ቀደም ባለው ጊዜ በሐገራችን የሚሰራጩ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን ቁጥር አነስተኛ ነበር፡፡ ከ 16ዓመት በፊት FM 97.1 ሳይጀመር፤ ጣቢያዎቹ የሚያስተላልፏቸው ፕሮግራሞች በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ደግሞ ከፍተኛ ነበር፡፡ የዕጅ ሰዓትን ለመሙላት ሳይቀር ማንጸሪያ እና መከራከሪያ ነጥቡ ከራዲዩ እኩል መሆኑ ነበር፡፡ አሁን በርከት ያሉ የራዲዮ ጣቢያዎች ባለቤት ነን፡፡ /የግልም የመንግስትም/ ለኢትዩጵያዊ ታዳሚ እንዲደርሱ ታልመው የሚሰናዱ የሳተላይትና የሀገር ውስጥ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥርም በማሻቀብ ላይ ነው፡፡ የተአማኒነቱ ጉዳይ ግን ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ ዛሬ ዛሬ በራዲዮ ድምጽን ማሰማት የጥቂት ደቂቃዎች ሙከራ ውጤት ነው፡፡ እንደቀደመው ዘመን ከፍ ያለ ትጋት አይጠይቅም፡፡
1. ሁሉም ጣቢያዎች ላይ ያሉት አብዛኛዎቹ ፕሮግራሞች በአጭር በአጭር የሚዘረዘሩ መረጃ ሰጪ ዝግጅቶች አሏቸው፡፡ የአንድን መጽሐፍ ማውጫ እንደማንበብ ያለ ማለት ነው፡፡ እንዲህ መሆኛ 9 ዘዴዎች፤ እንዲያ ማድረጊያ 7 ነጥቦች፤ እንትን የሆኑ 5 ነገሮች. . . በአንድ ወይም በሁለት ሙዚቃዎች ጣልቃ እያስገቡ ‘’እያዝናኑ ያስተምሩናል’’
ገጣሚ ታገል ሰይፉ ኢትዮጵያ ሬድዮ ግጥሞቹን ሊቀረጽ ይሔዳል፡፡ ጊዜው በዚህ መጣጥፍ አቆጣጠር ‹የቀደመው ዘመን› እያልን ስንጠራው የቆየነው ነው፡፡ ግጥም ለመቀረጽ ሬድዮ ጣቢያ ያመራው ታዳጊው ታገል የራዲዮ ድራማ ሲቀረጽ ለመታደም በቃ፡፡ ከመታደምም አልፎ ለድራማው ማጀቢያ ግብአት የሚሆን ድምፅ ሰጪ ላስቲክ ሲያናኮሻኩሽ ተቀርፆ ተመለሰ፡፡ ራዲዩ ጣቢያ ሔዶ ያጋጠመውን፣ የሆነውን ሁሉ ለቤተሰቡ አስረዳ፡፡ መሸ፡፡ በቤተሰቡ በጉጉት የተጠበቀው ድራማ ምሽት ላይ ሲደመጥ አባትና ልጅ በኩራት ተያይተው ብቻ አላበቁም፡፡ ጎበዝ ተባለ፡፡ አባትየው ይህንን የልጃቸውን ገድል ለበርካታ ዘመድ አዝማድና ጎረቤት ተርከውታል፡፡
እውቁ ኮሜዲያን አለባቸው ተካ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በፕሮግራም አቅራቢነት መቀጠር ዳገት ሆነበት፡፡ ውድድሩን፣ ፉክክሩን፣ ውጣ ውረዱን . . . ስላልቻለው መላ ዘየደ፡፡ ሹፍርናን እንደ አንገት ማስገቢያ ተጠቅሞ ተቀጠረ፡፡
ይህ ጽሁፍ ትላንትን በመናፈቅ ዛሬን ለማንኳሰስ የተፃፈ አይደለም፡፡ ይልቁንም የትላንት የሚድያዎችን ጥንካሬ ለዛሬዎቹ ለማጋባት የጓጓ ነው፡፡ ትኩረቱም የመዝናኛ እና የማህበራዊ ፕሮግራሞች ላይ ብቻ ነው፡፡
