በዘመን
እና ጥበብ መጽሔታችን የሰኔ ወር እትም ‹ተወራራሽ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች› በሚል
ርዕስ ሥር መጨዋወታችን ይታወሳል፡፡
መነሻቸውን አስቀድሞ ለታዳሚ በደረሰ የኪነ- ጥበብ ውጤት ላይ ያደረጉ ሥራዎችን በወፍ በረር ቃኝተናል፡፡ ያነሱትን የጥበብ ውጤት፤
ቀድሞ የነበረውን እንደነበረ በሌላ የጥበብ ዘውግ፤ ወይም ነባሩን ይዘው በሌላ ዓዲስ የሀሳብ መንገድ የተገለፁትን ዘርዝረናል፡፡
በእግረመንገድ ያስተዋልነውን፣ በትውስታ ማህደራችን ቀድመው የተከሰቱልንን ብቻ አነሳስተናል፡፡
ወጋችንን ስናሳርግ ‹ፍቅር እስከ
መቃብር› የተሰኘው ረዥም ልብወለድ ላይ ተመስርተው የተሠሩትን ለማነሳሳት ቃል ገብተን ነበር፡፡ ቃል አክባሪ ሆነን የዛሬውን ዋና
ርዕሰጉዳይ ከመጀመራችን በፊት ግን ሳንጠቅስ ያስተረፍናቸውን እና በሰኔው እትም ያዛነፍናቸውን እውነታዎች እናክም፡፡ በዚያውም ሐምሌ
ጠብቁን ብለን ነሐሴ ላይ ስላመጣነው ክፍል2 ጽሁፍ እና ስለተፈጠረው ስህተት እኔ እና የመጽሔቱ አዘጋጆች የየድርሻችንን አንባቢዎቻችንን
ይቅርታ እንለምናለን፡፡
‹ኤልዛቤል› የተሰኘው የአዳም
ረታ አጭር ልብ ወለድ ከወረቀት ወደ ሸራ ከተገለበጡ ሥራዎች መሐል አንዱ ነው፡፡ አብርሀም ገዛኸኝ ወደ ስክሪን ካመጣው
ሎሚ ሽታ የተሰኘ የሙሉ ጊዜ ፊልም ጋር ሲደመር የአዳም ሁለት ስራዎች በብርሃን እና ቀለም ድጋሚ ተጽፈዋል፡፡ የሀሳብ ድርቅ እየተመላለሰ
ያጠቃውን የፊልም መንደራችንን እንዲያንሰራራ ለማድረግ ይህ ተግባር ዓይነተኛ መፍትሄ ይመስለኛል፡፡ የራሱ ጥንቃቄዎች መፈለጉ እንደተጠበቀ
ሆኖ . . . ‹‹ያንገት ጌጡ›› የተሰኘው የደራሲ ጊደሞፓሳ ልብወለድ ታሪክ በአውግቼው ተረፈ ወደ አማርኛ ተቀድቶ ተወዳጅነትን
ያገኘ ነው፡፡ ታሪኩ የዳይሬክተሮችን ቀልብ ስቦ ለቴሌቪዥን እይታነት ሲበቃ በሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል የፊልም ስራው ተከናውኗል፡፡
አስር ያህል ከሚሆኑት የእንዳለኔታ
ከበደ ሥራዎች መሐከል ‹ኬርሻዶ› በ ድምፃዊ ዓለሙ ታፈሰ እና ‹እምቢታ› በድምፃዊ መላኩ ቢረዳ አሰናጅነት መነሻቸውን መፃሕፍቱን
በማድረግ- ግጥም ሆነው፣ ዜማ ለብሰው፤ በቅንብር ተውበው - በጉራጊኛ ቋንቋ ተቀንቅነዋል፡፡
በንባብ ወለድ ዘፈኖቹ ማንም
የማይስተካከለው እንዳለ አድምቄ በክፍል አንድ ጨዋታችን ካነሳንለት በተጨማሪ የበዓሉ ግርማን ‹ኦሮማይ› ዘፍኖታል፡፡ በአንድ ቃለ
መጠይቁ፡- መጽሔት ላይ ወጥታ ባነበባት እና እጅግ ስሜቱን በነካችው ታሪክ መነሻነት ‹አልጋ ወራሿ› የተሰኘ ዜማና ግጥም መስራቱን
ሲናገር ተደምጧል፡፡ ያቺ ሥራ ‹ከጥቁር ሰማይ ስር› በተሰኘው የአጫጭር ልብወለዶች ስብስብ ውስጥ ያለችው ‹ምጣዱ› የተሰኘች ታሪክ
ናት፡፡ ደራሲው ደግሞ እንዳለኔታ ከበደ . . .
