጀራና ጠጅ ጮክ ብለው እየተወራ ያለው ስለ ኢትዮጵያ ነው ይሉናል፡፡
እኔን የራበኝ ፍቅር ነው
ብሎ የመጀመሪያው የዜማ
ምዕራፍ ይደመደማል፡፡ የአካል ክፍሎችን እና የስሜት ሕዋሳትን ከሥራ ውጪ የሚያደርግ እንደምን ያለ ፍቅር ረሐብ ነው? ቀጣዩ ስንኝ
ግን መልሱን በመስጠት ፈንታ ሌላ ጥያቄን ይፈጥራል
አበባው ሲረግፍ ስሩ ሲበጣጠስ
ዝም ብለህ አትየው ወድቆ ሲበሰብስ
የምን
አበባ? ከየት የመጣ ስር? አበባው የምን ምሳሌ ነው? መሬት ቆንጥጦ ይዞ የያዘው ስር - የዘር መብቀያው ምድር ላይ ወድቆ ለምን
በሰበሰ? እነሆ ምላሽ
ጎጃም ያረሰውን ለጎንደር ካልሸጠ
ጎንደር ያረሰውን ለጎጃም ካልሸጠ
የሸዋ አባት ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ
የሐረር ነጋዴ ወለጋ ካልሸጠ
ፍቅር ወዴት ወዴት ወዴት ዘመም ዘመም
ሐገርም አለችኝ ወገን የኔ ህመም
ስሩ እንዳይበጠስ መቋጠሪያው ደሙ
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው ቀለሙ
የእህል
እጦት ብቻ ሳይሆን የፍቅር ረሐብም እንቅስቃሴን ይገታል፡፡ የስምምነት ረሐብም አካል እንዳይታዘዝ የማድረግ ብርቱ አቅም አለው፡፡
የግጥሙ መድፊያ
ስሩ እንዳይበጠስ መቋጠሪያው ክሩ
አረጓዴ ቢጫ ቀይ ነው ከለሩ
ቢሆንስ? ምን ይፈጠራል?
የሚሰብረው ዜማ አይኖርም፡፡ የግጥሙ እና የዜማው ሜትሮች አቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን የሚያፋልሰው ሐሳብ አለ፡፡ በግጥሙ ከፍ ያሉ
መስመሮች ላይ የተጠቀሰውን አበባ ምንነት ይመልሳል፡፡
አበባው በልዪነታችን
ውስጥ ያለው ውበት ነው፡፡ በአንድነታችን ውስጥ ያለው ፍቅር ነው፡፡ ያስተሳሰረን ገመድ አደንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቃችን ነው፡፡ ሦስት
ዓይነት ሥር፡፡ አንዲትን አበባ ለማኖር በአንድ ግንድ ላይ ተሳስሮ የሚኖር ሦስት ዓይነት ስር፡፡ ሦስት ዓይነት ደም፡፡
በተሳሰረ የዘር ግንድ
በቅሎ ህብረብሔራዊነትን ያዘለ ደም፡፡ ከአንድ ጎሳ ተቀዳ ማለትን የማያስችል የሁሉም የሆነ - ከሁሉም የሆነ ደም፡፡ አበባዋ ለቆመችባት
ምድር፤ ስሯን ቆንጥጣ ለቆመችባት መሬት የተከፈለ ደም፡፡
ለዚህ ነው ባለቅኔዋ
‹ስሩ እንዳይበጠስ መቋጠሪያው ደሙ› ማለቷ
ይህንን ሁሉ ከባድ
መልእክት በቀላል እና ግልፅ ቋንቋ፤ (ቀላል ማለት ተራ ማለት አይደለም) ያስተላለፈ ውብ የልብ መዝሙር፡፡
One
