Saturday, March 10, 2018

የአእምሮ ንብረት እና ተዛማጅ መብቶች



ሐገራችን አባል ካልሆነችባቸው (ካልፈረመቻቸው)፣ ዓለምአቀፍ አስገዳጅ ስምምነቶች አንዱ የቅጂና ተዛማጅ መብት ነው፡፡ ይህም ለዜጎች ከሚሰጠው ጥቅም በላይ፣ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ የተደረገ ነው፡፡ እየተጠቀምንበት ባለው ኮምፒውተር ላይ ያሉት እያንዳንዳቸው ‹ሶፍትዌሮች›፤ የእጅ ተንቀወሳቃሽ ስልካችን ላይ የሚገኙት እያንዳንዳቸው መተግበሪያዎች ‹አፕሊኬሽኖች›፤ በቅናሽ የዋጋ ተመን እጆቻችን የገቡት በዚያ ምክንያት ነው፡፡ በየኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች በቅጂ (በኮፒ) እየተባዙ ተጠርዘው የተማርንባቸው መጻሕፍት፣ ከዋናው መሸጫቸው ባነሰ ዋጋ የምንገዛቸው በዚያ ሰበብ ነው፡፡ 
ይህ ባይሆን ኖሮ፤ የ‹‹ሶፈትዌሩ›› ዋጋ ከኮምፒውተሮቻችን ተመን (ዋጋ) በላይ፤ የመጻሕፍቱ ደግሞ ተቋሙን ለመገንባት ከሚወጣባቸው ወጪ በላይ በሆነ ነበር፡፡
 
በቅርቡ The economist ይዞት የወጣው ዜና ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ስሙን በየዓለማቱ የሚያውቁት፣ የታዋቂ የፈጣን ምግቦች ‹‹በርገር›› አምራች ድርጅት በአዲስ አበባችን የተመለከቱ ቱሪስቶች ወደ ሱቁ ጎራ ይላሉ፡፡ የሚወዱት የንግድ ስያሜ ‹ብራንድ› አፍሪካ ድረስ ተከትሏቸው በመምጣቱ እየተደሰቱ በአንዱ ስፍራ ተቀምጠው ቀደም ሲል የለመዱትን ‹‹በርገር›› አዘዙ፡፡ ያዘዙትን ሲቀምሱ ግን፣ የበፊቱን ያህል ደስተኞች አልሆኑም፡፡ ጣዕሙ ጉድለት አለበት፡፡ የሚወዱትን ዐይነት አይደለም፡፡ እነኚህ የድርጅቱ ታማኝ ደንበኞች /loyal customers/፣ ሐገራቸው ሲገቡ ‹‹ምነው እንዲህ ጉድ ትሠሩን?›› ብለው ለድርጅቱ አቤቱታቸውን ያሰማሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የከፈታችሁት የ’’በርገር’’ መሸጫ ቤት አይመጥናችሁም፡፡ ጣዕሙም ሆነ ደረጃው፣ የናንተን አይመስልም!›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
የድርጅቱ መልስ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ‹‹እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ሱቅ የለኝም፡፡ ማነው በስሜ እየነገደ ያለ?››
ሱቁ መኖሩ እውነት፤ በአርማው እና በስሙ እየሠራ መሆኑም እውነት ሆኖ ሳለ፣ በዋናው ድርጅት ዕውቅና እና ፈቃድ ያልተከፈተ ‹ሕገወጥ› መሆኑም ያፈጠጠ ሐቅ ነበር፡፡
 
በድርጊቱ የተቆጣው ዓለማቀፍ ካምፓኒ ለክስ ተሰናዳ፡፡ ክሱ እውን እንዲሆን ግን ሐገሪቱ የ World copy write society አባል ትሆን ዘንድ ግድ ነበር፡፡ በዚህ ስሌት የማይዘጋ ካፌ እና ሬስቶራንት፤ የማይከሰስ ሱቅ እና ፈጣን ምግቦች ቤት አይኖርም ለማለት ያስደፍራል፡፡
 
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የቅጂ መብት ህግን አትፈርም እንጂ፤ የራሷ የአእምሮ ጥበቃና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ሕግ አላት፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ የአዕምሮ ንብረትና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ›› ይሰኛል፡፡ አዋጅ ቁጥር 410/96 ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለ 14ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ 
 