‹የሲሳይ ንጉሱ ‹ግርዶሽ› በፊልም
ተሰርቷል፡፡ ‹የከርሞ ሰው› የተሰኘው በሙላቱ አስታጥቄ የተቀናበረ የሰይፉ ዮሐንስ ዘፈን መነሻው የጸጋዬ ገብረመድህን ‹የከርሞ
ሰው› ቲያትር ነው፡፡ ሠይፉ ዮሐንስ ካቀነቀነው ግጥም የለበሰ ቅንብር በተጨማሪ አርቲስት ሙላቱ ወጥ የሙዚቃ ቅንብር ሰርቶለታል፡፡
ድምፃዊ ተሾመ አሰግድ ከጸጋዬ ገ/መድሕን ግጥማዊ ቲያትሮች መሐል አንዱን ዜማ አልብሶ በማቀንቀን ከዘፈኖች ዝርዝር ውስጥ ከቶታል፡፡
በባለፈው እትም ከጠቃቀስናቸው
ቴዎድሮስ ካሳሁን እና ጥላሁን ገሰሰ በተጨማሪ ልሳነ ወርቁ ድምፃዊ አሊ ብራ በኦሮምኛ ዘፈኖቹ ‹ሞናሊዛ› የተባለ ዘፈን አለው፡፡
አወዛጋቢዋን የዳቬንቺ የጥበብ ውጤት ለውበት ጥግ ማንጸሪያነት ተጠቅሞባታል፡፡
የተወዳጅ መፃኅፍት ህይወት በሌሎች
የጥበብ ስራዎች ላይ ብቻ ሳያበቃ በነባራዊው ዓለም ላይም ይንፀባረቃል፡፡ ታዋቂው ሐያሲ /ነፍስ ይማር/ አብደላ አህመድ ሳላህ
(አብደላ እዝራ/ እዝራ አብደላ) በአዳም ረታ ‹ማህሌት› የተሰኘ ልብወለድ አብዝቶ በመመሰጡ ልጁን ማህሌት ሲል ጠርቷታል፡፡ ጋዜጠኛ
ሰሎሜ የአንዱ ልጇ ሰም ስብሀት ነው፡፡ ለስብሐት ገ/እግዚአብሔር ሥራዎች ያደረባትን ፍቅር ለማሰብ ስትል ልጇን ስብሐት ብላዋለች፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ ታሪኮች
እየተመዘዘ በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ፤ በወቀሳም ሆነ በልመና . . . የተሠነዘሩ የኪነጥበብ ሥራዎች አሉ፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን
ይሁዳ ይመስለኛል፡፡ ስለ ይሁዳ በርካታ መነባንቦች ተመድርከዋል፡፡ ኤፍሬም ስዩም በ ‹ሶሊያና› የግጥም ሲዲው ‹ምን አለች እናትህ?›
ሲል ጠይቆ ግሩም ስንኞች ከትቧል፡፡ እንዳለጌታም በዙሪያው የሚያጠነጥን አጭር ልብወለድ አለው፡፡
ባህሩ ሰፊ ነው፡፡ የበረታ ለበለጠ
ጥናት እና ለሰፊ ትንታኔ ሊያበቃው ይችላል፡፡
ያነሳነው ነጥብ ዓዲስ መጤ አለመሆኑን
ለማሳየት ያህል፤ ዘለግ ላለ ጊዜ ከጥበብ ሥራው እና ሰራተኛው ዘንድ እንደከራረመ ለመንገር ያህል፤ እነማን በመንገዱ እንዳለፉ ለማስታወስ
ያህል... ያነሳናቸውን አነሳን፡፡ በስርአት ተሰድረው ማን? መቼ? ምን ሠራ? የሚሉ መረጃዎችን በቀላሉ በማናገኝበት ሁሉንም ዘርዝሮ
መጨረስ ቀላል አይደለምና እዚህ ላይ አንግታው፡፡
‹ፍቅር እስከ መቃብር› በበርካታ
የስነ-ጽሁፍ ሐያሲያን ዘንድ ዘመን አይሽሬ መሆኑ ተመስክሮለታል፡፡ በጥራቱ፣ በወጥነቱ እና በውበቱ የአንባቢን ብቻ ሳይሆን የምሁራኑን
ቀልብ እንደገዛ ኖሯል፡፡ ይኖራል፡፡ በርካታ ዘርፍ ያላቸው ጥናቶች በልዩ ልዩ ሙያተኞች ቀርበውበታል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ እና የሁለተኛ
ዲግሪ የጥናት ወረቀቶች ተሰርተውበታል፡፡ ‹ፍቅር እስከ መቃብር› የፊውዳሉን አገዛዝ መልክ እጅግ ኪናዊ በሆነ ለዛ ያስቀመጠ የምንጊዜም
ምርጥ ተብሎለታል፡፡
ደራሲው ሐዲስ ‹‹ያበሻ ወደኋላ
ጋብቻ››፣ ‹‹ተረት ተረት የመሰረት››፣ ‹‹ወንጀለኛው ዳኛ››፣ ‹‹የልም እዣት››፣ ‹‹ትዝታ››፣ ‹‹ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር
ያስፈልጋታል?›› የሚሉ መፃሕፍትን ያበረከቱ ሲሆን፤ በቅርቡ በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የመታሰቢያ ሐውልታቸው ሲመረቅ በሕይወት ካጣናቸው
ከ 14 ዓመታት በኋላ ‹‹ይድረስ ለወዳጆቼ›› የተሰኘ የግጥም መፅሐፍ አሳትሞላቸዋል፡፡