አንድ ጋዜጠኛ ህዝብ ፊት በቴሌቪዥን ቀርቦ አንዳች ሐሳብ ለመናገር - ስክሪፕት መፃፍ፣ ርዕሰ ጉዳዩን በልዩ ልዩ መልክ ማሰላሰል፣ ተገቢ ግብአቶችን መሰብሰብ፣ . . . ሳይሆን ፀጉርን መፈረዝና በዲዛይነር የተሰናዳ ልብስ መልበስ ቀዳሚ ጉዳዮች መሆን ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡
ሐሳብ ሳይኖራቸው የአየር ሰዓት የገዙ፤ የስፖንሰሮች ማስታወቂያ እና የማህበራዊ ሚድያ ቅንጭብጭብ መረጃዎችን ብቻ ይዘው ‘’አዝናኝ እና አስተማሪ’’ ዝግጅት እያቀረቡ ‘’ዘና ፈታ’’ የሚያደርጉን ፕሮግራሞች አብዝሀውን የአየር ሰአት በብቸኝነት ተቆጣጥረውታል፡፡
ቁጥር ውሸታም የሚሆነው እንዲህ ባለ ጊዜ ነው፡፡ የግልና የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ሚድያዎቻችን ቁጥር መብዛት /የህትመት አላልኩም/ ጥራት ያላቸው ፕሮግራሞች፣ ጥልቀት ያላቸው ሐሳቦች፣ ደርዝ ያላቸው ውይይቶች፣ ውሐ የሚቋጥሩ ክርክሮች፣ . . . እንዲበዙልን አላስቻሉም፡፡ ቁጥሩ ሲጨምር ጥራቱ ቀነሰ
መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ በአንድ የመድረክ ንግግራቸው ‹‹የበዛ ነገር አይከበርም፡፡ ሁሉም ቦታ ያለ አያጓጓም፡፡ ድንጋይ ከወርቅ የሚለየው ሁሉም ቦታ በመገኘቱ ነው፡፡ እንጂማ ወርቅም ድንጋይ ነው፡፡›› ብለው ነበር፡፡ ብዛቱ የወርቁን ክብር ድንጋይ ጎራ እንዳይጨምርብን መጠንቀቅ መጠንቀቅ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ከዘር እና ሐይማኖት ከፖለቲካ ቁጥጥሮች በላቀ የሥነ አእምሮ ልማት የሚያመጡ አመራማሪና ለዋጭ ፕሮግራሞች እንዲኖሩ፣ እንዲበዙና እንዲፈጠሩ መጣር ግዴታችን ነው፡፡
በአንድ ታዋቂ FM ጣቢያ ላይ የሚሰራጭ ‘‘ተወዳጅ’’ ፕሮግራም ላይ እዲህ ሆነ፡፡ የፕሮግራሙ አዘጋጆች አንድ ላፕቶፕ እና ብዙ ድፍረታቸውን አስተባብረው፤ ኢንተርኔትን ተማምነው፤ ሌጣቸውን ወደ ስቱዲዮ እንደሚገቡ ያስተዋሉት የጣቢያው ጋዜጠኞች ተንኮል ሰሩ፡፡ ያለምንም ቅድመ ዝግጅት ጉሮሯቸውን ጠራርገው እዚያው ስቱዲዮ ውስጥ /Live/ ከኢንተርኔት የተረጎሙትን ቀባጥረው መውጣታቸው ቢያበሳጫቸው፤ ህዝብን በዚህ መጠን መናቃቸው ቢያማርራቸው፤ አንድ ነገር አደረጉ፡፡ ወደ ስቱዲዮው የሚገባውን የኢንተርኔት መስመር ነቀሉት፡፡ የቀጥታ ስርጭት ስቱዲዮው ኢንተርኔት እንዳያገኝ ሆነ፡፡ አዘጋጆቹ ተደናገጡ፡፡ ሞከሩ፡፡ ሰኩ ነቀሉ፡፡ ወይ ፍንክች፡፡ አውቆ የተኛው ‘‘ኮኔክሽን’’ ቢቀሰቅሱት አልሰማም፡፡ በእለቱ የሙዚቃ ግብዣ በማድረግ ሰዓቱን ሞሉት፡፡ በየጣልቃው ዘና ፈታ በሉ እያሉ. . .