Ethiopia አልበም በስፋት እንዲደመጥ ያስቻሉት፡- የተለየ የቅንብር ከለር ይዞ መምጣቱ፣ በድምፁ ጥራት ብቻ አይደለም፡፡ ስንኞቹ
የተሸከሙት መልእክት እንደሆነ አምናለሁ፡፡
‹‹ከቢላስዌል ጋር
መገናኘትሽ በሙዚቃሽ ላይ ብዙ አስተዋጽኦ እንዳለው ይነገራል፡፡ አንቺስ ምን ትያለሽ?››
በማለት ለጠየቃት አንድ
የባህርማዶ ሚድያ ጋዜጠኛ እንዲህ የሚል መልስ ሰጥታለች፡፡
‹‹ባለቤቴ የድምጽ
ባለሙያ ነው፡፡ ድምጽ ደግሞ የሚደመጥ እንጂ የሚነገረው ነገር አይደለም፡፡›› አሁን ያለችበት የድምጽ ደረጃ(Vocal) እና አዘፋፈን
ፀሐይ አልበም ላይ ካለው ጋር ሲነጻፀር ያለው ልዩነት ልምድ ማግኘቷ እንደጠቀማት ያሳያል የሚሉ የሙዚቃ ተንታኞች አሉ፡፡ ባለቤቷ
ቢል ላስዌል ግን በሐሳቡ አይስማማም፡፡
‹‹ ጂጂ ተሰጥዖ ያላት ድምጻዊት ነች፡፡ በአሰልጣኝ የተገራ ድምጽ የላትም፡፡ ማዜምን የታደለች
ተፈጥሯዊ ዘፋኝ ናት፡፡ ለበርካታ ጊዜ ሳትዘፍን ሳትለማመድ ብትቆይም ችሎታዋ አይነጥፍም፡፡ በብርቱ ጥረት ተአምራዊ ለውጥ የምታመጣም
አይደለችም፡፡ ተፈጥሯዊ ስጦታዋ ነው፡፡ በመድረክ የመጫወት እድሉን ስታገኝም ከልቧ ትዝናናበታለች፡፡›› ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
አንድ
ናት የተሰኘውን ዘፈኗን ደግሞ ቀጥለን እንመልከት
የማንነቴ መለኪያ ኩራቴ መመኪያዬ ክብሬ
የሦስት ሺህ ዓመት እመቤት አንድ ናት ኢትዮጵያ ሐገሬ
በማለት
ታዜምና፣ ያለፉትን 3ሺ ዘመናት ስንቃኝ መንገዶቹ ሁሉ ቀና አለመሆናቸውን በማስተዋል ይመስላል እነዚህን ስንኞች የምታስከትለው፡፡
ዘመን አመጣሽ የዘር በሽታ
መድሐኒት አለው የማታ ማታ
ሐገር በወገን እንዴት ይረታ
ፍቅር በነገር እንዴት ይፈታ
ዘር ሳይለያየን ወይ ሐይማኖት
ከጥንት በፍቅር የኖርንባት
እናት ኢትዮጵያ ውዲት ውዲቷ
በጎጆ አያልቅም ሙሽርነቷ
እማማ
በጎጥ እና በቀበሌ
የመከፋፈል አባዜው ዘመን አመጣሽ በሽታ ነው፡፡ ታክሞ ሊፈወስ የሚችል ህመም ነው፡፡ ትለናለች፡፡
ሐገር በውበት ወጥመድ ተይዛ
የዘመን ስቃይ ጭንቅ እንደዋዛ
ከዚህ
ቀጥላ በምትደረድራቸው ስንኞች የራሷን ኢትዮጵያ ገንብታ ዘመናችንን ጥለን ወደኋላ እንድንጓዝ ታስገድደናለች፡፡ ወደ አፄ ቴዎድሮስ፡፡
ወደተረሳው ህልማቸው፡፡
ሐይለኛ አርበኛ አርበኛ ላይ
ልውጣ መቅደላ ልበል ዋይ ዋይ
ምነው ቢነሳ መይሳው ካሳ
አልወድም ጎበዝ ጀግና ሲረሳ
“ጀግና ሲረሳ” አንድም
ብዙ ያበረከተ ጀግና ሲዘነጋ አልወድም፡፡ ማለት ይሆናል፡፡ አንድም መሪ ሐሳብ ያላው ጀግና ሐሳቡ ሲተው፣ ተከታይ ሳይኖረው፣ .