ከሐዲስ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን
በዘመኑ ከነበሩ ሌሎች አቻዎቻቸው ሳይቀር ጎልቶ የወጣው እና ከ1958ዓ.ም ጀምሮ ከ 20 ጊዜ በላይ ለመታተም የበቃው ፍቅር እስከ
መቃብር ነው፡፡
ፍቅር እስከመቃብር ለበርካታ
ዘመናት ተወዳጅነቱን ጠብቆ የመቆየቱን ያህል፤ በበርካታ የኪነጥበብ ውጤቶች ላይ በልዩ ልዩ መልክ ተነስቷል፡፡ በቲያትር፣ በልብወድ፣
በዘፈን ውስጥ የተለያዩ ባለሙያዎች እደየፍላጎታቸው ተጠቅመውበታል፡፡
ከልብወለድ እንጀምር፡-
‹መረቅ› በአዳም ረታ የተፃፈ
ረጅም ልብወለድ ነው፡፡ 600 ገፆች ያሉት መረቅ በ2007ዓ.ም ለንባብ በቅቷል፡፡ በበርካታ ሐያሲያን ጥልቅ ትንታኔ ተሰጥቶበታል፡፡
ዳሰሳዎች ተሰርተውበታል፡፡ በርካቶች የድህረ ዘመናዊነት /Post Modern/ መገለጫዎችን አብዝቶ እንደሚጠቀም እና በአማርኛ ስነ-ፅሁፍ
ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራውን እንዳስቀመጠ ቢስማሙም እሱ ግን እንዲህ ይላል፡፡
‹‹ የዚህ ልብወለድ አጨራረስ
ሁለት የተረክ ዘዬዎችን አጣምሮ ይይዛል፡፡ አንደኛው የትውፊት ተረክ ስልት ሲሆን ሁለተኛው ህጽናዊነት ነው፡፡ ›› መረቅ ገፅ
599 ላይ
በሌላ ወገን ደግሞ ማናቸውንም
የጥበብ ውጤቶችን በጎራ ለመክፈል፣ ዘውግ ለማበጀት እና ባህሪያቸውን ነጣጥሎ ለማጥናት የሚያግዘን የ‹ኢዝም› ክፍፍል (ሞደርኒዝም፣
ናቹራሊዝም. . .) ብቻ ነው፡፡ የሚሉ ምሁራንም አሉ፡፡
ያም ሆነ ይህ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ
የአጻፃፍ ይትባህሉ ባለመሆኑ ከስያሜው እና ዘዬው ባሻገር ያሉትን ነገሮች እንመልት
በመረቅ የመጀመሪያዎቹ የታሪክ
ክፍሎች ላይ የፍቅር እስከመቃብሯ ሰብለወንጌል በመረቅ ውስጥ ህይወት ትዘራለች፡፡ አያት ሆና ታሪኳ በዚህ መልኩ ለልጅ ልጇ ይተረካል፡፡
በአዳም ረታ መረቅ ውስጥ
‹‹ልጅ ብዙ ጊዜ እናቱን ወይም
አባቱን ነው የሚመስለው አያት ጋር ምን አስኬደ? አያትህ ሰብለ እርግብግብ ነበረች፡፡ ለትንሹ ነገር ‘የዲማው ያለህ’፣ ‘የዲማው
ድረስ’፣ . . . ምንስ ፈረሰኛ ቢሆን ከዲማ እዚህ ይቅር በለኝ . . .እንደው መመሳሰላችሁ የእግዜር ስራ ይመስለኛል፡፡ እናትህ
ሮዛን ሞጆ ነው የወለደቻት›› መረቅ ገፅ 30
በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ
ያልኖረቻቸውን ህይወቶች ያኖራታል፡፡ በአንድ ወቅት አዳም ወደፊት ‹‹ከሁሉም መጽሐፎቼ ውስጥ ያሉትን ገጸባህርያት አሰባስቤ ሌላ
አንድ ልብወለድ እሰራለሁ፡፡ የአንድ ገጸባህሪ ህይወት በአንድ መጽሐፍ ብቻ መገደብ የለበትም›› ሲል ተናግሯል፡፡ /ንግግሩ ቃል
በቃል የተወሰደ አይደለም፡፡/
አዳም ረታ ሰብለወንጌልን ወደ
ልብወለዱ ውስጥ ሲያመጣ በፍቅር እስከመቃብር ላይ የነበራትን የህይወት ክፍል ሙሉ በሙሉ አልደመሰሰውም፤ ወይም በሌላ የህይወት ክፍል
አልተካውም፡፡ የተቀበላቸውም አሉ፡፡
‹‹በእናትህ በኩል ቅድመ አያትህ
ፊታውራሪ መሸሻ የሚባሉ አጥንተ ጥሩ የጎጃም ሰው ነበሩ፡፡ ሰብለ ዲማ ነው እንግዲህ የተወለደችው፣ ለአቅመ ሔዋን የደረሰችውም እዚያ
ነው. . . አባቷ ባል ሲመርጡ መዳሪያ ጊዜዋ ተላለፋት . . . እና ፊደል የሚያስቆጥራትን በዛብህ የሚባል ጎረምሳ ዲያቆን ወደደች፡፡
ያኔ እንደዛሬ ማንም ከማንም አይጋባም ዘር አለ ምን አለ . . .አባቷ ከሚንቁት ሰው የመዋደዷ ወሬ ሲደርሳቸው ‘ይሔን ቅማላም
