Saturday, March 10, 2018

የጥያቄዎቹ የአመላለስ መንገድ ይታረም!


በአንድ ወቅት ማህተመ ጋንዲ ‹‹የሐሳብ መለያየት ጠላትነት አይደለም፡፡ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ዋነኛ ጠላቴ ሚስቴ ትሆን ነበር፡፡›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በሐሳብ መለያየት አለመዋደድ አይደለም፡፡ በአንድ ርእሰ ጉዳይ የተለያየ አቋም መያዝ የጠላትነት ምልክት አይደለም፡፡ አንዱ የስልጣኔ መለኪያ የማይጥምህን ሐሳብ ታግሶ ማድመጥ መቻል ነው፡፡
 
ያለፉትን ዓመታት የሐገራችንን ክራሞት ስንታዘብ የሥህተቱ መጀመሪያ ልዩነትን መጥላት ነው፡፡ ተቃውሞን አለመሻት ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ የሥልጣን መንበሩ ላይ በንግስና ካሉት መኻል መቶ በመቶ ህዝቡን ያስደሰተ መንግስት የለም፡፡ አልነበረም፡፡ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ሥርአቱን የማይደግፍ ሊኖር ይችላል፡፡ እንኳን መጥፎ የሚባለውን ድርጊት ጥሩ ነገሮችም የማይዋጡለት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን የአጠቃላይ ስዕሉ አንድ ቀለም ነውና አይጣልም፡፡ የግዙፉ ምስል ትንሽ ክፍል ነውና ከጨዋታ ሜዳው አይባረርም፡፡
ህዝብ እንደ ህዝብ የመምረጥ መብት እንዳለው ሁሉ፤ የመኖር መብት እንዳለው ሁሉ፤ የመቃወም መብት እንዳለውም ሊታወቅ ግድ ነው፡፡ ክልከላ የሁሉም ችግሮች መፍትሔ አይደለም፡፡ ህዝቡ ጥያቄውንም ሆነ ተቃውሞውን የሚያሰማበት መድረክ አለመኖሩ(መጥበቡ) በሐይማኖታዊ እና ማህበረሰባዊ ስብሰባዎች ላይ ድምጹን እንዲያሰማ አስገድዶታል፡፡ የቢሾፍቱውን እሬቻ እና የወልዲያውን ጥምቀት ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፡፡  
የኢህአዴግ መንግስት ለተነሱት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሁሉ የሰጠው ምላሽ የሐይል እርምጃ መሆን አልነበረበትም፡፡ እርምጃው ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት ያስከፈለ፤ የማይታረም ጥፋት ነው፡፡ በታሪክ መዝገብ ላይ በዓላቱ በተከበሩ ቁጥር የሚታወስ ጨለማ ክስተት ሆኗል፡፡ በዳይ ተበዳይን ቂም የሚያቋጥር ምግባርም ነው፡፡
ግጭቶች መኖራቸው የእንቅስቃሴ እና የለውጥ ምልክት ነው፡፡ ተቃውሞ ስህተትን የመንቀስ ድርጊት ነው፡፡ ህዝብ ያልተመቸውን ሲቃወም እንዲመቸው የማድረግን የቤትሥራ እየሰጠ ነው፡፡ ህዘብ ‹‹ልክ አይደለህም!›› ሲል ልክ ወደመሆን ክልል ተመለስ የሚል ማሳሰቢያ ነው፡፡ መፍቻ መንገዱም ጥይት መሆን አልነበረበትም፡፡ የማስፈራራት፣ የመግደል፣ የመሳሪያ ብዛት ወዘተ የህዝብን ተቀባይነት ለማግኘት እንደማያስችሉ የመላው አፍሪካ መሪዎች እና ህዝቦች ታሪክ ብርቱ ምሳሌ ነው፡፡  
በኃይል የሚፈቱ ችግሮች ካሉ ለጊዜው ጥገናዊ ለውጥ ያመጡ እነደሁ እንጂ አይዘልቁም፡፡ የአጭር ጊዜ እፎይታን (እፎይታ ከተባለ) እንጂ፤ ሥር ነቀል መፍትሔ አያመጡም፡፡ ለዚህም ምስክሩ ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡ ጭቆናን ታግሎ ለመጣል በረሃ ገብቷል፤ እኩልነትን እና ፍትህን በመላ ሐገሪቱ ለማስፈን መስዋእት እንደሆነ ዘወትር ሰምተናል፤ . . . እና አሁን ምን እያደረገ ነው? ወታደራዊ መንግስት የሆነ እስኪመስል ግርግሮችን ሁሉ በጥይት መበተን ለምን ፈለገ? ጥያቄዎችን ሁሉ ለምን በሐይል ለመፍታት ይጥራል? ተቃውሞዎች ሁሉ በሞት፣ በእስር እና በማስፈራራት ለምን ተደመደሙ? 
የመፍትሔ ፍለጋ እና ትግበራ መንገድን በጥንቃቄ ይመረጥ፡፡ ለተቃውሞ ያለው ሸውራራ እይታ ይታረቅ፡፡ ትልቁን ወንዝ ለማድረቅ ትንንሽ ገባሮቹን ማሳጣት ቀዳሚ ተግባር እንደሆነው ሁሉ፤ እየገዘፈ የመጣውን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ከትንንሾቹ ገባሮች እስከ ዋናው ምንጭ ድረስ ለመሔድ የተነሳሳ ፓርቲ፣ መንግስት፣ መሪ እና አመራር ያስፈልገናል፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!!

© ዘመን እና ጥበብ መጽሔት ------- 2010ዓ.ም እትም ላይ የወጣ

No comments:

Post a Comment