Saturday, March 10, 2018

የኢትዮጵያዊያን የዘር ግንድ ምርመራና ውጤቱ


የዘር ሐረግ ምርመራ /DNA/ የሚታወሰን የቤተሰብ ዝምድናን ለማረጋገጥ ሲከወን ነው፡፡ የአባት እና ልጅነት ክርክሮችን ለመፍታት ሁነኛ መላ አድርገነው ሰንብተናል፡፡ የዘር ሐረግ ምርመራ በአብላጫ ተመራማሪዎች ይሁንታን ተችሮታል፡፡ በበርካታ ሐገሮችም ተቀባይነት አግኝቶ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በአሜሪካ የዜግነት እና የወላጆች መረጃ 99.99 በመቶ ተቀባይነት አለው፡፡ (100% ላለማለት ይመስላል)
ዲ.ኤን.ኤ ምንድነው?
ዲ.ኤን.ኤ (Deoxyribonucleic Acid) በጣም ጥልቅሞልዩኪል” ሆኖ ህይወት ያላቸውን ማናቸውንም ፍጡራን፣ አትክልት እንስሳትባክቴሪያ ወዘተ የዘር-ቀመር (Genetic code) ያዘለ ነው። የአንድ ፍጡር .ኤን. በዚያ ፍጡር ማናቸውም ህዋስ (ሴል) ውስጥ ይገኛል። እያንዳንዱ በምድር ላይ ያለ ፍጡር የራሱ የሆነ ልዩ ባህርይ እንዲኖረውም ያደርጋል። ይህ የሚሆነው ማንኛውም ፍጡር አካሉን የሚገነባባቸው “የፕሮቲን ሞለኪሎችን” አመራረት የሚመራው ዲ.ኤን.ኤ በመሆኑ ነው፡፡
የአንድ ህዋስፕሮቲን” የዚያን ህዋስ ተግባር ይወስናል። .ኤን.ኤ ከወላጅ ወደ ልጅ ይተላለፋል፡፡ ስለሆነም ወላጆችና ልጆች ተቀራራቢ ባህርይ እና መልክ እንዲኖራቸው ያደርጋል። አንድ ዓይነት የማይሆኑበት ምክንያት ልጆች ከሁለቱ ወላጆች ድብልቅ ዲ.ኤን. ስለሚወርሱ ነው።