ካልገደልኩ’ ሰሉ ይሰማና በዛብህ በፍሱን ሊያድን ወደሸዋ ይሰደዳል፡፡ ቆየት ብሎ እሷ መሸሹን ስትሰማ ሳትውል ሳታድር … አስረዋት
አልነበር … ተእስር አምልጣ … እግሩን ተከትላ ወደ ሸዋ፡፡ ››
መረቅ ገፅ 31
በነበረው የታሪክ ሐዲድ ላይ
ሲጓዝ ይቆይና አጨራረሱን በራሱ መንገድ ይቀጥለዋል፡፡ በውጪው ዓለም
የአንድን ተወዳጅ ልብ ወለድ አጨራረስ ያልወደደው አንባቢ በሌላ የተለየ አጨራረስ ሊደመድመው እና ለአንባቢ ሊያደርሰው ይችላል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ውስጥ ያለፉ ሥራዎች እንዳሉ ሰምተናል፡፡ በኛም ሐገር ሌሊሳ ግርማ ‹የንፋስ ህልም› በሚሰኘው የአጫጭር ልብወለድ
ታሪኮች ስብስብ መጽሐፉ አንድን አጭር ልብወለድ በ 2 መንገድ ጨርሶት አሳይቶናል፡፡ ልብወለዱ ሲጠናቀቅ አማራጭ ማለቂያ በማለት
መጨረሻውን ይቀይረዋል፡፡
‹‹ ስለ አያትህ ስለ ሰብለ
ልቀጥልልህ፡፡ በዛብህ ሲሞት ‘ምን ቀረኝ ዲማ አልመለስም’ ብላ እሱን ደጀሰላም ቀብራ ነጋዴ ተከትላ አዲስ አበባ መጣች፡፡ አራዳው
ጊዎርጊስ ነው ያገኘኋት እንደ ነዳይ አፈር ላይ ተኝታ፡፡ ከግንባሯ፣ ቀን የጣላት እንደሆነች ማንም ይገባዋል፡፡ ቤቴ ወሰድኳት፡፡
እኔ ምን ነበረኝ ያኔ? ምንም፡፡ ሴት ነኝ የሁለታችንን ሆድ መሙላት አልችል፡፡
አገሩን ስትለምድ ‘በይ ተነሽ
አሁን’ አልኩና ብዙ ሳትቆይ ብቻ ከተማውን ለምዳለች ነጋዴ አደረኳት፡፡ ቅጠላቅጠል፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ዱባና ቅል እሸጥ ነበር፡፡
አብረን መነገድ ጀመርን ›› መረቅ ገፅ 32
ሳርኪን ከተባለ አርመን አልአዛር
የሚሰኝ ልጅ የምትወልደው የፍቅር እስከመቃብሯ ሰብለወንጌል በመረቅ ውስጥ የህይወቷ የመጨረሻ ክፍል እንዲህ ይተረካል፡፡
‹‹በዚህ በዚህ በመሳሰለው ተዳከመችና
የኔ እመቤት ታመመች፡፡ በሽታዋ ምን እንደሆነ ሐኪሙም አያውቅ፡፡ አልጋ ላይ ብዙ አልቆየችም ያውም፡፡ ሞተችብኝ . . . ለኔ ቀረችብኝ
እንጂ እሷማ ተዝጌር ጋር ናት፡፡ እንደተወለደች ነው የተመለሰችው ወደርሱ ወደፈጣሪ፡፡ ወደደች አዘነች፡፡ ወደደች ወለደች፡፡ ጎጃሜም
ሆነ አርመን፡፡›› መረቅ ገፅ 37
እንዲህ እንዲህ እያለ የሰብለን
የልጅ ልጅ ታሪክ በመረክ ውስጥ ይፈሳል፡፡ የአዳም ረታ መረቅ . . . እንደ እህት የምታያት የታሪኳ ነጋሪ የደም ትስስር የላትም፡፡
የኛ የሐበሾች ኑሮ ከደም ዘምድና በላይ የሰብአዊነት ትስስር ይጎላብናል ለማለት ፈልጎ ይሆን አዳም?
‹ወሪሳ› 40 ምዕራፎች እና
‹የወሪሳ ምሽቶች›፤ ‹የእሪበከንቱ ውድቅቶች› በሚሉ 2 ክፍሎች ተጠርዞ በ240 ገፆች የቀረበው ‹‹ወሪሳ (የውድቅት ፈለጎች)››
ከዓለማየሁ ገላጋይ 10 ስራዎች መሐል 9ኛው ነው፡፡
እንደ ቴዎድሮስ አጥላው አገላለጽ
(የስነ-ፅሁፍ ተመራማሪ) ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ የጦማራዊ /Epistolary/ አፃፃፍ ስልትን ከተለምዷዊው ጋር በማዋሀድ የሚጠቀም
እና በበርካታ ደራሲዎቻችን በማይደፈር መልኩ /Experimental novelist/ ነው፡፡ ብሎታል፡፡ ወሪሳን ጨምሮ በቅበላ እና
በብርሐን ፈለጎች ውስጥም እንደ ዲበ ልቦለዳዊነት /Meta-Fiction/ እና ቅንጥብጥብ /Parody/ ያሉ የድህረ ዘመናዊነት
/Post Modern/ ቀለሞችን ተጠቅሟል፡፡
ወሪሳ ስለተባለች በእሪ በከንቱ
የምትዋሰን ምናባዊ መንደር ክራሞት የሚተርከው ልቦለዱ ‹‹እንደ ኢየሱስ በወንበዴዎች መካከል ተቸንክሬአለሁ›› ብሎ ይጀምራል፡፡
በሳቅ ጫሪ እና አመራማሪ ገፀባህርያቱ እያባበለ ወደፊት ያስጉዘናል፡፡
‹‹ፍቅሮ እስከ ቅብሮ
.
