Showing posts with label ልብወለድ. Show all posts
Showing posts with label ልብወለድ. Show all posts

Monday, November 17, 2014

ከብዙ ዓመታት በኋላ የሚነገር የከብዙ ዓመት በፊት ታሪክ



መግቢያ


ጥቂት የማይባሉ አያሌ ዘመናትን ወደፊት ተሻግረን ከቀናቶች መካከል ባለ የተለመደች አዘቦት ቀን ላይ ነን፡፡ ተንጠራርተን እያስተዋልናት ባለችው በዚህች ተራ ቀን  ድሮ ምን ይመስል እንደነበር ልንቃኝ ነው፡፡ በአሁን የጊዜ ፈረስ ተፈናጠን ነገን በዛሬ ልናነፃፅር . . .


ትዝታ አይደለም፡፡ ትዝታ የኖሩትን በምናብ መድገም ነው፡፡ ከትውስታ ጓዳም ከህልውና መድረክም ሊሰርዙት አይቻልም፡፡ መከሰቱም ማለፉም የተረጋገጠ ነው፡፡

 
ትንቢት አይደለም፡፡ ትንቢት ያልኖሩትን መገመት ነው፡፡ ስምረቱንም ክሽፈቱንም ማረጋገ ከባድ ነው፡፡
ይህ ከሁለቱም ይለያል፡፡ ሁለቱንም መሳይ ገፅ አለው፡፡

Tuesday, September 9, 2014

ጉዞ


(ንዑስርዕስ ) ወደብርሀን
የምንገኘው ብርሀን ከሚታደልበት ብርሀን ውስጥ ነው። የብርሀን ማነስ ድንግዝግዝን ካወፈረበት ዓለም። ብርሐን ማለት ዕውቀት ነው። ዕውቀት ማለት እውነት፣  እውነት ማለት ውበት ማለት ነው። ሐቀኛ ውበት ከልከኛ እና ከቀና እውነት ይወለዳል። ውበት ሁሉ እውነት አይደለም። እውነት ሁሉ ውበት አይደለም። በሀቅ ካባ የተጀቦነ - በበግ ለምድ የተሸሸገ ተኩላዊ እውነት አለ። በሽንገላ ከንፈር ማንነቱን የተነጠቀ እውነት አለ። ብልጭልጭ የጋረደው። አርቴፊሻል ውበት አለ በብልጭልጭ ብዛት፣ በወከባ ብዛት፣ በግርግር ብዛት ውበት ማማ ላይ የተሰቀለ። የድንጋሪው ማጥሪያ ወንፊት ማስተዋል ነው። ማስተዋል። በመገለጡ ውስጥ ያለውን ቅኔ መፍታት።

ግስጋሴው ወደፊት ነው። ፈትለፊቱ ድንበር የለውም። ጫፉ መሻት ነው። ዕውቀትን መሻት። ጥልቀትን፣ ምጥቀትን፣ ስፋትን፣ ርዝመትን መሻት . . . ሁሉም በፍላጎት ነጻ ፈቃድ የሚወለዱ፤ በጥረት እልህ አስጨራሽ ትጋት የሚያድጉ እና የሚጎለምሱ ነገዎች ናቸው። የዕውቀት ኬላ ማማዎች . . . ያልደረሱበትን፣ ያመረመሩትን እየጓጉ የሚናፍቁበት፤ የያዙትን አጣጥመው የተሻለ የሚማትሩበት፤ እንደመሰላል ያለ የከፍታ አጋዥ። ተንጠራርተው እየጨበጡ። የጨበጡትን ሳይረግጡ ይልቁንም ባለው ላይ እየደመሩ። የመንገዱ መቋጫ እርካታ ነው። ደረስኩ፣ በቃሁ፣ ነቃሁ፣ በሰልኩ፣ ባሉበት ቅጽበት የጉዞው ምዕራፍ ይዘጋል። ‘ብርሀናማ ጨለማ’ን ‘ወርቃማብርሀን’ ነው ብሎ በማምለክ ቅያስ ውስጥ መዳከር ይጀመራል። . . .

Friday, August 22, 2014

0(ዜሮ)


‹‹ከቁጥሮች መካከል የመጨረሻውን ባዶ ደረጃ የያዘችው ‘0’ ናት፡፡ አንተም በሰው ልጆች የዕውቀት፣ የዐስተሳሰብና የዐመለካከት መስፈርቆች ስትገመገም ማርክህ ዜሮ ቢሆን ’ዋጋ የለኝም’ አትበል፡፡
ያቺ . . . የቁጥሮች ሁሉ አናሳ ዜሮ በሙሉ ቁጥሮች ስሌት ወቅት ቀዳሚውን የፊት ወንበር ትቆናጠጥ እንጂ፣ ዋጋ ባላቸው የመቁጠሪያ ቁጥር መገልገያዎች እርሷን ከፊትለፊት ቦታ ያስቀደመ ትርጉም አልባ ድምሮችን ከማንኳተቱ በተጓዳኝ አላዋቂነቱን ያሳብቃል፡፡ ታዲያ . . . አንተና መሰሎችህ አጠቃላይ ሰዋዊ ውጤታችሁ ዜሮ ሆኖ ሳለ ከሁሉም ፊት መቆማችሁ፣ ሙሴነትን መተግበራችሁ ይቅርና ለማሰብ መነሳሳታችሁ ራሱ ከስህተት በላይ ነው፡፡ 
ዜሮ ከፍ ካሉ ቁጥሮች መካከል አለያም ከበስተኋላ በተከታይነት ስትቆም የምታሳየውን ትርጉም አዘል ለውጥ አስተውል፡፡ ራስ በመሆን ብቻ ሳይሆን ጭራ በመሆንም ግዙፍ ለውጥ አምጪ ታሪክ መስራት ይቻላል፡፡ ራስህን ሁን፡፡ ››

