ዘመናችንን በጥበብ ለመቃኘት የጀመርነውን ጉዞ ስንቀጥል የዛሬ ማረፊያችንን ተወራራሽ ጥበባት ላይ አድርገናል፡፡ በኪነ-ጥበቡ ዓለም አንድን ጥበባዊ ሥራ መነሻ በማድረግ፤ ወይም ሃሳቡን በሌላ ያልታየበት አቅጣጫ በማየት፤ ወይም ሙሉ ስራውን ወስዶ በሌላ የጥበብ ዘውግ መግለጽ እንግዳ ተግባር አይደለም፡፡
‹‹የማዕበል ዋናተኞች›› የተሰኘው የራዲዮ ድራማ ተዘፍኖለታል፡፡ ድርሰቱ የሐይሉ ጸጋዬ ነው፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው ሲሆን በበርካታ ታዳሚያን ልብ ውስጥ ለመግባት የቻለ ነበር፡፡ ድራማው ሲጠናቀቅ የዋናዋን ገጸባህሪ ስም ‹‹ዕፁብ ድንቅ›› ስያሜው በማድረግ ግሩም ዘፈን ተሰርቷል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀነቀነው ጎሳዬ ተስፋዬ ነው፡፡ ቆይቶ በላፎንቴኖችም ተዘፍኗል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማነት መጥቷል፡፡ ተቀባይነቱ በራዲዮ የነበረውን ያህል መሆኑን ግን እጠራጠራለሁ፡፡
ከመጻህፍት ታሪኮች በመነሳትም ፊልሞች ተዘጋጅተዋል፡፡ በአዳም ረታ የተፃፈውን ‹ያንገት ጌጡ› የተሰኘ አጭር ልብወለድ በፊልም ተመልክተነዋል፡፡ ‹ቃል ኪዳን› የተሰኘው ረዥም ልብ ወለድ ታሪክ በፊልም ተሰርቶ በሲኒማቤቶች ታይቷል፡፡ ‹ሎሚ ሽታ› በብዕር እና ወረቀት በአዳምረታ ተፅፎ በመፅሐፍ ስናነበው፤ በብርሃን እና ቀለም በኢሳያስ ግዛው ተጽፎ ደግሞ በሲኒማቤቶች ሸራ ታድመነዋል፡፡ ተቀባይነቱም መጽሐፉን በወደዱት ሰዎች ሳይቀር ያስጨበጨበ ነበር፡፡ ይህ ሁል ጊዜ አይሰምርም፡፡ ‹የነገን አልወልድም› በኢሳያስ ግዛው ዳይሬክቲንግ ወደ ፊልምነት የመጣ በገነነ መኩሪያ ‹ኢህአፓ እና ስፖርት› መጽሐፍ ላይ ተመስርቶ ለተመልካች የተበረከተ ሥራ ነው፡፡
‹ሎሚ ሽታ› እና ‹የነገን አልወልድም› የመጽሐፉን መንፈስ በትክክል ወደፊልም ማጋባት የቻሉ ናቸው፡፡ አንድ የመጽሐፍ ታሪክ እንዴት ባለ መላ ወደፊልምነት እንደሚቀዳ ያስተማሩ ስራዎች ናቸው፡፡ በዓመታዊ ውድድሮች ከ አንድ በላይ ሽልማቶችን መውሰድ ችለዋል፡፡