. . ሲረሳ አልወድም፡፡ በሚል ልንፈታው እንድንችል ክፍት አድርጋ ጽፋዋለች፡፡
እማማ
እናት ኢትዮጵያ እማማ አንቺ እናት ዓለም እያለች ስታዋያት የቆየች የሐገሯን በአጤ ቴዎድሮስ ቃል ዘፈኑን ትደመድመዋለች፡፡ ‹‹ቃል
የዕምነት እዳ እንጂ የናት ያባት አይደለም!››
የኀይለ ሥላሴ - የምኒሊክ እጅ
የምዬ ጣይቱ - የዮሐንስ እጅ
ተነሳ ተነሳ አላማህን አንሳ
በጭራህ አስተኛው ጅቦ ጠግቦ አገሳ
የምትለን ደግሞ ‹ሰላም›
በተሰኘው ዘፈን ነው፡፡ ‹ጂጂ/ጉራማይሌ› በሚለው አልበሟ ውስጥ ይገኛል፡፡ የቀደምቶቹን በጎ ተግባራት ጎትታ በማምጣት ሰላምን ለመስበኪያ
ትጠቀምበታለች፡፡
ሰላም ላለም ይሁን ሰላም ለምድራችን
ሰላም ላለም ይሁን ሰላም ላገራችን
ምቀኝነት ይጥፋ ከሰውነታችን
ለመልካሙ ስራ ይፍሰስ ጉልበታችን
ቀና መልእክቶችን ተግተው
የሚሰብኩ ግጥሞች ባለቤት ናት፡፡ ችግር የመሰላትንም ትገልጻለች በዘመናዊው ዓለም በህዝቦች ጦርነት እንጀራቸውን ስለሚያበስሉም ዝም
አላለችም፡፡
ሆድ አይሞላምና ይሔ ገንዘባቸው
ሰላም ይስጡንና አርሰን እናብላቸው
ሐገር ማለት? በሚለው
ጥያቄ ውስጥ አከራካሪ ምላሾች አሉ፡፡ ሐገር ማለት ሰው ነው፡፡ ሐገር ማለት መሬቱ ነው፡፡ የሚሉ የእጅጋየሁ ሐሳብ በዘፈኖቿ ውስጥ
ሲታይ ሐገር ማለት ሰው ነው ወደሚል ምላሽ ያደላ ይመስላል፡፡
ተራራው ሰው ሆኖ ከንፈሬን ባይስመኝ
ተራራው ሰው ሆኖ ጡቴን ባይዳብሰኝ
ተራራው ሰው ሆኖ ዓይን ዓይኑን ባላይ
ፀሐይ እሞቃለሁ ወጥቼ ከላይ
የተሰኘው ዘፈን ግን
ድምዳሜውን ያፈርሰዋል፡፡ ሐገር ማለት ሁለቱም ነው፡፡ የሚል ምላሽ ያስገኛል፡፡ አፈሩም ኗሪውም፡፡
በአሁኑ ሰዓት የምትገኝበትን
ሁኔታ በተመለከተ እህቷ ሾፊያ ሽባባው እና እናቷ ተናኜ ስዩም ለተለያዩ የሐገር ውስጥ ሚድያዎች እናዳሳወቁት በማህበራዊ ሚድያዎች
ተጋኖ እንደተሰራጨው ወሬ ባይሆንም መለስተኛ የጤና መታወክ አጋጥሟታል፡፡ ይህም በመላው ቤተሰቧ እንክብካቤ እና ፍቅር በመታከም
ላይ ነው፡፡ ዳግም በመድረኩ እንድትነግስበት፤ በግጥም እና በዜማዎቿ ፍቅርና አንድነትን የምትሰብክበት ዘመን የቀረበ እንዲሆን የዝግጅት