.
ቋንቋዋም ተስተካክሎብኝ፡፡ ትወናዋ
አበቃ ይሆን? ‹‹ርዕሱ አልገባኝም አልኳት››
‹‹ ‘ፍቅሮ’ ማለት ፍቅር ማለት
ነው፡፡››
‹‹እሺ››
‹‹ ‘እስከ’ ያው እስከ ነው››
‹‹እሺ››
‹‹ ’ቅብሮ’ ደግሞ መቃብር
ነው፡፡››
‹‹እንዴ? ፍቅር እስከ መቃብር?››
‹‹አዎ›› ጅኑን አንስታ ተጎነጨች፡፡
‹‹ይሔማ የጥበብ ስርቆሽ ነው፡፡››
ዘወር ብላ ገረመመችኝ፡፡ የመታዘብም የመናደድም አይደለም፡፡ ታዲያ የምን? ‹‹ታሪኩ ምን ላይ ነው ማለቴ በርዕሱ ብቻ . .
.››
‹‹ታሪኩ ወሪሳ እና እሪበር
ላይ ነው፡፡ አንድ ወሪሳዊ ሀይለኛ የሪ በር ልጅ አፍቅሮ የቺኳ (የሴቷ) አባት መሬ (ሀይለኛ) ናቸው፡፡ እና ወሪሳዊውን እመርሸዋለሁ
(እገድለዋለሁ) ሲሉ ተሸብልሎባቸው ወሪሳ ይመጣል፡፡ ልጃቸውን ያስሯታል፡፡ ወሪሳዊው ቢጠብቅ ቢጠብቅ ቺኳ አልከሰት (አልመጣ) ስትለው
ወደ እሪበር ለመሄድ ይቆርጣል፡፡ በመጀመሪያ ግን በሞባይል ሜሴጅ ልኮላት ነበር፡፡ ቺኳ ትጨነቅና ወደ ወሪሳ ስትመጣ እሪበከንቱ
ወንዝ ማጁካዎች (ማጅራት መቺዎች) ሀንግ ሰርተውት (ማጅራት መተውት) ወድቆ ታገኘዋለች፡፡ እዛው እጇ ላይ ይሞታል፡፡ ከዚያ በኋላ
ቺኳ ወደ አረብ ሐገር ትሔዳለች፡፡ እዛ ሞታ አስከሬኗ ሲመጣ በተናዘዘችው መሠረት ከፎንቃዋ (ከፍቅረኛዋ) ጋር አንድ መቃብር ላይ
ትቀበራለች፡፡ በቃ፡፡››
የምለው ጠፋኝ
‹‹ሜሴጅ ምን ብሎ ቢልክላት
ጥሩ ነው?››
‹‹እ?››
‹‹ስሟ ቤቲ ነው››
‹‹እሺ››
‹‹በግጥም ነው ሜሴጁ››
‹‹ቀጥይ››
‹‹ቤቲ፣ ቤቲ፣ ቤቲ ጀለሴ እመቤቴ
ከሚጨሰው ጫሽ ነሽ ከቃሚው ቀማቴ
ፋክት ከሆነማ እኔ አንቺን ማጣቴ
ምን ዋጋ ሊኖረው ያ-አራድነቴ
መንጩ ሰሩኝ ወይኔ - ወሪሳ
መሆኔ››
‹‹ፍቅር እስከ መቃብር የተሰኘውን
ልብወለድ አንብበሽዋል?›› ስል ጠየኳት
‹‹አዎ ምነው?››
‹‹ምንም፣ ጨርሰሽዋል?››
‹‹አዎ፣ ምነው?››
‹‹ምንም››
ከዚህ በላይ ምን ይወራል? ዝም
ብዬ ትኩረቴን ጅኑ ላይ አደረኩ፡፡ ›› ወሪሳ ገፅ 79-80
እያለ ይቀጥላል ልብወለዱ፤ ቀደም
ሲል ከተመለከትነው የአዳም ረታ ስራ ጋር የሚለየው ‹ፍቅር እስከ መቃብር› ልብወለድ መሆኑን ባለመካዱ ነው፡፡ ዋናው ገጸ ባህሪ
እኛን ሆኖ ይሟገታል፡፡ ከአንባቢያኑ ጋር በመሆን የምናውቀውን ታሪክ
አዲስ ትላለች እንዴ? ይላል፡፡
ዓለማየሁ በወሪሳ ድርሰቱ ላይ
ለምናባዊ ትረካው እስከተመቸው ድረስ የትኛውንም እውነተኛ ወይም የፈጠራ ሰው በማስገባት የተረኩ ማጣፈጫ፣ የታሪኩ ማጠናከሪያ አድርጓል፡፡
አሁን ደግሞ ወደ ሌላ የጥበብ
ዘውግ እናምራ ቲያትር፡-
‹ፍቅር እስከለቃብር›ን ተንተርሰው
ከተሰሩት ቲያትሮች መሐከል የጌታቸው ታረቀኝ ‹ደራሲው በሰማይ ቤት› እና የሳሙኤል ተስፋዬ ‹ምዕራፍ ሁለት› ይጠቀሳሉ፡፡
ከሐዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከመቃብር
