Monday, May 15, 2017

ቴዲ አፍሮ - ከ’አቡጊዳ’ እስከ ‘ኢትዮጵያ’


1993 . ለህዝብ በቀረበው ‹‹አቡጊዳ›› በተሰኘ አልበሙ የሙዚቃ አድማጭን ቀልብ ለመግዛት በቅቷል፡፡ ‹‹ያስተሰርያል›› ‹‹ጥቁር ሰው›› ‹‹ኢትዮጵያ››  የተሰኙ ወጥ የአልበም ስራዎችን እስካሁን አበርክቷል፡፡ ስለ ስራዎቹ ሲጠየቅ በዝርዝሩ ውስጥ የማያካትተው ስራም አለው፡፡ ‹‹ቴዲ›› ይሰኛል የአልበሙ መጠሪያ - አቦጊዳ ከተሰኘው አልበሙ በፊት ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር የተሠራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሚሊንየም አካባቢ የወጣው አልበሙ 2 አዳዲስ ሥራዎችን እና ከመድረክ የተቀዱ ነባር ስራዎችን አካቶ ለገበያ የቀረበ ሥራው ነው፡፡ ተሰብስበው ቢጠረዙ ከአንድ አልበም የሚተርፉ ነጠላ ዜማዎችንም በተለያየ ጊዜ አበርክቷል፡፡ 

 
በእያንዳንዱ አልበም ውስጥ 10 እስከ 14 የሚደርሱ ዘፈኖች ተካተዋል፡፡ በዚህ ስሌት ከድምፃዊ ሸዋንዳኝ ጋር ከሠራው ሙሉ አልበም እና ከኩኩ ሰብስቤ ጋር የሠራውን ነጠላ ዜማ ሳይጨምር 60 በላይ ዘፈኖችን ተጫውቷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አቡጊዳ ላይ ከተካተቱት ‹‹እንደ ቢራቢሮ›› እና ‹‹ዓይኔ ሁልጊዜ›› በስተቀር ሁሉም ዜማና ግጥሞች በድምፃዊው የተደረሱ ናቸው፡፡
  
ዘፈኖቹ ከሚያጠነጥኑበት ርዕሰ-ጉዳይ አንፃር መድበን ለማየት ብንሞክር፡- ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚያነሱ፣ በጾታዊ ፍቅር ላይ ያተኮሩ፣ የቀደምት መሪዎችን ገድል የሚያወሱ፣ ታሪክ የሰሩ ባለታሪኮችን የሚያወድሱ፣ ፍቅርና አንድነትን የሚሰብኩ . . . በሚሉ መደቦች ውስጥ ፈርጀን ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡ በያንዳንዱ አልበም ውስጥ ዝርዝሮቹን አሟልቶ ይቀርባል፡፡ በተለይ ከአቡጊዳ በኋላ፡፡ቴዲየተሰኘውን አልበም የሚረሳውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ አዲስ የሙዚቃ አስተሳሰብ ከማምጣቱ በፊት የተወለደች በመሆኗ፤ ይህ ተግባር በቴዲ ብቻ የሚታይ አይደለም፡፡ ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህም ስራዎቹን ሲቆጥር ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር የጌትነትን ግጥሞች በፒያኖ አጅቦ የሰራውን ምርጥ የበኩር ስራመለያ ቀለሜ የኔ ብሎ መጥራት ሲቸገር አስተውያለሁ፡፡   
በአቡጊዳ እና እሱን ተከትለው በወጡት አልበሞቹ አንድ ተሞጋሽ መሪ አያጣም፡፡ ኀይለሥላሴ፣  ምኒሊክ፣ አሁን ደግሞ ቴዎድሮስ፡፡ ሌሎቹንም መደቦች /Categories/ ይሆነኝ ብሎ እንደሚጨምር ያስታውቃል፡፡ በአንድ ወቅት በሰጠው የራዲዮ መጠይቅ ላይ በአንድ ዓይነት ስልት ብቻ መዝፈንን አስመልክቶ፡-  
 