በከያኒያኑ ዘንድ ሳይቀር የቅጂ መብትን የተመለከተ የአረዳድ ክፍተት አለ፡፡ የኪነ-ጥበቡ ባለሙያዎች፤ ከሥራዎቻቸው ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም የሚያሳጣቸውን ኮፒ አድርጎ (ቀድቶ)፣ አስመስሎ የሚበትነውን እንጂ፤ በውስጥ ሐሳቦቹ ላይ ያለውን መዘራረፍ (ፕላጃሪዝም) አይመለከቱም፡፡ ዘረፋ ስለመሆኑ ግንዛቤ እንዳላቸውም ያጠራጥራል፡፡ ከአንዳንድ የሙዚቃ አቀናባሪዎች፤ መደበኛ ባልሆነ ጭውውት እንደሰማነው፣ ከውጪ ሙዚቃዎች ላይ የሚገኝን የመሣሪያ አጨዋወት በመምዘዝ፤ ‹‹ይቺን አስገባልኝ?›› የሚሉ ጥቂት አይደሉም፡፡ ‹‹ሙዚቃችንን በዓለምአቀፍ ደረጃ እንዲሰማ የራሴን ድርሻ እወጣለሁ›› ከሚል ከባለራዕይ ሙዚቀኛ የሚጠበቅ ምግባር አይደለም፡፡
 
ወደፊልሙ ዓለም ስናመራም፣ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ታሪክን በሕጋዊ መንገድ፣ በፈቃድ፣ በክፍያና በትክክለኛው መሥመር ባልመጣ የውጭ ሙዚቃ ማጀብ እንግዳ ተግባር አይደለም፡፡ ሙሉ ታሪኩን ገልብጦ ጥቂት መቀባቢያ በማድረግ ማቅረብ የነውር አይደለም፡፡ እየተለመደ የመጣ ብርቱና አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡
 
ከላይ ባነሳነው የቅጂ መብት አዋጅ ቁ410/96 መሠረት የትርጉም ሥራን ጨምሮ፣ ማንኛቸውም ዓይነት (ልቦለድ፣ ግጥም፣ ቴአትር፣ ስነ-ስእል፣ ፎቶግራፍ፣ ሲኒማ) የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራዎች የሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡
 
በጥበባዊ ሥራዎች እርስ በ’ርስ መዘራረፍ ረገድ የሙዚቃው እና የፊልሙ ሠፈር ብዙ ተብሎለታል፡፡ በርካታ ክርክሮችንም አስተናግዷል፡፡ የ’ኔ የመረጃ እጥረት ካልሆነ በቀር፣ መሰል ክርክሮችን ሰምቼባቸው የማላውቀው የጥበብ ዘርፎች ስነ-ስዕልና ቅርጻ-ቅርጽ ናቸው፡፡
በገጣሚ ኤፍሬም ሥዩም የተጻፈው፣ ‹ተዋነይ› የተሰኘው የግዕዝ ቅኔያት ትርጉም ስብስብ መጽሐፍ፣ በሕገወጥ መንገድ በድጋሚ ታትሞ ነበር፡፡ በደራሲው የታተመው መጽሐፍ ከሚሸጥበት ብር 100.00 ባነሰ፣ በብር 70.00 በአደባባይ ሲቸበችብ ተይዟል፡፡
 
የዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) ሐሳቦች እና ትንታኔዎችን አደንቃለሁ የሚል ግለሰብም፣ ከባለቤቱ ፈቃድ ውጪ ‹የዳኛቸው ሐሳቦች› በሚል ርዕስ በመፅሐፍ አሳትሟቸዋል፡፡ 
የመብት ባለቤቶቹ ፍርድቤት ቀርበው፤ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተወሰነባቸውን አነሳን እንጂ ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በሐሜት እና በሰሚ ሰሚ እንዳይሆኑ በሚል ለዛሬ ታልፈዋል፡፡
የሙያው ባለቤቶች ከሚስቷቸው መኻል የትርጉም መጻሕፍትም መብት እንዳላቸው ነው፡፡ Les Miserable የተሰኘው የቪክቶር ሁጎ ረዥም ልቦለድ መጽሐፍ ‹‹ምንዱባን›› እና ‹‹መከረኞቹ›› በሚል፣ በሁለት ተርሚዎች ለንባብ በቅቷል፡፡ 
 