‹ውበትን ፍለጋ› የተሰኘው የጌትነት እንየው ቲያትር በመድረክ ለ 3ዓመታት ያህል ታይቶ በፊልም ልናየው የታደልነው ድንቅ ሥራ ነው፡፡ ከመድረክ የወረደው በተመልካች እጦት ሳይሆን ዋና ተዋናይዋ ሙሏለም ታደሰ በመድረኩ ብርሐን ሳቢያ ዓይኗን በመታመሟ ነው፡፡ የቲያትር ግርማው አብሮት ባይኖርም ለዛውን እንደጠበቀ ለስክሪን በቅቷል፡፡
ተወዳጅ መፃህፍት ወደ ዘፈን የተቀየሩበት አጋጣሚም በርካታ ነው፡፡ የፍቅረማርቆስ ደስታ ‹አቻሜ› ላይ ተመስርቶ የተሰራው የፍቅራዲስ ነቅአጥበብ ‹ያሙ› አንዱ ነው፡፡
ጠንቃቃስ ነበር - ተምሮስ ነበር
ወደቀ እንጂ ድንገት - አዳልጦት ፍቅር
የግጥም እና ዜማው ድርሰት የጉምቱው ባለሙያ አበበ ብርሃኔ ነው፡፡ ሙሉውን የመጽሐፉን ታሪክ በጥቂት መስመር ስንኞች ጥንቅቅ አድጎ ገልጾታል፡፡ ከገጸባህርያቱ ስሜት ጋር እያጫወተ፣ በሃሳባቸው እያስተከዘ ይበልጥ ወደ እውናዊው ዓለም ያቀርባቸዋል፡፡ ለመጽሐፉ ሌላ ህይወት የመቀጠል አቅም ዓለው፡፡ ያላነበበውን ሰው እንዲያነበው የመገፋፋት ታላቅ ሀይልም ጭምር . . .
ሊቁን እንደማያውቅ ያስቆጥራል ፍቅር
ከግር ስር ሲያሳድር
አባ ኢላ ያሙ
አባ ጉያ ያሙ
‹ሽልንጌን› በተሠኘው የተባባሪ ፐሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ አጭር ልብወለድ ላይ በመመስረትም ዘፈን ተሠርቷል፡፡ የግጥምና ዜማ ደራሲውም ዘፋኙም አንዳለ አድምቄ ነው፡፡ በአጭር ልብወለዱ የተፃፈውን ታሪክ በጥሩ ገለጻ በዘፈን ግጥሞቹ አስቀምጦታል፡፡ ያ ብቻውን ግን አልበቃውም፡፡ ጉዳዩን ሽልንግ ከተረሳባት ማንጎ ሻጭ በላይ አሳድጎ ሀገራዊ አጀንዳ በማድረግ ያቀርበዋል፡፡
ሽልንጌን ሽልንጌን እያለች
ያላደላት ደሃ ወድቃለች . . . ብሎ ታሪኩን ካስቃኘን በኋላ
ዓለም ለብዙዎች ብትሆንም ፈተና
ሊደጎም ይገባል ድሀው እንዲል ቀና . . . በማለት የመፍትሄ አቅጣጫ ያመላክታል፡፡
ለጥቂቶች ድሎት እልፎች ሲንገላቱ
ልብ እንዳሳዘነ ያበቃል ትእይንቱ . . . በማለት ይደመድመዋል፡፡
የዓለማየው ሂርጶ ‹ዴዝዴሞና› የተሸኘ ዘፈንም አለ፡፡ ታሪኩን እንደ ምሳሌ በማንሳት ነባራዊውን ዓለም ለማስቃኘት ይሞክራል፡፡
ንፁህ ፍቅር መሐል የሚገባ ሰርጎ
ጦሰኛ መሐረብ በጉያው ሸሽጎ
አቤት ይቺ ምድር ስንት አላት ኢያጎ
ቲያትሩ የሚወሳቸውን የታሪክ ክስተቶች ለራሱ የቀዳ፣ ተመሳሳይ ስህተት የሰራ እና ጥፋቱን ያመነ፣ ኦቴሎ ገጸባሕሪ ፈጥሮ ያጫውተናል፡፡
ይቅር በይኝ ባክሽ ማሪኝ ዴዝዴሞና
የኔዋ ዴዝዴሞና … እያለ