ሰብለ ወንጌልን፤ ከበዓሉ ግርማ ከደራሲው አበራ ወርቁን፤ ነጥሎ በማውጣት ሰማይቤት እንዲገናኙ የሚያደርገው ‹ደራሲው በሰማይ ቤት›
ቲያትር ገጸ-ባህርያቱ በመጽሐፍ ውስጥ የምናውቅላቸውን ባህሪ እንደያዙ በልዩነቶቻቸው ላይ የሚያደርጉትን ፍትጊያ ለማሳየት የጣረ
ነው፡፡
‹ምእራፍ ሁለት› ድርሰቱ የደራሲና
ተዋናይ ሳሙኤል ተስፋዬ ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም በተስፋዬ ገብረሐና አዘጋጅነት እና በደስታ አስረስ፣ በሒወቴ አበበ (ነፍስ ይማር)፣
በሳሙኤል ተስፋዬ እና በሌሎችም ተዋንያን ለእይታ በቅቷል፡፡ በአሲስ አበባ ዪኒቨርስቲ ብቻ የታየውን ‹ምዕራፍ ሁለት› በድጋሚ ለመድረክ
ለማብቃት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን በመስማታችን በዚህ አጋጣሚ ይበል ለማለት እንወዳለን፡፡
ከትልልቅ መጻህፍት የተውጣጡ
ምናባዊ ገፀባህርያት በተዘጋ ቤተመጻህፍት ውስጥ የሚያደርጉትን ውይይት የሚያሳየው ምእራፍ 2 ባለ አንድ ገቢር ነው፡፡ 12 ገፀባህርያት
አሉት፡፡ ከነዚህ መካከል ከፍቅር እስከ መቃብር ላይ ሰብለወንጌልን እና ጉዱ ካሳን፤ከከአድማስ ባሻገር ሉሊትን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ
ጠቢቡ ሰሎሞንን እና ሎሎችንም ከኦቴሎ፣ ከሐምሌት፣ ከአላቻ ጋብቻ፣ ከእናት አለም ጠኑ ላይ በመውሰድ በየራሳቸው ጥግ እውነቴ የሚሉትን
እንዲሞግቱ እድል ያመቻችላቸዋል፡፡
‹‹ ሰብለወንጌል፡- እባክሽ
ሉሊት እሺ በይኝ፡፡ ይህ ነገር ምንም አይጠቅምሽም፡፡ ማንንም አይጠቅምም፡፡
ሉሊት፡- አይሆነም አልኩሽኮ
ሰብለወንጌል፡፡ …በፍጹም ለአዳም ዘር የሚያዝን ልብ የለኝም፡፡ ወንዶችን እየናቅኳቸው፣ እያስለመንኳቸው፣አዋርጄ ላሰቃያቸው እፈልጋለሁ፡፡
ታዲያ አንዳንዴ ምኞቴ ጣር ሆኖብኝ ስሰቃይ አስራለሁ ›› ምዕራፍ ሁለት ቲያትር ገጽ 19 /ያልታተመ/
ፍቅር እስከ መቃብር በልብወለዶች
እና በቲያትር ስራዎች ብቻ ሳይሆን በዘፈኖቻችን ላይም ተነስቷል፡፡
‹‹አባ ዓለም ለምኔ - አባ አለም ለምኔ
ጀንበር ወጥታ አትገባም - ሳልሰራ ኩነኔ››
እጅጋየሁ ሽባባው
እጅጋየሁ በበሳል ግጥሞቿ የምትታወቅ፣
የዘፈኖቿን ግጥምና ዜማ ራሷ የማታዘጋጅ ድምፃዊት ነች፡፡ በ 1995 ዓ.ም በተለቀቀው አልበሟ ላይ ባለው አባዓለም ለምኔ ዘፈን
ውስጥ የፍቅር እስከመቃብሯን ሰብለ የመጨረሻ ዘመናት እናደምጣለን፡፡
‹‹ዛሬ ቀጭን ኩታ - ነገ ራቁቴን
ያገኙትን ወዳጅ - ደግሞ ማጣትን››
የዘፈኑ መነሻ ፍቅር እስከ መቃብር
መሆኑን የምታሳውቅባት ቃል ‹አባ ዓለም ለምኔ› ናት፡፡ ለዘፈኗ የበለጠ ህይወት ልትሰጠው ሽታለችና ሙሉ ለሙሉ ፍቅር እስከመቃብር
ታሪክ ላይ አላጣበቀችውም፡፡ ስለመጽሐፉ አንድም ቀን ሰምቶ የማያውቅ፣ ታሪኩን ያልሰማ ሰው እንኳን ቢሰማው ትርጉም እንዲሰጠው፤ገብቶት
ተመስጦ እንዲሰማው አድርጋ አበጅታዋለች፡፡
‹‹አምላኬ እባክህ ጠብቀኝ!