ይህ ድንገቴ ፈጠራ /Improvisation/ የዋጠውን ስልት የወለደው - የአቀራረብ ልፋትን መሸሽ ነው፡፡ አንድን ጉዳይ ጥንቅቅ አድርጎ ለመስራት የሚጠይቀውን የንባብ፣ የምርምር፣ የዝግጅት፣ የኤዲቲንግ. . . ጣጣዎች በመፍራት የመጣ ነው፡፡ አቋራጭን ከመሻት የተዘየደ ነው፡፡
ለዚህ ማሳያ የሚሆኑንን ሁለቶች እንደምሳሌ እናንሳ
2. አሁንም ሁሉም ጣቢያዎች ላይ ሊባል በሚችል ሁኔታ የቀጥታ ስልክ ቃለመጠይቅ አለ፡፡ ይህም የዝግጅት ማነስን አብዝቶ የሚያሳይ ተግባር ነው፡፡
አስር አስራ አምስት ሰው ለሚታደምበት አነስተኛ መርሐግብር እንኳን ቀድሞ አለመዘጋጀት አግባብ አይደለም ብቻ ሳይሆን ፀያፍ ነው፡፡ እንኳንስ በእድሜ፣ በፆታ፣ በዕውቀት፣ በአኗኗር. . . ለተለያየ ማህበረሰብ የሚሰናዳን ቀርቶ፤
ያነሳነው ነጥብ አስተዛዝቦን ከማለፍ ባሻገር ከዳኛ ፊት የማስቆም አቅም አለው፡፡ አለማወቃችንን ተገን በማድረግ በርትተው ሲሳሳቱ - ሐይ ባይ ጠፍቶ እንጂ፤ ከሳሽ የለም እንጂ፤ ተከሳሽ በሽ ነው ያስብላል፡፡
በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1689 (1) እና (2) ላይ በተደነገገው መሰረት ከአቅም በላይ የሆነ ችግር እስካልገጠመው ድረስ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት በቃል ወይም በጽሁፍ የገባውን ቃል ማክበር እንዳለበት ይህ ባይሆን ግን ቅጣት እንደሚጠብቀው አስቀምጧል፡፡
እዚህ ጋር ስንቱ የውድድር አሸናፊ በሚድያ ቃል የተገባለትን ተከልክሏል? በአደባባይ የተገቡ የእርዳታ ቃልኪዳኖች ለማስታወቂያ ፍጆታነት ውለው ሲያበቁ በጓዳ ተሽረዋል? በተረጂዎች ስም ተነግዷል?
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ድርጅቶች ለአድማጭ ተመልካች በሽልማት መልክ እንዲቀርቡ የተበረከቱ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች፣ የኮንሰርት ቲኬቶች፣ የቲያትር መግቢያዎች፣ የፊልም ግብዣዎች. . . የስንቱን ኪስ አደልበዋል?
ይህንን ድርጊት በእምነት ማጉደል ወንጀል የሚከስ ቢኖር በፍ/ሕ/ቁ 675 መሠረት እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እስራት ወይም በ5 ዓመት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡
እንደ ነገሩ ሁኔታ ታይቶ ከ 5 ዓመት በማያንስ እስራት እና ከ 100ሺ ብር በማይበልጥ ገንዘብ የሚያስቀጣው እና በሚድያዎች ተደጋግሞ የሚሰራው ስህተት ደግሞ በህግ የማይፈቀድ ወይም የተከለከለን ድርጊት እንደፈጸሙ መናገር ነው፡፡
‹‹ እንደማንኛውም ራስታ ሐሽሽ እንደምወስድ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው ››
የሚል እና
‹‹ ሆኜ ለመስራት ስላሰብኩ የእውነት ሀሽሽ ወስጄ ነው የተወንኩት ›› የሚሉ ደፋር ተጠያቂዎችን /interviewee/ በቴሌቪዝናችን መስኮት ተመልክተናል፡፡
እንኳን መጠቀም ቀርቶ ይዞ መገኘት ወንጀል በሆነባት ሀገር ብዙሐን በሚከታተሉት ኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ማስተላለፍ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ልብ ይሏል፡፡ ታዳጊ ተመልካቾች፣ ወጣት ታዳሚዎች ምን ይማሩበት ይሆን?
