Monday, December 11, 2017

ያልተገባ አድናቆት የወለዳቸው የጥበብ ሥራዎች

ለሰሩ ሰዎች፤ ልከኛ በሆነ መንገድ ተጉዘው የራሳቸውን በጎ አሻራ ላኖሩ ጥበበኞች፤ ምስጋናን መቸር ተገቢ ነው፡፡ ለላቀው ጥበባቸው አድናቆት እና ሽልማት ማበርከት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የዚህ ክዋኔ ግብረመልስ ከዋነኞቹ የአሁን ጥበበኞች በላይ ለከርሞ ተተኪዎች የጎላ ጠቀሜታ አለው፡፡ በጠንካራ ሥራዎቹ ሰበብ እውቅና የተሰጠው፤ በላቀ አበርክቶው ምክንያትነት ምስጉን ለመባል የበቃ፤ . . . የጥበብ ዋርካ ሲበረክት አርዓያ የሚያደርጉት የነገ ፍሬዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ ያግዛል፡፡ ሁኔታው ለጠጥ ተደርጎ ሲታሰብ እንደ ሐገር እየተተካካን ሩቅ እንድንጓዝ የሚያስችለንን ነዳጅ የሚሞላልን ግብአት ነው፡፡


ነገሩ በጥንቃቄ የማይከወን ከሆነ ግን የከባድ ጥፋት መነሻ ይሆናል፡፡ ለማይታረም ብልሽት ጅማሬነት ይታጫል፡፡ በአሁን የኑሮ ፈረቃ በተዛባና ባልተደላደለ መንገድ የእውቅና ካብ ላይ የተፈናጠጠን ዘመነኛ ማሞገስ፣ ማወደስና መሸለም ነገ አግድም ለሚያድገው ሠላሳ እና ስልሳ የሚያፈራ ብልሹ ፍሬ ተስማሚ የአየር ንብረት ማበጀት ነው፡፡ በተቃራኒው በጎ መንገድ የያዘን ተስፈኛ በዝምታ ማለፍ፤ ከእውነት ምንጭ የተቀዱ ስራዎቹን አለመዘከር፤ . . . ከሥር ሊበቅሉ የሚችሉ ተተኪ ችግኞችን ማቀንጨር ነው፡፡

በኪነጥበቡ የመሮጫ ሜዳ ላይ ከማወቅ በፊት መታወቅ የመረጡ፤ ከሥራ በፊት ገንዘብ ያስቀደሙ፤. . . ደፋሮች የበረከቱት ለዚህ ይመስለኛል፡፡

አሁን በምንኖርባት የ21ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያዊያን ‘ጥበበኞች’ 

‹‹እንኳን ሌላ ነገር ላነብ የፊልም እስክሪፕትም ግድ ሆኖብኝ ነው›› የሚሉ እውቅ ተዋንያን፤ ‹‹ማንበብ ላይ እስከዚህም ነኝ መጽሐፍ ካነበብኩ ብዙ ቆይቻለሁ›› የሚሉ የግል ሚድያ ባለቤቶች፤ (በሚድያቸው ላይ የተለያዩ ምሁራንን እና አንባቢያንን እየጋበዙ የሚጠይቁ) ‹‹ሥራ ስለሚበዛብኝ አላነብም›› የሚሉ የማስታወቂያ ባለሙያዎች እና የፊልም ደራሲዎች አሉን፡፡
ለክብራቸው ስንል በዚህ ፅሁፍ ላይ ስማቸውን ባንጠቅስም (እነሱ ራሳቸውን ባያከብሩም እኛ እናክብራቸው)  


የባህር ማዶዎቹ ይህን የሚያመጣጥኑበት ስርአት አላቸው፡፡ የገበያውን ሁኔታ አሸንፎ በህዝብ የተጨበጨበለት ሥራ፤ በባለሙያዎች ሙያዊ ትንታኔ አፈርድሜ ሊበላ ይችላል፡፡ በርካታ ገንዘብ በመስራት ያልተሳካለት ጠንካራ ሐሳብ ያነሳ ሥራ የምርጥነትን ካባ ሊያሸንፍ ይችላል፡፡ ዘርፉ ብዙ ነው፡፡ አንድ አንደኛ የለም፡፡ በየዘርፉ በርካታ አሸናፊዎች አሉ፡፡ መለኪያው ህዝብ ይወደዋል ብቻ አይደለም፡፡ 