‹‹አንዳንድ ሰው ቀይ ወጥ ብቻ ይወዳል፣ ሌላው ደግሞ ሽሮ ብቻ ሊወድ ይችላል፡፡ እኔ ደግሞ ማህበራዊ ስለምወድ ማንበራዊ አደረኩት›› ብሏል ልከኛ ምላሽ ይመስለኛል፡፡ የሐሳቡም ጉዳይ እንደዛ ነው፡፡ በተአምረኛ ውብ ገለጻው /Expression/ ተጠቅሞ የሀሳብ መዘርዝር ያቀርብልናል፡፡ በርካታ ሰዎች እንደሚስማሙበት ከድምፃዊነቱ በላይ ገጣሚነቱ ይጎላል፡፡
 
ሙዚቃ ከባድ ሃይል ያለው የኪነጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ የስሜትን ግለት ለማናር፣ የምክኒያታዊነትን ድንበር ለመጣስ፣ . . .የሚያስችል ጉልበት አለው፡፡ መንፈሳዊ - አለማዊ፤ በመሳሪያ የታጀበ - ያልታጀበ፤ ግጥም የለበሰ ያልለበሰ፤ . . . እያልን በርካታ ክፍልፋዮችን በመስጠት በዘርፍ በዘርፉ ልንመድበው ይቻለናል፡፡ ክፍልፋዩም በውስጡ ሌሎች ክፍልፋዮችን ያቀፈና ባለ ብዙ ቀለም ነው፡፡
አሁን እያወጋንለት ስለምንገኘው ፖፕ ሙዚቃ ብቻ እንኳን ዜማ፣ ቅንብር /Arrangement/ ማዋሐድ /Mixing/ ግጥም፣ የመሳሪያ አጨዋወት . . . እያልን በመሰንጠቅ የእያንዳንዱን ውበት ልናደንቅ፤ የእያንዳንዱን ጉድለት ልንነቅፍ፤ እንችላለን፡፡
 
ኪነ-ጥበባዊ ወጎችን ስንከትብ ከዚህ ቀደም እንዳደረግነው ሁሉ ሰበዝ እንመዛለን፡፡ ስፋቱን ለማጥበብ፣ ጥልቀቱን ለመመጠን ይረዳን ዘንድ ግጥም ላይ አርፈናል፡፡ የቴዲ አፍሮ የዘፈን ግሞች ላይ 

