ሐገራችን
ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ ቀድመን በትንሽ በትንሹ እያጠራቀምን ያመጣናቸው ችግሮች ተራራ አክለው ተጋፍጠውናል፡፡ ሁላችንም
የየድርሻችንን በቀላሉ ያዋጣንበት የስህተት ማጥ በቀላሉ ልንቋቋመው እንዳንችል ሆኗል፡፡ ዓለማቀፍ ሚድያዎች ሳይቀሩ መስቀለኛ መንገድ
ላይ መቆማችንን እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ሁኔታችንን ታዝቦ፤ ድርጊታችንን ተመልክቶ፤ ነጋችንን ተንብዮ፤ አለመፍራት አይቻልም፡፡
እውቁ
ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን በደርግ ውድቀት ማግስት እና በኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ለእይታ ባበቃው ቲያትሩ
እንዳለው፤ ‹‹ሀ ሁ ወይም ፐ ፑ›› የምንልበት ቀይ መስመር ላይ ነን፡፡ አልፋ ብለን፣ ለዚህ ችግር የዳረጉንን እንከኖች ነቅሰን፣
አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት፤ ወይም ኦሜጋ ብለን፣ የነበረውን እንዳልነበረ የምናፈራርስበት ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡
በታሪካችን
መንግስት እና ሕዝብ አለመግባባታቸው ብርቅ አይደለም፡፡ አለቃና ምንዝር መቃቃራቸው ልዩ ክስተት አይደለም፡፡ ገዢ እና ተገዢ መቆራቆዛቸው
እንደ ተአምር አይታይም፡፡ ቀድሞም የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ የተደራጀም ያልተደራጀም፤ ፓርቲ የመሰረተም ያልመሰረተም፤
የገባውም ግራ የገባውም ሐይል ሥልጣን ላይ ከሚገኘው መንግስት ጋር ተጣልቶ ያውቃል፡፡ አለመስማማት ፈጥሮ፤ መቃቃር አበጅቶ ያውቃል፡፡
ፍላጎት ባደገ ቁጥር ለውጥን መናፈቅ ጤነኛ ነገር ነው፡፡ ሁኔታው የለውጥ እንቅስቃሴ የሚወልደው ነውና ባንፈልገውም ይከሰታል፡፡
ተከስቷልም፡፡
በሐገራችን ከበቅርብ ዓመታት
ወዲህ እየተመለከትን የምንገኘውን የመሰለ ድርጊት ግን የኛን አይመስልም፡፡ በእያንዳንዱ ስነ-ቃላችን፤ በኪነ-ጥበብ ውጤቶቻችን፤
በየቤተ-እምነቶቻችን፤ በትምህርታችን፣ በጉራ እና በንግግራችን፤ ራሳችንን ለዓለም በምንገልጥባቸው መንገዶች ሁሉ የሌለ ነው፡፡ ያልነበረ
ነው፡፡ አዲስ ነው፡፡
በአንድ ክልል የሚኖሩ የሌላ
ቋንቋ ተናጋሪዎች ከክልሉ መባረራቸውን ሰምተናል፡፡ አንድ ሁለት አይደለም፡፡ አስር ሃያም አይደለም፡፡ ከሰባት መቶ ሺህ በላይ፤
የሌላ ጎሳ አባላት በመሆናቸው
ብቻ ክቡር ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች መኖራቸውን ሰምተናል፡፡ አንድ አካባቢ አይደለም በበርካታ አካባቢዎች፤ የአንድ ጎሳ ብቻ አይደለም
ከልዩ ልዩ ጎሳ፤
ምን እየሆንን ነው? ማን ሆነናል?
ያስብላል፡፡
በስጋ የማይዛመደንን አጥምቀን
ወደ ማህበረሰቡ የምንቀላቅል የ‹ጸማይ› (ጸማኮ) ትውልዶች ምን ሆነናል? ያልወለድነውን ልጅ በጉዲፈቻ ከልጃችን በላይ የምናሳድግ
ሕዝቦች ምን ሆነናል? ለቃል ለመታመን ሕይወታችንን የምንሰጥ ባለማተቦች ምን ነካን? በእምነት የማይመስለንን አግብተን በፍቅር የኖርን
ሰዎች ምን አገኘን? አብሮ ለመብላት ከፍያለ ትርጉም የምንሰጥ ማሕበራዊያን ምን መጣብን? ‹‹ብልህ ከሰው ይማራል›› ብለን የምንተርት
እኛ፤ የሌሎች ዓለማትን ሁናቴ አስተውለን ስለምን ይህን ማውገዝ ተሳነን? በደምስሮቹ ከአንድ ብሔር ብቻ የሆነ ደም የሚዘዋወርበት
ንፁህ ዘር (ያልተቀላቀለ) እንደሌለ እየታወቀ፤ ተዋልደን፣ ተዋደን፣ ተጋብተን፣ እንደኖርን እየታወቀ፤ ሱዳንን እንደመሰሉ ሐገራት
ደቡቡ ከሰሜኑ የማየጋባበት፤ ሕንድን እምደመሰሉ ሐገራት ከጎሳ ውጭ ማፍቀር የሚከለከልበት እንዳልሆንን እየታወቀ፤... እየሆንን
እንዳለነው ለምን ሆንን?
በርግጥ የብሔሮች እኩልነት ጥያቄ
ውስጥ የገባበት ዘመን ነው፡፡ ሙስና ከመቼውም ጊዜ በላይ ተንሰራፍቷል፡፡ ፍትህ ተጓድሏል፡፡ ፍርድ ተዛብቷል፡፡ ብዙ ልክ ያልሆኑ
ነገሮች አሉ፡፡ በርካታ አለመመቻቸቶች አሉ፡፡ እጅግ የበዙ ስህተቶች አሉ፡፡ መፍትሔው ግን ሕዝብ በሕዝብ ላይ መነሳቱ አይደለም፡፡
የማይሽር ጠባሳ ማበጀት አይደለም፡፡
መንግስታት ያልፋሉ፤ አገዛዞች
ይለወጣሉ፤ ባለስልጣናት ይቀያየራሉ፤ ሕዝብ ግን አይቀየርም፡፡ ስህተት በስህተት አይታረምም፡፡ እድፍ በቆሻሻ አይጠራም፡፡ ወደምናውቀው፤
ወደምንታወቅበት ኢትዮጵያዊ ማንነታችን እንመለስ!
No comments:
Post a Comment