ወደጓዳችን ስንመለስ ግን ጉዳዩ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ጥበቡ እንደተራ የሸቀጥ ንግድ ገንዘብ ብቻ እያባረረ፤ ተራ ጭብጨባ ብቻ እየገዛ ይኖራል፡፡ ከዓመቱ ምርጥ እስከ ሎሬትነት ማእረግ በትንንሽ የማስታወቂያ ድርጅቶች በክፍያ፣ በእውቂያ፣ በመሰለኝ እና በደሳለኝ እየታደለ ነው፡፡ የደራሲያን ማህበር፣ የፊልም ሰሪዎች ማህበር፣ የሙዚቀኞች ማህበር . . . ለሙያቸው ልዕልና ቆመናል የሚሉ ማህበራትም ዝምታን መጠዋል፡፡  

  
ወደንም ሆነ ሳንወድ፤ ብቻ በማናቸውም ሁኔታ የምንከታተላቸው ሚድያዎች ደግሞ የመስፈሪያ ሚዛኑን እያዛቡት ይገኛሉ፡፡


የሚዛኑ መዛባት ያስከተለው ማእበል ያለ እውቀትና ተሰጥዖ የሚዳክሩ ጉልበተኞች ሜዳውን እንዲቆጣጠሩትና ሥፍራውን እንዲያጣብቡ እድል ሰጥቷል፡፡


ማንም ጥበበኛ መመዘን ያለበት ነኝ ብሎ በመጣበት ዘርፍ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ደራሲ በአሉ ግርማ በረጃጅም ልብወለዶቹ አስደምሞናል፡፡ የግጥም መጽሐፍ ስለሌለው፤ አጫጭር ልብወለዶች ስላላሳተመ፤ በሚሉ መስፈሪያዎች መዳኜት የለበትም፡፡


በሚችለው፣ በመረጠው፣ በተካነበት፣ በአደባባይ በመጣበት ዘርፍ ብቻ ተለክቶ ካልሆነ ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡ የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰን በህይወት ያጣነው ሰሞን ይነሱ ከነበሩ ጉንጭ አልፋ ክርክሮች መሐል አንዱ፡-
ጥላሁን በራሱ የሠራው የግጥምና ዜማ ፈጠራ የለውም፡፡ ሥለዚህ ክብሩን እናሳንስበት የሚል ዓይነት ይዘት የነበረው ይገኝበታል፡፡
በመጀመሪያ ጥላሁን ራሱን የገለጠው ‹ድምጻዊ› በሚል የጥበብ ዘርፍ ሆኖ ሳለ በደራሲነት መዳኜት ለምን ያስፈልገዋል? በማያዳግም ሁኔታ አስውቦ እና አርቅቆ ያዜማቸውን ግሩም ዘፈኖች አስጥሎ፤ የተቸረውን የተፈጥሮ ስጦታ አሳድጎ የብቃት ጣራ ላይ ማድረሱን አስጥሎ፤ ሌላ መሥፈሪያ መፈለግስ ተገቢ ነው? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ሐሳብ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ጥላሁን ከ 15 በላይ ስራዎቹን ዜማዎች በራሱ ሰርቷል፡፡)
በአብዛኛዎቹ ቃለመጠይቅ አድራጊዎች አንደበት ከማይጠፉት ጥያቄዎች መኻል አንዱ ፡-
‹‹ከዘፈኖችህ መኻል ባንተ የተሰሩ ግጥምና ዜማዎች አሉ?›› የሚለው ነው፡፡ የጥያቄውን ስህተትነት ከመላሾቹ ምላሽ ውስጥ ማውጣት ይቻላል፡፡ ‹‹አዎ ሰርቻለሁ›› ብሎ እከሌ እነከሌ እያለ መዘርዘር ያልቻለው ድምጻዊ

 ‹‹ሐሳቦች ነግሬ እንዲፅፉልን አደርጋለሁ፤ ዜማ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመተባበር እሰራለሁ፤ 
 እየሞከርኩ ነው በቅርቡ ለፍሬ ይበቃሉ፤ . . .›› የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ተጠያቂው በልበ ሙሉነት 
 ‹‹አላውቅም!›› የሚል ምላሽ የመስጠት ድፍረት ማጣቱ ጎልቶ ይታያል፡፡ ‹‹እኔ ድምጻዊ ብቻ ነኝ!››  የሚል ወኔ እንደሌለው ያሳብቃል፡፡ 