‹ፌስታሌን› የተባለው የአንድ ሰው ተውኔት ገፀ-ባህሪ እያዩ ፈንገስ እንዲህ አለ ‹‹ በቀደም ለታ በሬዲዮ ሁለት ጎረምሶች ሲያወሩ . . . . . . /ይቅርታ ጋዜጠኛ ማለት ስለቸገረኝ ነው/ ››
በእብደት የተከለለው እያዩ ፈንገስ ሐቂቃውን በቀልድ አዋዝቆ ተናግሮታል፡፡ እነዚህን ጋዜጠኛ ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ጋዜጠኛ የተጠያቂውን እና የማህበረሰቡን ደህንነት በጠበቀ መልኩ መረጃውን እንዴት ማስተላለፍ እንዳለበት ካላስተዋለ ምኑን ጋዜጠኛ ሆነው? ይህ የሚድያ ሀ ሁ አይደለምን? ያስብላል፡፡
ሌላው ከሳሽ ፈላጊ ደግሞ እነሆላችሁ፡- ለህብረተሰብ ጥቅም የሚሰጥ ካልሆነ በስተቀር የማንኛውንም ሰው ምስል፣ ተንቀሳቃሽ ምስል፣ ድምጽ የባለቤቱን ፈቃድ ሳይጠይቁ ለማንኛውም ተግባር ማዋል፣ በሚድያ ማስተላለፍ ወንጀል ነው፡፡
ድንገቴ የስልክ ጥሪ /Surprise call/፣ የማቄል ጨዋታ /Prank/ እና ሌሎችም መሠል ባህሪ ያላቸው የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በዚህ ምድብ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በፍ/ሕ/ቁ 28 (2) መሠረት የቅጣት እርከን የወጣለት የጥፋት ተግባር ነው፡፡
እነዚህ እና እነዚህን የመሰሉ ሌሎችን ችሎት የሚገትር ቢኖር ማን ይተርፋል?
ስህተትን እንደጌጥ በማየት ባለመቻላቸው - በአደባባይ የሚሳለቁትን /በተለይ በቋንቋ እና በቃላት/፤ በመረጃና በመዝናኛ ሽፋን ሐሜትና ፕሮፖጋንዳ የሚነዙትን፤ በመነገሩ እና ባለመነገሩ መሐከል ያለው ልዩነት ለ ዜሮ የተጠጋ ጉዳይ መረጃ በማለት የሚግቱንን፤ የግለሰቦችን የግል ምስጢርና የውስጥ ገመና ለአደባባይ ያዋሉትን፤ ባልሰለጠኑበት ፈቃድ ባላወጡበት፣ ከተገቢው አካል የእውቅና ይሁንታ ባለገኙበት ሙያ ይፋ የምክር አገልግሎት የሚሰጡትን፤
ወዘተ ወዘተ ወዘተ ከሳሽ ቢያገኙ በርከት ያለ ቁጥር የላቸውም?
የዚህን ሁሉ ተከሳሽ ዝርዝር ስተነትን የት ቦታ እንደሰማሁዋት የተዘነጋችኝ ምልልስ ትዝ አለችኝ፡፡ ምናልባት ቲያትር ላይ ሊሆን ይችላል፡፡
አንዱ ተናጋሪ አንዲህ ይላል፡- ‹‹ ተወው በቃ ይህንን ለእግዚአብሔር መስጠት ነው ››
ሁለተኛው ሰው ቀበል አድርጎ ‹‹ ስንቱን ለእሱ ሰጥተን እንችላለን? ይችን ይችን የምንችላትን ቀላል ቀላሏን እንኳን እናግዘው እንጂ . . .››
እኛም እንግዲህ ብለን ወጋችንን እንደምድም፤ ስንቱን ለከሳሽ አሳልፈን እንሰጣለን? አንዳንዱን እንዳላየ ማለፍ፤ አንዳንዱን ህሊናው እንዲከሰው መመኘት ግፋ ካለም መጸለይ . . .
©''ዘመን እና ጥበብ'' መፅሔት
መስከረም 2009 ላይ የወጣ
No comments:
Post a Comment