ረጅሙን መግቢያ አጠናቀን ለዛሬ ወደወጠንነው ጉዳይ የሚወስደን በር ላይ እንገኛለን፡፡ ቴዎድሮስ ከአቡጊዳ እስከ ኢትዮጵያ አልበሙ ድረስ በግጥሞቹ ያነሳውን በጎ ፋይዳ በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡
አቡጊዳ
ከአቡጊዳ አልበም አቡጊዳ የተሰኘውን ዘፈን እናንሳ- የዚህ ዘፈን ዓላማ ማስቆጠር ቢሆን 1, 2, 3 ሊል ይችል ነበር፡፡ የዚህ የዘፈን ግጥም ግብ መማርን ማሳወቅ ቢሆን A B C D ማለት ይቻል ነበር፡፡ ፍቅርን ከማንነት ጋር ሊገምደው ፈልጓልና፤ ማንነትን የራስን ከማክበር ጋር ሊያስተሳስረው ሽቷልና
አቡጊዳ ብዬ ፊደላት ቆጥሬ
የፍቅርን ትርጉም ለልቤ አስተምሬ
አለ፡፡ ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ ነውና ተረቱም ይዤሽ ባቆፋዳ ብሎ ይቀጥላል፡፡ 
ይዤሽ ባቆፋዳ እንደቆሎ ተማሪ
አቡጊዳ ልበል የፍቅር ጀማሪ
ይዤሽ በቦርሳዬን ማን ከልክሎት አቆፋዳን መረጠ? ግዕዝን፣ አቡጊዳን፣ ከፍቅር ትምህርት ጋር በምን ስሌት አቆራኘ? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ የዘፈኑ ወጥዋጭ ሁላችንም ከላይ የምናየውን እና የምንታለልበትን ሰም አስቀመጠ፡፡ በውበት አበጅቶ ሲያበቃ ለትርጉም ክፍት አድርጎ ተዋት፡፡ በቆሎ ተማሪ መንገድ ባይጓዝም በማንነት መስመር ላይ አግኝቶታልና ተጠቀመበት፡፡ በጥበብ እና በውበት ከሽኖ አቀረበው፡፡
ከየኔታ ከመምህሩ
አቦጊዳን ሲያስተምሩ
ማልዳ አውጥታኝ ከፌደል ጣት
እንዴት ሊረሳት
አቡጊዳ ለአልበሙ መጠሪያነት ሲመረጥ የቃላቱ ማማር ብቻ አልታየም፡፡ የግጥሙ ውበት፣ የዜማው ስምረት፣ ብቻ ከግምት አልገባም፡፡ ወደራስ የመመልከትን፣ ከማንነት የመጋባትን ትርጉም ይሰጥ ዘንድ እንጂ
ይህንኑ ግብረመልስ /Reflection/ በሌሎቹም አቡጊዳ ላይ በተካተቱ ዘፈኖች ውስጥ በገደምዳሜ እናገኘዋለን፡፡ ኃይለሥላሴን ሲያነሳ እና ሐይሌ ገብረስላሴን ሲያሞግስ ወደራስ ማየትን፣ ወደውስጥ መመልከትን፣ አጥብቆ እየሰበከ ነው፡፡ የራስን ጀግና የማወደስ . . .
ለማን ልማሽ እኔ አንቺ ፍቅሬ
ብዙ ነው ሚስጥሬ
ቢከፋኝም ሆዴን ቢብሰው
አላማሽም ለሰው
ጎዶሎ ቢኖርሽም፣ ልክ አለመሆን ክልል ውስጥ ብትሆኚም፤ የኔ ነሽና ገመናሽን አሳልፌ አልሠጥም፡፡ የሚል መንፈስን ያዘለ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ ካነሳነው የማንነት ፍለጋ ጋር ዘወርዋራ ተዛምዶ አለው፡፡ የራስን ከነ እንከኑ መቀበል እንጂ ጉድፍን አደባባይ አለማስጣት፤
የኤልያስ መልካ የመጀመሪያ የቅንብር አሻራዎች ያረፉበት ውብ ግጥም፣ ግሩም ዜማ፣ ከድንቅ ቅንብር ጋር ያዋሐደ ሸጋ አልበም ነው፡፡ እነባይገርምሽእነሞናሊዛእነልጅነት አላት› . . . የተካተቱበት
 
ያስተሰርያል
 
የአልበም መጠሪያውን ተጠንቅቆ እንደሚመርጥ ያሳያል፡፡ የአልበሙ መጠሪያዎች በሙሉ በህዝብ ተወደውለታል፡፡ ይህ ሁልጊዜ አይሰምርም፡፡ የግጥም መፅሀፍ ወይም የአልበም መጠሪያ ሆነው በደራሲያኑ የሚመረጡት ሥራዎች በህዝብ ተቀባይነት ውስጥ ለመጠሪያ የማይበቁ ይሆናሉ፡፡ ያኔ የደራሲው አንደኛ እና የተደራሲው አንደኛ ይለያያሉ፡፡ ቴዲ ግን ይህ እስካሁን አልገጠመውም፡፡ ‹‹አቡጊዳ›› ‹‹ያስረሰርያል›› ‹‹ኢትዮጵያ›› . . .
ይህ አልበም በግጥሞቹ በኩል ያዘለው መንፈስ ልመና ነው፡፡ ወደላይ ማንጋጠጥ፣ ከአምላክ ጋር ያለን ግንኙነት ማጠንከር
ማለት ፈጣሪ መሠረይ ይቅርታ
እኛ ስንዋደድ ይሰማሻል ጌታ /ያስተሰርያል/
 በአንድ ዘፈን ውስጥ የአንድ ቃል ትርጓሜ የዘፈኑ አካል ሆኖ ሲካተት የመስማት እድል በቴዎድሮስ ዘፈኖች ብቻ ያስተዋልነው ሀቅ ነው፡፡ ማለት ፈጣሪ!› በኢትዮጵያ አልበሙ ላይምኦላ የሚለው ዘፈን ላይ ‹’መገኖካልን ጌታይላል፡፡ ሳይጎረብጠን ምንነቱን ያሳውቀናል፡፡ ወደ ምሳሌአችን እንመለስ
እኔም ልማል ባላህ አንቺም በቁልቢ
ክርሽን ሳትፈቺው በይ ከቤቴ ግቢ
ካልወጣሁ ካስርቱ ሰፂፈቱ ሲታ
አንቺን በመውደዴ አይቆጣም ጌታ /ሼመንደፈር/