በዲ.ኤን.ኤ መዋቅር ዙሪያ ህይወት ካላቸው ፍጡራን ሁሉ “ቫይረሶች” ለየት ይላሉ። “ቫይረሶች” በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ገሚሶቹ እንደሌሎች ፍጡራን ዲ.ኤን.ኤ ሲኖራቸው፤ ገሚሶቹ ደግሞ አር.ኤን.ኤ ብቻ ይኖራቸዋል። ዲ.ኤን.ኤ ያላቸው ቫይረሶች ሌሎች ህዋሳትን የሚያጠቁት አስኳሉ ውስጥ በመግባት ሲሆን አር.ኤን.ኤ ብቻ ያላቸው ደግሞ የህዋሱ “ሳይቶፕላዝም” ውስጥ ነው። ኤድስን የሚፈጥረው የ “ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ” ከኋለኞቹ ወገን የሚመደብ ነው።
ዲ.ኤን.ኤ ከሥነ ቅመማ አንጻር ከ “ኑክሊክ አሲድ” (nucleic acid) የተሠራ ሲሆን በመቶ ሚልዮን በሚቆጠሩ የተጣመዱ “ኒኩልቲዲም” ጥምዝ መሰላል ይሰራሉ፡፡ ይህ ጥምዝ መሰላል የዝርያውን ሙሉ መረጃ የያዘ ነው፡፡
መቼ ታወቀ?
በ1869 የኬሚስትሪ ባለሙያ የሆኑት ፍሬድሪክ ሚሸ በዛሬው ጊዜ ዲ.ኤን.ኤ (Deoxyribonucleic Acid) ተብሎ የሚጠራውን የሴል ክፍል አገኙ።
በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ ደግሞ ፊበስ ለቪን የተባሉ የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ በዲ.ኤን.ኤ ውስጥ ያሉ የአንዳንድ የኬሚካል ንጥረ ነገሮችን ቅደም ተከተል እንዲሁም፤ እነዚህ ንጥረ ነገሮች እንደ ሰንሰለት ያለ ሞለኪውል ለመሥራት የሚዋሃዱበትን መንገድ ደረሱበት።
በ1950 ኢርቪን ሻርጋፍ የተባሉ የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ የዲ.ኤን.ኤ አወቃቀር ከአንዱ ፍጡር ወደ ሌላው እንደሚለያይ ተገነዘቡ።
በ1953 የሞለኪውል ባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ጄምስ ዋትሰንና ፍራንሲስ ክሪክ ስለ ሕይወት ባለን ሳይንሳዊ ግንዛቤ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ አንድ ግኝት ይፋ አደረጉ። ዲ.ኤን.ኤ ጥንድ የሆነ ጥምዝ ቅርጽ እንዳለው በምርምር ደረሱበት።
በአብዛኛው በሴሎች እንብርት ውስጥ የሚገኘው ይህ ክር መሰል ንጥረ ነገር፤ የዘር ቀመር (Genetic code) የያዘ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ሴሎቻችን ሕያው ቤተ መጻሕፍት ናቸው ብለን በምሳሌያዊ መንገድ መግለጽ እንችላለን። ይህ አስገራሚ ግኝት በሥነ ሕይወት መስክ አዲስ ዘመን እንዲጠባ አድርጓል፡፡
ተመራማሪዎች ምን አሉ?
ጀርመናዊው የሳይንስ ሊቅ በርንት ኦላፍ ኩፐርስ እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹በሰው ቋንቋ ሲገለጽ፤ የባክቴሪያ ሴል የሚሠራበትን መንገድ የሚገልጸው ሞለኪውሉ ላይ የሰፈረው “ጽሑፍ” (ኮድ) ባለ አንድ ሺህ ገጽ መጽሐፍ ሊወጣው ይችላል።››  ኩፐርስ አክለው ስለሰው ልጅ ህዋስ ሲናገሩ ‹‹አንድ ቤተ መጻሕፍት ሊሞሉ የሚችሉ በሺህ የሚቆጠሩ ጥራዞችን የመያዝ አቅም አለው›› በማለት ተናግረዋል።
የዝግመተ ለውጥ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ሪቻርድ ዶከንዝ ‹‹ዲ.ኤን.ኤ ዝርዝር መረጃ የያዘ ነው፡፡ ይህም ማለት በኬሚካል ኮዶች የተጻፈ መልእክት ሲሆን፤ እያንዳንዱ ፊደል በአንድ ኬሚካል ይወከላል፡፡›› በማለት ጽፈዋል። ‹‹ጉዳዩ ለማመን የሚያዳግት ቢሆንም ኮዱ እኛ በሚገባን መንገድ የተጻፈ እንደሆነ ማወቅ ችለናል›› ሲሉ ገልጸዋል።
ጥናቱ አሁንም አልተጠናቀቀም፡፡ ግኝቱ አበቃለት ተብሎ ፋይሉ አልተዘጋም፡፡ ወደፊትም ባልሰማናቸው ግኝቶች እንደመማለን፡፡ የእድገቱ ደረጃ በፈቀደልን መጠን መረጃዎችን እንሰማለን፡፡
ምርመራና ውጤት
በዘመናችን የዘርሐረግ ምርመራ ከቅርብ ቤተዘመድ ማስተማመኛነት በላይ ነው፡፡ የዘር ግንድን ማወቂያ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከጥንት ቅድመ አያት እና ምንጅላቶች ጀምሮ ያለውን የዘር ሰንሰለት መመልከቻ ሆኗል፡፡ በዓለማቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸው እንደ My heritage DNA, Ancestry ያሉ በርካታ ድርጅቶች ፍላጎት ላለው ሁሉ ምርመራውን ከአንድ መቶ ዶላር ባነሰ ዋጋ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
አገልግሎቱን ማግኘት የፈለገ ማንኛውም ግለሰብ ምዝገባ ማካሔድ፣ ክፍያ መፈጸም፣ ሙሉ ስም እና የትውልድ ዘመን ማስመዝገብ ብቻ በቂው ነው፡፡
ወደ አሜዲካ ለመግባት ጥያቄ ላቀረቡ ሰዎች የሚደረገው ምርመራ ላይ ግን እንደዚህ አይቀልም፡፡ ህጎች አሉት፡፡ ተጠቃሚው አዋቂ ከሆነ አምባሲ ከመድረሱ ከአንድ ሰዓት በፊት፤ ህፃን ከሆነ ከ30 ደቂቃ በፊት ምግብን መመገብ፤ መጠጥ/ ለስላሳ መጠጣት፣ ማስቲካ ማኘክ፣ ከረሜላ መምጠጥ፣ ሊፕስቲክ/ ቻፕስቲክ ተቀብቶ መምጣት የተከለከለ ነው፡፡ የሚጠቡ ህፃናትም ከምርመራ 30ደቂቃ ቀደም ብለውጡት እንዳይጠቡ መደረግ እንዳለበት ያዛል፡፡ ከደም ባንክ የምርመራ ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች ስለመሆናቸውም htpp://www.aabb.org ላይ ገብቶ ማረጋገጥ እንደሚገባ፤ እንዲያ የማይሆን ከሆነ ምርመራው ተቀባይነት እንደማያገኝ ያስጠነቅቃል፡፡