ወጣቶችን በማቅረብ እና በማበረታታት የሚታወቀው ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ (ጋሼ) የዚህ ገፈት ቀማሽ ነው፡፡ በህንዳዊው ፈላስፋና የሥነ-መለኮት መምህር ኦሾ የተጻፈውን ‹‹Sex Money and Power›› የተሰኘ ሥራ፣ እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር በ1997 ‹‹ወሲብ፣ ገንዘብ፣ ሥልጣን›› በሚል ወደ አማርኛ መልሶ ለንባብ አብቅቶታል፡፡ ይኸው መፅሐፍ ለንባብ ከበቃ ከጥቂት ወራት በኋላ፣ በሌላ ተርጓሚ ‹‹ፍካሬ ወሲብ፣ ገንዘብ ወስልጣን›› ተብሎ ቀርቧል፡፡ ጉዳዩ በወቅቱ አነጋጋሪ ነበር፡፡
አንዲሁ ሌላ ታዋቂ ደራሲ፣ ከለታት አንድ ቀን፣ ‹‹ቴሌቪዥን›› ሲመለከት በአጭር ልቦለድ መልክ የፃፈውና የታተመ ታሪክ፣ በድራማ መልክ ሲተወን መመልከቱን አጫውቶኛል፡፡
 
በተመሳሳይ ምልኩ በ1980ዎቹ ገደማ በተርጓሚ ሳሙኤል ማሞ ‹‹በሬ ካራጁ›› በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተመልሶ የነበር የሲድኒ ሼልደን ‹‹›› መጽሐፍ በ2009ዓ.ም ‹‹የደም ውርስ›› በሚል ርዕስ በሌላ ተርጓሚ ቀርቦ ለገበያ ውሏል፡፡ (የዚህ ድርጊት ፈጻሚ ከታች በምናነሳው ሥራ ላይ ተከሳሽ ናቸው፡፡)
የተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ (ጋሼ) ጉዳይ በዚህ አያበቃም፡፡ በ1999ዓ.ም ‹‹የአሁንነት ኃይል›› በሚል ለንባብ ያበቃው የኤከኻርት ቶሌይ መጽሐፍም ‹‹የአሁን ሃይልነት›› በሚል በሌላ ተርጓሚ 2007ዓ.ም ላይ በድጋሚ ተሰርቷል፡፡ የወጥ ሥራው ርዕስ /The Power of now/ የሆነው ተወዳጅ መጽሐፍ ከ35 በላይ በሆኑ ዓለምአቀፍ ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡
 
ተርጓሚ አፈወርቅ ‹‹የነገሩ መደጋገም፣ ብዙ ሰው ግንዛቤው እንደሌለው ስለጠቆመኝ፤ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስጄዋለሁ›› በማለት ስለ ጉዳዩ ያስረዳል፡፡ አክሎም ‹‹የትርጉም ሥራ ቋንቋ በማወቅ ብቻ በዘፈቀደ የሚሠራ አለመሆኑን እና የመጀመሪያው የትርጉም ሕትመት ሕጋዊ ጥበቃ እንደሚደረግለት ሁሉም እንዲያውቅ እፈልጋለሁ›› ይላል፡፡ ‹‹ጥቂት ለውጦች ብቻ እያደረጉ፣ የሰውን ጊዜና ጉልበት፤ ላብና እውቀት፤ ገንዘብ እና ሥራ መዝረፍ አግባብ አይደለም!›› በማለት አቋሙን ይገልጣል፡፡
 
በመዝገብ ቁጥር 162184 ተመዝግቦ፣ በግራ ቀኙ ክርክር ከሚያዝያ 13ቀን 2007ዓ.ም ጀምሮ በክርክር ሒደት ላይ የከረመው ከላይ የተጠቀሰው የተርጓሚ አፈወርቅ ጉዳይ ታህሳስ 12ቀን 2010ዓ.ም ብይን በመስጠት ተጠናቋል፡፡
 
በአዋጅ ቁጥር 410/96 አንቀጽ 4 (1) (ሀ) የትርጉም ሥራ ራሱን ችሎ ጥበቃ የሚደረግለት ስለመሆኑ በግልጽ በተደነገገው መሠረት 3 ተከሳሾች ማለትም ተርጓሚው፣ አሳታሚው እና አታሚው እንደየድርጊታቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተወስኖባቸዋል፡፡ 
ቅጣቶች አስተማሪ የሚሆኑት ጥሩ ተማሪ ሲኖር ነው፡፡ የቅጂ መብቶችን ማክበር ከድርጊቱ ቀጥታ ተዋንያን ማለትም፡- ደራሲያን፣ አሳታሚዎች፣ አከፋፋዮች በአጠቃላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጥበቡ ሥራ ላይ ካሉ ባለድርሻዎች መጀመር አለበት፡፡


© ዘመን እና ጥበብ መጽሔት ------- 2010ዓ.ም እትም ላይ የወጣ


No comments:

Post a Comment