ላይ ሳይ አይኔን አንስቼ ወዳለህበት
ጭንቄን ብትሰማኝ ተው ምናለበት
የፈጠርካትን ያዳም መከታ
የናቴን ምትክ ተው ስጠኝ ጌታ /ላይ ሳይ(በል ስጠኝ)/
ሰላም ይጠየቃል፣ እርቅ ይጠየቃል፣ ፍቅር ይጠየቃል፣ የትዳር አጋር ይጠየቃል፣ ፍትህ ይጠየቃል፡፡ በርግጥም አልበሙ የወጣበት ዘመንም የጥያቄ ነበር . . .
 
ጥቁር ሰው
ትላንት ምናባቱ አለፈ አከተመ፡፡ የፊቱን ብቻ ነው እንጂ ማየት ለሚሉ ተከራካሪዎች እንዲህ የሚል ምላሽ በመስጠት ይጀምራል፡፡ ለመዘጋት አደጋ ላይ ያለ የታሪክ ዲፓርትመንት ያላት ሐገር፣ የካቲት 12 ምን እንደተደረገ የማያውቅ የየካቲት 12 /ቤት ተማሪ ያላት ሐገር መኖሯ የቆጨው ይመስል
የትጋ እንደሆን ይታይ የኛ ፍቅር መሠረቱ
የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ
ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ
ሰው አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ
ትውልዱ ሐሞት የለውም፣ አቋራጭ መንገድን እንጂ ትክለኛውን የጥበብ፣ የህይወት፣ የፍቅር መንገድ ስቷል ተብለናል፡፡ እንኳን ታላቆቻችን እኛም ራሳችን በኛ ጉዳይ አንስማማም፡፡ እነሆ በዜማ የተቀመረ መድሐኒት
ዳገቱ ላይ አትዛል ጉልበቴ
የተራራው ጫፍ ፍቅር ናት ርስቴ
ቀላል ይሆናል ቀና አድርገኝ ጽናቴ
 የተራራውን ጫፍ አስብ፣ የስኬትህን መዳረሻ አልም፣ በውጤቱ ስትረካ የጉልበትህን መዛል ትዘነጋለህ፡፡ ከባድ መስሎ የታየህ ሁሉ በቁጥጥርህ ስር ይውላል፡፡ በጎ እሳቤን ያዘለ አበረታች ዕፅ፡፡ በጆሮ የሚገባ ቅመም መልእክት 
 