ሰለስቱ ደቂቅን ከሳት ዳንኤልን ከግበ አናብስት ያዳንክ አምላክ እባክህ አድነኝ! አምላኬ የምህረት መልእክተኛህን ላክልኝ›› ፍቅር
እስከ መቃብር ገጽ 495
በቀኝ አውለህ አሳድረኝ
ክፉ ነገር ሳይነካኝ /ጂጂ/
ሌላው ድምፃዊ ሚኪ ዘሪሁን
/ማንዴላ/ ነው፡፡ በ 2005 ዓ.ም ባወጣው ‹ማንዴላ› አልበሙ ውስጥ የተካተተው እና ከአልበሙ በፊት በነጠላ ዜማነት የሰማነው
‹ሐዲስ ዓለም› የተሰኘ ዘፈኑ ፍቅር እስከ መቃብርን መሠረት አድርገው ከተሠሩት ዘረኖች ውስጥ ይመደባል፡፡ ዘፈኑ ገላጭ በሆኑ ውብ
ስንኞች የተሞላ ነው፡፡ በወቅቱ ነጠላ ዜማው የተሰራጨው ቴዲ አፍሮ በሚል ስያሜ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የዚህ ምክንያት ከድምጻቸው
ተፈጥሯዊ መመሳሰል ውጪ ሚሊ ዚ የቴዲ አፍሮን የአዘፋፈን ስልት ሆነ ብሎ የሚኮርጅ ወይም ድምጹን ለማመሳሰል የሚጥር ያስመስልበታል፡፡
ሐዲስ ዓለም
ሐዲስ ዓለም
ዓየሁ ባንተ ውስጥ የልብህ ስሜቱ ባይሰምርም በብዕር
ለሸክም የበዛ ፍቅር
ለካስ ያደርሳል ወይ እስከ መቃብር
የደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁን ግላዊ የፍቅር ታሪክ ከምናባዊ የፈጠራ ውጤታቸው ጋር
ያስተሳሰረ ስንኝ ነው፡፡ የሐዲስ ዓለማየሁ ለሸክም የበዛ ፍቅር መቃብር ድረስ መዝለቁን ያብራራል፡፡
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በቅርቡ
ባስነበበን ጽሁፍ ‹‹ጋሽ ሐዲስ ባለቤትዎ ወ/ሮ ክበበ ጸሐይ ካረፉ በጣም ረጅም ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ በነዚህ ዓመታት ግን እርስዎ
ሌላ ትዳር አልመሰረቱም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ምክንያቱ ምንድነው? አልኳቸው፡፡ ጋሽ ሐዲስ የግራ እጃቸውን ከፍ አደረጉልኝ፡፡ እጃቸው
ላይ ቀለበት አለ፡፡ ግራ ስጋባ እንዲህ አሉኝ፡፡ ‘ይህንን ቀለበት ያሰረችልኝ ክበበፀሐይ ነች፡፡ እኔም ለሷ አስሬአለሁ፡፡ እሷ
ድንገት አረፈች፡፡ እዚህ ጣቴ ላይ ያለው እሷ ያሰረችልኝ ቀለበት ነው፡፡ ቀለበቱን አልፈታችውም፡፡ ሳትፈታው አረፈች፡፡ ስለዚህ
ይህንን ቀለበት ከኔ ጣት ላይ ማን ያውልቀው? ካለ እሷ፤ ካለ ክበበፀሐይ ይህንን ቀለበት ከጣቴ ላይ የሚፈታው የለም፡፡’ አሉኝ፡፡››
ሰንሰቅ ጋዜጣ ግንቦት 1 2009
በልብወለድ ታሪኩ ጎን ሆነን
ስንመከለተው ደግሞ የበዛብህ ታሪክ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አባዓለም ለምኔ ሰብለ ወንጌል ብትሆንም፤ ድምፃዊው ለበዛብህ ይሰጠዋል፡፡
በቃ አንቺን አሳጣኝ አወይ ድህነቴ
አጀብ ደስታ ህይወቴ የለች መድኒቴ
አባዓለም ለምኔ ይሻለኛል ሞቴ
በኪነ-ጥበባዊ ሒስ ስራዎች ላይ
አንድ አከራካሪ ጉዳይ አለ፡፡ ስራዎቹን የሚተነትነው ግለሰብ የታየውና በትንታኔው የሚያነሳቸው ነጥቦች እውነተኛ የደራሲው ሐሳብ
ባይሆኑስ? የሚል፤ ሐያሲው ሥራውን ከአቅሙ በላይ አግዝፎት ቢሆንስ? የሚል፤ የአንደኛውን ተከራካሪ ወገን ምላሽ እንጠቀምበት፡፡
ሥራው የሚናገረው በሙሉ ደራሲው ያላሰበው እንኳን ቢሆን የሥራው ጥንካሬ ነው፡፡