ድምፃዊ ለመሆን የሚያስፈልገው የማዜም ችሎታና ተሰጥዖ ነው፡፡ የዘፈን ግጥም ጸሐፊ የመሆን መስፈርቱ ድምጸ መረዋነት አይደለም፡፡ ነገርየው የተምታታ ይመስላል፡፡ ድርብ ተሰጥኦ ያለው ሰው ከፍያለ አድናቆት ቢቸረው ልክ ነው፡፡ የአንድ ተሰጥኦ ባለቤት የሆነን ሰው ማንኳሰስ፤ እንዴት ከአንድ በላይ አልቻልክም ብሎ ማነወር ግን ከስነምግባር ውጪ ነው፡፡ ስህተት ነው፡፡ ይልማ ገብረአብ ለልዩ ልዩ ድምፃዊያን ከ2000 በላይ የዘፈን ግጥሞችን ሲሰራ ባለማንጎራጎሩ መወቀስ ነው ያለበት ወይስ በብቃቱ መሞገስ? 
በ1990 ዎቹ አካባቢ የሚሰሩ የቪድዮ ፊልሞች ላይ የአንድ ሰው ስም በተደጋጋሚ መታየቱ ሲያስወግዝ አስታውሳለሁ፡፡ ደራሲና ዳይሬክተር ለምን ሆንክ? ደራሲና ተዋናይ መሆንህ ልክ ነው? የሚሉ አፋጣጭ ጥያቄዎችን አስከትሎ ያስተች ነበር፡፡ አስተያየትና ጥያቄው ስራውን ምን ያህል በብቃት ተወጥቶታል? የሚለውን ለመመለስ ያልተሰናዳ ነበር፡፡ አብዛኞቹ በወቅቱ የሚሰጡት ምላሽ የበጀት እጥረት ላይ የሚያሳብብ ነበር፡፡ 
 
የቃለመጠይቅ አድራጊዎቹ ጥያቄ ተዋንያንንም ሲያሳቅቅ ተስተውሏል፡፡
‹‹የራስህን ፊልም /ቲያትር/ መቼ ነው የምትሰራው?››
‹‹አንድ ተዋናይ የራሱን ፊልም /ቲያትር/ መሥራቱ ግድ ነው? ትወናውን በብቃት መተወኑ በቂ አይደለም?›› ብሎ ጥያቄን በጥያቄ የመለሰ አላጋጠመኝም፡፡
‹‹በቅርቡ ፕሮዲዩስ ላደርግ ነው››
‹‹እየፃፍኩ ነበር ለመጨረስ ጊዜ አጣሁ››
‹‹ወደፊት አስቤአለሁ›› ዓይነት ምላሾች ናቸው የሚሰጡት፡፡
ፈሳሽን በሜትር፣ ጠጣርን በሊትር የመለካትን ያህል ተፋልሶ ያለው ይህ ድርጊት ያመጣው ጥፋት አሁን አሁን እየወጡ ባሉ ሥራዎች ላይ እየታየ ነው፡፡ የኤርትራ፣ የሱዳን፣ የናይጄሪያ፣ የማሊ ሙዚቃዎችን ዜማ በመውሰድ አነስተኛ ለውጦችን እያደረጉ ወይም ሙሉ በሙሉ ወስዶ የደራሲው ስም ላይ ስማቸውን የሚጽፉ ድምጻዊያን እጅግ ብዙ የሚባል ቁጥር አላቸው፡፡ የውጪ ፊልሞችን ታሪክ እየገለበጡ በመሥራት አንቱ የተባሉ ዳይሬክተሮች በርካታ ናቸው፡፡ 

መደምደሚያ
አለመቻል ስንፍና አይደለም፡፡ አትችሉም በተባሉ ቁጥር፡- ከድሮ የሐይማኖት መዝሙሮች ዜማ መስረቅ፤ ከዘፈን ስንኝ የፊልም ርዕስ መምረጥ፤ ጉድለትን መሸሸጊያ ይሆናል፡፡ ይልቁንም የማይችሉትን እችላለሁ ብሎ መውተርተር የበለጠ ጥፋት ነው፡፡ ለዚህ ጥፋት ተጠያቂው የአደናነቃችን ባህል መዛባቱ ነው፡፡ የአንድ ጥበበኛን ተግባር መዳኘት የሚገባን በተዛማጅ ጥበባቱ ችሎታ ሳይሆን በራሱ እችላለሁ ብሎ በሰጠን ብቻ መሆን ይገባዋል፡፡ ካልሆነ ግን የበለጠ ተደናቂነትን ለማግኘት የበለጠ የሚደፍሩ አላዋቂዎችን ማፍራታችን ይቀጥላል፡፡ አይመስላችሁም?


© ዘመን እና ጥበብ ህዳር 2010 እትም ላይ የወጣ

No comments:

Post a Comment