Thursday, August 14, 2014

አጣብቂኝ



ላለው ይጨመርለታል። ብር ላለው ወርቅ፤ ጠገራ ላለው ማርትሬዛ፤ መከራ ላለው ፍዳ ይጨመርለታል። ትላንት የተጨመሩለትን አሰበ። በዲግሪ ላይ ስራ፤ በስራ ላይ ረብጣ፤ በገንዘብ ላይ ቆንጆ ሚስት፤ በሚስት ላይ ውብ ልጅ ተጨምረውለታል። ደስታቸውን እያጣጣመ አልፏቸዋል። በሚገባ ተጠቅሞባቸዋል። ኖሯቸዋል።

ሁለተኛውን ምዕራፍ ግን በአግባቡ ማስተናገድ አቃተው። ሳቅን የሚያውቅ የልቅሶን ጣዕም ለመረዳት ከሳቁ መንፈስ በሀሳብም በምግባርም መውጣት እንዳለበት ዘነጋ። እሱ መከራ፣ ፈተና . . . ብሎ የገለጸውን የህይወት ክፍል በብቃት መተወን ተሳነው። ቀድሞ በበጎ ገጹ ሳለ“ተጨመረልኝ” ሲል በ ‘ለኔ’ የገለጸውን አሁን“ ተጨመረብኝ” በማለት በ ‘እኔ ላይ’ አደረገው።

በትላንትናው ውስጥ የገነባው የኑሮ ግንብ የእንቧይ ካብ የሚሆንባቸውን ምክንያቶች በቅደም ተከተል ደረደረ።
*ውብ ፍሬው ካለማወቅ ብርሀን ታመልጥ ዘንድ፤ ክፉውን እና በጎውን በሚያስለየው የዕውቀት ጠበል ትጠመቅ ዘንድ እንዳትችል ኪሱ ከስቷል።

Tuesday, April 9, 2013

ፍትህ

ከዳዊት ዓርአያ
/አጭር ልቦለድ /
ብርሀን ባለበት የጨለማ ግርማ ይገፈፋል። ጨለማ ሲኖርም የብርሀን ጸጋ ስፍራውን ያስረክባል። ይህ ክፍል እንደዚያ አይደለም ፡፡ ብርሃንም ጨለማም ነግሰውበታል። ሠሃራም ሳይቤሪያም፣ ወተትም ቡናም ያልሆነ ማኪያቶ ክፍል ነው።

ጡንቻውን በስፖርት ያደለበ፣ አንጎሉን በዕውቀት ያጣበበ፣ የሰውን ልጅ ከትንኝ ነፍስ የሚያስተካክል፣ ራሱን ከትቢያ በላይ የሚያበክት፣ አማኝ ከሀዲ ተጠራጣሪ… ከያይነቱ ተውጣጥቶ የተጠራቀመ የ’ሰው’ ዓይነት አለበት።

ከጥፋታቸው እንዲማሩ ወይንም በወንጀላቸው እንዲማረሩ የሚታሸጉት ህ ስፍራ ከአንስታይ ፆታ በቀር የእድሜ ገደብ የለበትም። የትምህርት፣ የኑሮ፣ የዕውቀት፣ የእምነት፣ የአስተሳሰብ ልዩነት ቢኖርም ኗሪዎችን ከመግባባት አያግድም። ባለመግባባት ከሚፈጠር ግጭት በላይ በመመሳሰል የሚፈጠረውን ’ሰላም’ ሁሉም ተገንዝቧል። መስሎ አስመስሎ ቀን ይገፋል። በተመሳሳይ ወግ ተመስጦ ተመሳሳይ ሳቅ ይስቃል።

Wednesday, January 30, 2013

እየመጣ ነው!

እንደምን አላችሁ!!!
መልካምና አመቺ በምንላቸው መንገዶች ሁሉ ተጠቅመን የሆድ የሆዳችንን ስናወጋም አልነበር? እነሆ ሰፋ ያለ ሜዳ አሰኘንና በዚህ መንገድ ደግሞ ልንገናኝ ነው!  በቅርብ ቀን 
ኪነጥበቡንም ማህበራዊውንም ጉዳይ እናነሳሳበታለን
http://dawitaraya.blogspot.com