ኢትዮጵያ
እንደተለመደው ኢትዮጵያ አልበም ላይም የመጣበትን ስልት ጠብቆ መጥቷል፡፡ አስቀድሞ በነጠላ ዜማ መልክ የተደመጡ 2 ዜማዎችን እና ጥቁር ሰው አልበሙ በወጣበት ሰሞንወደ ፍቅር . . .› ሲል ለሰየመው ኮንሰርት ማድመቂያነት የተጠቀመበትንኦላ ጨምሮ 14 ዘፈኖችን ያካተተ አልበም ነው፡፡
ከመሳሪያ በፊት ድምፁን አስገብቶ መሳሪያው እንዲከተለው የሚያደርግበት ስልት አለ፡፡ ታላላቅ መሪዎችን ማወደሱም አልረሳም፡፡ ታሪክ ሰሪዎችን መዘከሩም ወደ ምናባዊ ሰዎቻችን ሳይቀር ዘልቋል፡፡ፍቅር እስከመቃብርየተሰኘው ዘመን አይሽሬ ልብወለድ መጽሐፍማር እስከ ጧፍበተሰኘው ዘፈን ምንክያት ሽያጩ መጨመሩን ስንሰማ ደስ ብሎናል፡፡ ተፅእኖ የመፍጠር አቅሙን እንዲህ ላለ ተግባር ማዋሉም እጅግ ሊደነቅለት የሚገባ ነው፡፡ ጸጋዬ ገብረመድህንን ያነሳበት ስራው ከዚህ ምድብ ጋር አብሮ የምስጋና ድርሻውን የሚጋራ ሥራው ነው፡፡
ባልፍም ኖሬ
ስለናት ክብሬ
እኔስ ሀገሬ
እስካሁን ባየናቸው አልበሞች ላይ የገነባነውን መመንዘር ልንጀምር ነው፡፡ ዓመትም ባልኖር፣ ኖሬም ባልፍ፣ ምንም ብሆን ምንም እኔ የሀገሬ ነኝ፡፡ እኔ የእኔ ነኝ፡፡ በአቡጊዳ አልበም ያየነው የማንነት ስብከት ነው፡፡ 3 ስንኝ በቡሄ በሉ ቤት አጥሮ ሲመጣ፤
ስንት የሞቱልሽ በስምሽ ዘብ አድረው
አልፈው ሲነኩሽ ባህርሽን ተሻግረው
የጀግኖች ሀገር የደም እግር አሻራ
ፈለገ ጊዮን ያንቺ ስም ሲጠራ
መመንዘራችንን ቀጥለናል፡፡  ራሱ አርቲስቱ ከመዓዛ ብሩ ጋር በሸገር ራዲዮ በነበረው ቆይታ ሁሉም ዘፈኖች በቀጥታ የኔ የህይወት ግልባጭ ባይሆኑም እኔን ግን ይመስላሉ ብሏልና እናመሳስላለን፡፡
ነገስታቱን ባነሳበት ዘፈን ላይ ያወደሳቸው የኢትዮጵያ ባለውለታ ጀግኖች፡፡ ደም የከፈሉላት ባለውለታዎች 4 መስመር ስንኝ ተቀንብበው መጡ፡፡
ቴዎድሮስን፣ ምኒሊክን፣ ሐይለስላሴን የወጉት ባህር ተሻግሮ መጪዎች፤ በባልቻ የተተካው ለሀገሩ ሟች ገበየሁ፤ የመቅደላ፣ የአድዋ፣ የማይጨው ደም ያስከፈለ የሀገር ክብር፤ የአልገዛም እምቢ ባይነት ለፈለገ ጊዮን ነው፡፡ 
እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ
ስምሽ ሲጠራ ማን ዝም ይላል ሰምቶ
ከብሄር፣ ከሀይማኖት፣ ከአብሮ መብላት፣ ከመልከአ ምድር፣ ከቅርስ፣ ከዜማ - ከቅኔ፣ ከአምልኮ ስፍራዎች ዝርዝር . . . ያልተነካካ ምርጥ ዘፈን፡፡ ኢትዮጵያን ብቻ እንድናስብ የሚያስገድድ የስካሁኖቹ ጭማቂ መረቅ ኢትዮጵያ፡፡
እንኳን ሰማይ ላይ አለ እንጂ እንኳን ሸንደቅ ላይ አላለም፡፡ ከአምላክ ጋር ያለን የጠነከረ ትስስር ያሳይለት ዘንድ ቀስተደመናውን መረጠ
ወደራስ መመለስ + ከአምላክ መታረቅ + ኋለኞችን ማክበር  = ኢትዮጵያ
 
ምን እንጠብቅ?
 