በቀጣይ የምንመለከተው ቴዎድሮስ
ካሳሁን ኢትዮጵያ በተሰኘው አልበሙ የተጫወተውን ‹‹ማር እስከ ጧፍ›› ነው፡፡ ከርዕሱ እንጀምር፡
ማር ጣፋጭ፣ በሁሉም የሚወደድ
ተፈላጊ ነው፡፡ የማር የመጨረሻ ዝቃጭ ደግሞ ሰም ነው፡፡ ሰሙ ለምግብነት አይዋል እንጂ፤ ጣፋጭነቱ ይቀንስ እንጂ፤ የማይፈለግ አይሆንም፡፡
የሚጣል አይደለም፡፡ ለሌላ ተግባር ይውላል፡፡ ለጧፍ መስሪያ፤ ምላስ ላይ ጣፍጦ ለጣዕም፤ ሆድ ውስጥ ገብቶ ለጤና የሚስማማው ማር
እየነደደ መስዋዕት ሊሆን፤ እየተቃጠለ ብርሓን ሊያበራ፤ ቢጫ ልብሶ ይመጣል፡፡
ማር ሲገባ ገዳም ድንጋይ ተንተርሶ
ጧፉም እንደመናኝ እዩት ቢጫ ለብሶ
የሰብለወንጌልን ውበት፣ የተወዳጅነቷን፣
የአለመሸጋነቷን ጥፍጥና ወይም ማርነት ለፍቅር ራስዋን እስከመስጠት፣ የሞትን መንጋጋ እስከመጋፈጥ የደረሰ ጧፍነት እንዴት ባለ ውብ
ገለጻ /Expreshion/ እናዳስቀመጠው ልብ ይሏል፡፡
ታሪኩን እና በታሪኩ ድጋፍሰጪነት
መግለጽ ያሰበውን ሐሳብ፣ ማጋባት የፈለገውን ስሜት በዜማ እያዋዛ በተመረጡ ቃላት እያለሰለሰ ይነግረናል፡፡ ጉዳዩን ከመለኮት ጋርም
ያገናኘዋል፡፡
ለካ ሰው አይድንም በኦሪቱ ገድል
ወንጌል ይዞ መጥቶ ፍቅር ካረገ ድል
ወንጌልን ይዞ በምድር ላይ ስለሰበከው፤
የኦሪቱን ህግ (ብሉይን) በአዲስ ስርዓት (በሀዲስ ኪዳን) ስለተካው ‹የሰው ልጅ› በመንቶ ስንኞች ሸምኖ ያቀርብልናል፡፡
የመደቡ ልዩነት ተሸሮ የፍቅር
አሸናፊነት የተንጸባረቀበት፤ የባላባት እና የታችኛው መደብ የልዩነት ግንብ በፍቅር ጩኸት ስለመናዱ የሚያትት እማሬያዊ ፍቺም ዓለው፡፡
ብራናዬ አንቺ የልጅነቴ ቀለም
እኔ እንዳንቺ ያጠናሁት ፊደል የለም
.
በጊዜ ተደፋ የቀለሙ ቀንዴ
የኔ ፊደል መሆን ካንቺ አዳነኝ እንዴ
ከላይ ካነሳናቸው ዘፈኖች በተለየ
በርካታ ገጸ-ባህርያትን፣ አካቶ ይዟል፡፡ /ውድነሽ በጣሙን፣ ዲማ ጊዮርጊስ፣ ማንኩሳ፣ ቀለመወርቅ፣ ካሳ፣ ሲኖዳ ዮሐንስ፣. .
./ የደራሲውን እና በራሳቸው በክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ሳይቀር ‹ህይወት ዘርቶበታል› ተብሎ የተመሰገነው ወጋየሁ ንጋቱንም
አንስቷል፡፡ ባለታሪኮቹን ካነሳሳና ካወደሰ አይቀር የትረካው ድባብ ያለ ዋሽንቱ አይደምቅምና ለባለዋሽንቱ ለዮሐንስ አፈወርቅም ቦታ
ቢሰጥ የበለጠ ምሉዕ ያደርገው ነበር፡፡
ይህ ዘፈን በርካታ ውይይት እና
ክርክሮችን አስተናግዷል፡፡ የድጋፍ እና የቅሬታ ሐሳቦችንም ተነስተውበታል፡፡ የውይይት እና የሐሳብ መነሾ መሆኑ በራሱ በጎ ጎን
እንደሆነ ወስደን፤ በልከኛ ስንኞች የተዋቀረ ግሩም ሥራ መሆኑን መስክረን፣ አድማጭን ከፍ ላለ ምልከታ ጋብዘን፤ . . . እንቋጨው፡፡
በወፍበረር እይታ የተሰናዳው
ድንክዬ ምልከታ ከርዕሰጉዳዩ ግዝፈት አንፃር ሲታይ ቢያጥርም ለባለ ውሱን ገጽ መጽሔት ግን ልከኛ ነው፡፡ የአምዱ ዋና ዓላማ የሀሳብ
መዘርዝር አቅርቦ በየፊናችን እንድንተነትው ማድረግ በመሆኑ፤ ያንን ተስፋ እናድርግና የዛሬውን እንደምድመው፡፡ ለወሩ ያድርሰን እና
ሌላ የኪነጥበብ ርዕሰጉዳይ ላይ ደግሞ በጋራ እንቆዝማለን፡፡
No comments:
Post a Comment