በቀጣዩ ሒደት ግለሰቡ በሰጠው አድራሻ መሠረት የሚላኩለትን የናሙና መቀበያ መሳሪያዎች ይጠብቃል፡፡ ናሙና መቀበያው በፖስታ ይደርሰዋል፡፡ በሚላከው ናሙና መቀበያ መሠረት መመሪያዎችን ተከትሎ ናሙና ይልካል፡፡
የአንድን ሰው የዲ.ኤን.ኤ ምርመራ ለማካሔድ ከሰውነት ፍሎቹ ውስጥ አንዷን ቅንጣት ማግኘት በቂ ነው፡፡ ያቺ የፀጉር፣ የጥፍር ወይም የሌላ አካል ክፍል በላብራቶሪ ውስጥ ገብታ የግለሰቡን ሙሉ ማንነት፣ ምንነት፣ እንዴትነት፣ ከየትነት በዝርዝር ታስረዳለች፡፡ አሁን እያነሳን ያለነውን ምርመራ የምናካሒደው ግን በጉንጭ እና በመንጋጋ መኻል ካለው ለስላሳ የሰውነት ክፍል በምትጠረግ የናሙና ቅንጣት ነው፡፡
ከዚህ ሒደት በኋላ መከታተያ መንገዱ ይቀየራል፡፡ በፖስታ መሆኑ ቀርቶ በኢሜል ይሆናል፡፡ ጉዳይህ እዚህ ደርሷል፤ እዚያ ይገኛል፤ እያለ መረጃ ሲሰጠው ይቆያል፡፡ በመጨረሻም ከአራት እስከ ስድስት ሳምንት የሚጠጋ ጊዜ ፈጅቶ ይደርሳል፡፡ ተጠባቂው ውጤት ኡደቱን ጨርሶ ወደ ለባለቤቱ ይላካል፡፡
ውጤቱ የግለሰቡ 100% DNA ከየት አካባቢ በተገኙ የዘረመል ቅንጣቶች እንደተገነባ ይዘረዝራል፡፡ የዓለም ካርታ አስቀምጦ ከየት ተነስቶ የት እንደገባ፤ ስንት ስንተኛው ከምን ጎሳ የተውጣጣ መሆኑን ያስረዳዋል፡፡
ይህንን ምርመራ ከመላው ዓለም የመጡ በርካታ ሰዎች አድርገውታል፡፡ ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ የጠበቁትን ውጤት አላገኙም፡፡ የኔ የዘርሐረግ ሊኖርበት ይችላል ብለው በፍጹም ከማይጠረጥሩት የዓለም ጥግ የተገኘ ቅመም ውስጣቸው እንዳለ አውቀዋል፡፡ ባነሰ መጠንም ቢሆን ስሙን እና ቋንቋውን ምናልባትም በየትኛው የካርታ አቅጣጫ ላይ እንዳለ ከማያውቁት ሰው ጋር ያላቸውን ዝምድና ተረድተዋል፡፡