በወዳጆቹብልቴናው የለውጥ ሐዋርያወዘተ በመባል የሚሞካሸው ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲ እና ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት መካድ አይቻልም፡፡ አሳምኖ ተከታዩ ያደረጋቸው በርካታ ናቸው፡፡

 
ኢትዮጵያ አልበሙ በወጣ ጊዜ የሱን ሲዲ አለመግዛት ክልክል እስኪመስል ድረስ በብዙዎች እጅ ላይ ነበር፡፡ ይህንን ትዕንትፍሬሽማንቲያትር ክፍል ሁለት ለእያታ በበቃበት ጊዜ ታዝበናል፡፡ የበእውቀቱ ስዩምከአሜን ባሻገርበወጣበት እለትም ለመታዘብ ታድለናል፡፡ ኢትዮጵያ አልበም ያህል ትርምስ ግን ምናልባት የመጀመሪያችን ሳይሆን አይቀርም፡፡ የሱን አለማድመጥ ነውር እስኪመስል በበርካታ የድምፅ ማጉያዎች እና የሲዲ ማጫወቻዎች ላይ ነበር፡፡ ታክሲው፣ ካፌው፣ ሱቁ ሁሉም እሱላይ ነበር፡፡ ይህንን በጎ እድል በመጠቀም የሙዚቃውን ደረጃ ከፍ እንዲያደርግ እንጠብቃለን፡፡ ከፍተኛ ተከፋይ ነውና ራሱንም ሙዚቃችንንም ዓለማቀፍ ደረጃ የሚያደርሱ ቅጂዎችን /Recording/ እንዲያከናውን እንጠብቃለን፡፡

 
ሆበል ማሲንቆ -ሆበል ክራሬእያለ የማሲንቆ ድምፅ ያልነካው ዘፈን መስራቱን፤ታምታራም ሳደርገው  ብቅበይ ክራሩንብሎ ክራር ያልጎላበት ቅንብር መስጠቱን፤ እንዲያርም እንጠብቃለን፡፡
ይዞት በመጣው ስልት /Stile/ ተጠቅሞ የበለጠ ሀገራዊ መግባባት የሚያመጡ ሰላም እና አንድነትን የሚሰብኩ ዝማሬዎችን እንናፍቃለን፡፡

እንደ  ‹ነፍሴ፣ እጅ እንዳትሰጪው ለኪሴእናበናፍቆትሽ እንባ እየራሰ አልጋዬ፣ ካላንቺ አቅቶኛል ማደር ለብቻዬ › ‹ሳሙኝ የሚል ከንፈር፣ ድንገት አጉል አርጎኝ ነበርዓይነት ከራሱ የገለጻ ችሎታ፣  የሀሳብ ጥልቀት እና የቋንቋ አቅም አንፃር የማይመጥኑ ስረዎቹን እንዲተው እንመኛለን፡፡ የተደጋገሙ የሚመስሉ ዜማዎቹን ጥሎ አዲስነታቸው ከውበታቸው እና ልዩነታቸው ጋር የሠመረ ዜማዎች እንዲያቀብለን እንጓጓለን፡፡


እንዲሁም ‹‹መንታ ወድጄ ካንድ ቤት ሁለት›› የመሠሉ አፍራሽ መልዕክቶችን ያዘሉ ሐሳቦችን የማናገኝበት አልበም እጠብቃለን፡፡
‹‹በቀን ባራተኛው በለተ ሐሙስ›› ‹‹ካፈሩ ላይ የሰራሐት ነፍሴ›› የመሳሰሉ ስህተቶችን አርሞ እንዲቀርብ፤
‹‹አበባአየህ ወይ›› የመሰሉ የትውፊት እና የትርጉም መጣረሶችን የሚስከትሉ ህፀፆችን እንዳይደግም እንሻለን፡፡ ሐሳቦችን መነሻ አድርጎ ሲሰራ ወይም የተሠሩትን አንስቶ ሲጠቀም በግልጽ እንዲነግረን እንወዳለን . . . ለሁሉም ኖረን ለመተያየት ያብቃን፡፡


© ዘመን እና ጥበብ መፅሔት ግንቦት 2009 . ላይ የወጣ

No comments:

Post a Comment