ክፍላችን መልካም ምኞቱን ይገልፃል፡፡
ጂጂ ብቻቸውን ሰፋ
ያለ ትንታኔ ሊሰራባቸው የሚችል ትላልቅ ዘፈኖች አሏት፡፡ ካህኔ፣ አድዋ፣ ናፈቀኝ እና ሌሎችም፡፡ በዛሬው የዘመን እና ጥበብ የጥበብ
አምድ ህይወት እና ስራዋን በጥቂቱ ለማየት ሞክረናል፡፡ በዚህ ምልከታ ብዙም ትኩረት ያልተረደገባቸው ስራዎቿ ላይ አተኩረናል፡፡
ወደፊት በተናጠል ሥራዎቿ ላይ እንመለሳለን፡፡ የዛሬውን የምናጠናቅቀው ግን ‹ምስጋና› በሚለው ዘፈኗ ያነሳችውን እውነት በመግለፅ
ነው፡፡
ሐይልን በሚሰጠኝ በእግዚአብሔር አምናለሁ፡፡
ለስሙም ለክብሩም ቆሜ እዘምራለሁ፡፡
እግዚአብሔር ጥቁር ነው ነጭ ነው አትበሉ
እሱ የፈጠረው ሁሉንም ባምሳሉ
በመልክ ይመስለናል እኔንም አንተንም
የአንድ አባት ልጆች ነን እህትና ወንድም
እውቁ ሰዓሊ ገብረክርስቶስ
ደስታ ይህንን ሐሳብ እንዲገልጽለት ኢየሱስን በቀይ ቀለም ስሎታል፡፡ በቀይ እና በጥቁር ቀለም፡፡ መልኩ በደሙ እንዲሸፈን አድርጎ
ሸራ ላይ አስቀምጦታል፡፡ በቀዩ ስዕል (ምስለ ኢየሱስ) በቆዳው ቀለም ሳይሆን በደሙ ዋጅቶናል ሲል ለዓለም ተናግሮበታል፡፡ ይህንን
ስዕል ቴዎድሮስ ካሳሁን ግሩም ግጥም ጽፎበት በንባብ አስደምጦናል፡፡ ጂጂም በተራዋ ‹በመልክ ይመስለናል እኔንም አንተንም› አለች፡፡
በጂጂ ዘፈኖች ውስጥ
ሰው መሆን በውልደት የሚገኝ አይደለም፡፡ እነሆ ማስረጃ ‹ባለቅኔ› ከሚለው ዘፈን
ውበት ባለችበት ውበት ትኖራለች
ብርሐን ባለችበት ብርሐን ትኖራለች
ደግነት ባለበት ደግነት ይኖራል
ኑር ብለው ያኖሩት ካኖሩት ይገኛል
ሰው ካለማወቁ ሰውነት ይማራል፡፡
‹ሰው ካለማወቁ ሰውነት
ይማራል› ውብ ነገር ሁሌም ውብ ነው፡፡ ብርሀን፣ ደግነት . . .ጥሩ እምንላቸው ውብ እሳቤዎች ሁሉ ከማወቅ ማህጸን ይገኛሉ፡፡
ማወቅ ደግሞ ሰው ያደርጋል (መወለድ ሳይሆን)፡፡ የሚል ተፈላሳፊ መልእክት አለው፡፡ ሰው መሆን ከማወቅ ይወለዳል፡፡ ሰው ወደመሆን
ከፍታ ሁላችንንም ያድርሰን! አሜን፡፡
© ዘመን እና ጥበብ መጽሔት ጥቅምት 2010ዓ.ም
እትም ላይ የወጣ
No comments:
Post a Comment