ምርመራውን ካከናወኑት ኢትዮጵያውያን መኻል የሁለት ሰዎችን ሙሉ ውጤት በዝርዝር እንመልከት፡፡ የአንድ ወንድ እና የአንድ ሴት፡፡ የተወለዱት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ እነሱም ሆነ ቤተሰቦቻቸው የሌላ ሐገር ዜግነት የለንም ብለው ያምናሉ፡፡ እነሆ በመቶኛ የተከፋፈለው ውጤት፡-


ስም፡- ዮዲት ሰሙ
2.3% ሴራሊዮን
19.9% መኻከለኛው ምስራቅ
23.1% ሶማሊ
54.7% ኢትዮጵያን ጂዊሽ

ስም፡- ብርሐኔ ንጉሴ
0.9% ሶማሌ
1.5% ሴራሊዮን
1.5% ናይጄሪያ
7.8% ማሳይ
17.1% መኻከለኛው ምስራቅ
71.3% ኢትዮጵያ


በሒደቱ ያለፉት ሰዎች ውጤት አስገራሚ ነው፡፡ በተመሳሳይ የዘርሐረግ ምርመራ ውጤታቸውን ያጋሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የማህበረሰብ ትስስር ገጽ በሆነው በዩቱብ ላይ በብዛት ይገኛሉ፡፡ ሁሉም ውጤት ነጋሪዎች ያልጠበቋቸው ሐገር ዜጎች ዘመዶች መሆናቸው አሰደንቋቸዋል፡፡
አቶ ብርሐኔ ተአማኒነቱን አስመልክተው ሲናገሩ ‹‹ይበለልጥ እንዳምነው ያደረገኝ ካርታው ነው›› ይላሉ፡፡ ‹‹ከውጤቱ ጋር የሚላከው ካርታ ኢትዮጵያ ውስጥ መወለዴን ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ የተወለድኩበትን አካባቢና ቀበሌ የሚገልጽ ነው፡፡›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
በቅርቡ በእንግሊዝ ተመራማሪዎች የተደረሰበት እውነትም አነጋጋሪ ነበር፡፡ የመጀመሪያው እንግሊዛዊ ጥቁር መሆኑን የሚያረጋግጡ የአርኪዮሎጂ ማስረጃዎች ተገኝተዋል፡፡
ተማሪዎቻቸውን የዘር ግንድ ምርመራ እነዲያደርጉ ያዘዙት መምህርም ሌላው የአስገራሚው ውጤት ማሳያ ናቸው፡፡ ራሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ተማሪዎቻቸው እንዲመረመሩ ያዘዙት ፕሮፌሰር በመልክ ጥቁር የሆነው ተማሪያቸው የነጭ ዝርያ፤ በመልክ ነጭ የሆነው ተማሪያቸው ደግሞ የጥቁር ዘረመል በደም ዝውውሩ ውስጥ እንዳለ ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡
መደምደሚያ
በቅርቡ በሞት ያጣነው ባለቅኔ ሰሎሞን ደሬሳ በአንድ ወቅት ብሔርን ለተመለከተ ጥያቄ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ ‹‹በሴት አያቶቼ ደጅ ማን እንዳለፈ የሚያውቁት እነሱ ናቸው …›› ነገሩ ዓለማዊነት (Citizen of the world) የሚለውን ሐሳብ ያጎላዋል፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ አንድ ነው፡፡ ሁላችንም ወንድማማቾች ነን የሚለውን ገዢ ሐሳብ ያጎለብተዋል፡፡ ክፍፍልን ወደጎን ብለን፤ የማይጠቅሙ ሐሳቦችን አራግፈን፤ ሰው በመሆን ርዕስ ላይ መግባባት ከቻልን ሌላው ሁሉ ቀላል ይሆናል፡፡


© ዘመን እና ጥበብ መጽሔት ------- 2010ዓ.ም እትም ላይ የወጣ



No comments:

Post a Comment