‹ሞናሊዛ› የተሰኘችው የዳቬንቺ ስዕልም በዘፈኖቻችን ዝርዝር ውስጥ በዘፋኞቻችን ጉሮሮ አልፋ እናገኛታለን፡፡
ቃላቶች ያጥሩኛል ምን ብዬ ላድንቅሺ
እንዲያው በደፈናው - ሚናሊዛዬ ነሺ
ልሳነ ወርቁ አቀንቃኝ ጥላሁን ገሠሠ ሞናሊዛን የተጠቀመባት ለውበት ማንፀሪያነት ነው፡፡ የሚለው ሲጠፋው፣ መግለጫ ግራ ሲገባው የመዘዛት የደምግባት ገላጭ ቋንቋ
ሰዓሊው ቡሩሹን ነክሮት በቀለሙ
ብራና ወጥሮ አንቺን ከማለሙ
በቀለማት መሐል ድንገት ተገኘሺ
አተኩሮ ሲያይሽ ለካ ሞናሊዛ ነሺ
ቴዎድሮስ ካሳሁን ደግሞ ለራሷ ዘፈነላት፡፡ በሸራ ላይ ለምትኖረው የሰዓሊው ፍጥረት፡፡
የሮማ ዋርካ የጥበብ ታዛ
ሞናሊዛ … ብሎ እሷነቷን ብቻ አወደሰ
በሳል ግጥሞችን በማቀንቀን የሚታወቀው ድምፃዊ እና የዜማ ደራሲ ሚካኤል በላይነህም በዚህ መስመር ላይ በብዛት ተመላልሷል፡፡ ‹አፋጀሺኝ› በተሰኘው የዮፍታሔ ንጉሴ ቲያትር መነሻነት የሰራው አንድ ዘፈን አለው፡፡ ‹አፋጀሺኝ›
የገብረክርስቶስን ‹ስወድሽ› የተሰኘ ስነ ግጥም ለዘፈን እንዲሆን አሳጥሮ እና አሳምሮ፣ ውብ ዜማ አልብሶ ዘፍኖታል፡፡
የትዕግስት ማሞ የግጥም መድበል የሆነው ‹ቁጭት› አብዛኛዎቹ የግጥሙ ሐሳቦች በሸራ ላይ አርፈው በመጽሐፉ ምርቃት ወቅት ለዕይታ በቅተዋል፡፡ የቴዎድሮስ ካሣሁን ‹ጥቁር ሰው› የሙዚቃ ቪዲዮ በሚመረቅበት ጊዜ አብዛኛዎቹ ሐሳቦች በሰዓሊያን ብሩሽ ተነድፈው ተመልክተናቸዋል፡፡
አንዱ በአንዱ እየተነሳ፣ አንዱ በሌላው እየተወሳ መቀጠሉ በድህረ ዘመናዊው /Post Modern/ የኪነጥበብ ዘውግ የተለመደ ነው፡፡ ገፀባህርያቱ መልካቸውን እንዲቀይሩ፣ የቀደመ ተፈጥሯቸውን ትተው ዓዲስ ማንነት እንዲይዙ በማድረግ ለተደራሲው ሌላ የሐሳብ መንገድ ያቀብላሉ፡፡
ከአንድ በላይ በሆኑ ከያኒያን፣ ከአንድ በላይ በሆነ የኪነጥበብ ዘርፍ ተደጋግሞ የተወሳ መጽሐፍ ደግሞ አለ፡፡ ‹ፍቅር እስከ መቃብር›፤ ይህ ዘመን አይሽሬ ልብወለድ ታሪክ በቲያትር፣ በዘፈን፣ በሌሎች ልብወለድ ታሪኮች ላይ ወዘተ . . .ተነካክቷል፡፡ እነማን አንዴት ባለ መልክ ገለጹት? የሚለውን ጠለቅ ባለ ዕይታ የመተንተን ሐሳባችንን በይደር አቆይተን፤ በወፍ በረር የቃኘነውን ከመግቢያ ቆጥረን የዛሬውን እናሳርግ፡፡ ሠላም!
© ዘመን እና ጥበብ መጽሔት ሰኔ 2009
No comments:
Post a Comment