Wednesday, August 12, 2015

የማስታወቂያዎቻችን ነገር

‹ሱዛን ፎርማን› የተባሉ ጸሐፊ ‹‹The Media of Advertising›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ ማስታወቂያ አጀማመር ሲገልጹ 

‹‹ማስታወቂያ ስረ መሰረቱ በጥንታዊት ሮም መኳንንቶችን ለማስደሰት የሚደረጉ ድብድቦች /Gladiators/ በታላላቅ አደባባዮች የሚካሄዱ መሆኑን የሚያስተዋውቁ፤ በመካከለኛው ዘመን የሞት ፍርድ በአደባባይ የሚፈፀም መሆኑን የሚያመላክቱ፤ በአሜሪካ ጠረፍ በትልቁ ተፅፈው የሚንጠለጠሉ የ ’ወንጀለኛ ይፈለጋል’ ማሳሰቢያዎች ናቸው፡፡›› ይላሉ፡፡

በግብጽ በ 3200 ዓ.ዓ አካባቢ በተሰሩ የማምለኪያ ህንፃዎች ላይ ማንኛው ንጉስ እንዳስገነባው የሚጠቁሙት ጽሁፎች ከማስታወቂያ ይመደባሉ የሚሉ ምሁራንም አሉ፡፡

በታሪክ የመጀመሪያው ተብሎ በ (Encyclopedia Britanica,Vol 1 ,180) የተመዘገበው የጽሁፍ ማስታወቂያ 

‹‹ሼም የተባለው ባሪያ ሃፑ ከተሰኘው አሳዳሪ ተሰውሯል፡፡ ሃፑ የቴቢስ መልካም ዜጎች ሁሉ ይህን የጠፋ ባሪያ ቢመልሱለት ይወዳል፡፡ ባሪያው ባለቡናማ ዓይን ነው፡፡ ያለበትን አካባቢ ዜና ላመጣ ግማሽ የወርቅ ሳንቲም ይሰጠዋል፡፡ ሼምን ወደአሳዳሪው ለሚመልስ ደግሞ እንደፍላጎቱ ልብስ የሚደሸመንለት ሲሆን ሙሉ የወርቅ ሳንቲምም ይሰጠዋል፡፡››

የሚል ሲሆን ከ 3ሺህ ዓመት በፊት በፓፒረስ ላይ የተጻፈ መሆኑ ተገልጧዋል፡፡
በዘመናዊና በተደራጀ መልኩ ከቀረቡት ማስታወቂያዎች በፊት ግን ሰዎች ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ ማስታወቂያቸውን ይናገራሉ፡፡ በሐገራችንም ይህ ተግባር የተለመደ ነበር
 ‹‹አዋጅ አዋጅ አዋጅ
የደበሎ ቅዳጅ
ያልሰማህ ስማ
የሰማህ ላልሰሙ አሰማ›› 
በሚሉ ቃላት በነጋሪት ታጅቦ ህዝባዊ እና መንግስታዊ መልእክቶች እና ትእዛዞች እንዲሁም ማስታወቂያዎች ተላልፈዋል፡፡
ምልክቶችም አይነተኛ ማስታወቂያዎች (የንግድ ምልክቶች) በመሆን አገልግለዋል፡፡አሁን ያለንበት ዘመን ድረስ እየተጠቀምንበት ያለነው ከመሬት ላይ በተተከለ እንጨት ላይ የተንጠለጠለ ጣሳ ከበሩ ደጃፍ ላይ መስቀል አንዱ ምሳሌ ነው፡፡ በጥንታዊት አቴንስ በሱቆቻቸው በር ላይ ሱቅነትን የሚገልፅ ስዕል ይሰቅሉ ነበር፡፡

በ1450ዓ.ም ጉተንበርግ ማተሚያ ማሽንን ከፈለሰፈ በኋላ ጽሁፍን በብዙ ቅጂ ማውጣት መቻሉ በቃል ይተላለፉ የነበሩትን መልዕክቶች በጽሁፍ በማስፈር ለማስታወቂያው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ 

የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ የራዲዮ መገኘት፣ የቴሌቪዥን መምጣት . . . እነዚህ ሁሉ ታላላቅ የዓለም ቴክኖሎጂያዊ ለውጦች እየተቀባበሉ ለማስታወቂያው እድገት የራሳቸውን ድርሻ እያበረከቱ ኖረዋል፡፡ እነ ኮንፒውተር ኢንተርኔት እና ተንቀሳቃሽ ስልኮችም እድገቱን በከፍተኛ መጠን ያናሩት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው፡፡
በሐገራችንም ከመጀመሪያው ጋዜጣ ‹‹አዕምሮ›› እስከ 65 ዓመት በላይ ዘመን እስካስቆጠረው ‹‹አዲስ ዘመን›› በርካታ ማስታወቂያዎች ተጽፈዋል፡፡ እ.ኢ.አ በ 1928ዓ.ም ስርጭቱን ከጀመረው የኢትዮጵያ ራዲዮ እስከ 1957 ዓ.ም ለእይታ የበቃው ‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን› ብሎም አዳዲሶቹ ኤፍ ኤም ጣቢያዎች ድረስ ማስታወቂያ ይታያል ይደመጣል፡፡
ዳዲሽ ሼዝ የተባሉ የማስታወቂያ ባለሙያ እንደሚያስቀምጡት ማስታወቂያ 4 ዓላማዎች አሉት
ማሳሰብ /Precipation/:- ይህ የማስታወቂያ ዓይነት ደንበኞች ሊጠቀሙ (ሊገለገሉ) አስበውት የማያውቁትን ምርት ለማስተዋወቅ የምንጠቀምበት ነው፡፡ ዋና አላማው ስለምርቱ ምንነት፣ ባህርያት የት እንደሚገኝ ማሳወቅ ነው፡፡
ማሳመን/Persuation/፡- ተጠቃሚዎች ምርቱን ወደመግዛት አገልግሎቱን ወደመጠቀም እንዲሸጋገሩ ሊያሳምኑ የሚችሉ ቃላትን እና ስሜትን የሚነኩ ቴክኒኮችን በመጠቀም የሚዘጋጅ ነው፡፡
መገፋፋት /Reinforcement/፡- ከነባሮቹ ምርጫዎች መሀል ምርቱን የሚያስመርጠውን ነጥብ በማንሳት እና ጠቀሜታውን በማጉላት ላይ አተኩሮ ይዘጋጃል፡፡
ማስታወስ /Reminder/፡- ይህ አይነቱ ማስታወቂያ ዓላማው የምርቱን መለዮ /Brand/ ማስታወስ ነው፡፡  
ማስታወቂያ ጥበብ ነው ወይንስ ሳይንስ የሚለው ክርክርም ገና አሸናፊው ይልለየ በሂደት ላይ ያለ ያልተቋጨ ሙግት ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸውን ማሳመኛ ለማቅረብ ይሞክራሉ ጋዜጠኛ ዳንኤል ብርሃኑ ‹‹የማስታወቂያ መሰረታዊ ሃሳቦች›› በሚለው መጽሀፉ  ‹‹ማስታወቂያ ሳይንስ አይደለም፡፡ ማሳመኛ ነው፡፡ ማሳመን ደግሞ ጥበብ ነው፡፡›› ሲል ዊልያም በርናባስን ጠቅሶ አስፍሯል፡፡
እዚህ ጋር አፍታ ወስደን ለማሰላሰል እንሞክር፡፡ ያየናቸውን፣ የሰማናቸውን፣ ያነበብናቸውን …ማስታወቂያዎች በህሊናችን እናመላልስ፡፡ በርግጥ ጥበብን የተላበሱ አሳማኝ ናቸውን? በምሳሌ እና በማስረጃ እየተነተንን ለመዳደስ እንሞክር፡፡

የሚድያውን ባህሪ ያልተረዱ ማስታወቂያዎች
1)በባለጥቁር እና ነጭ ቀለም በታተመ ጋዜጣ፣ መጽሄት ወይም ሌላ የህትመት ውጤት ላይ ታትሞ ያየነውን ማስታወቂያ በባለ ቀመም ህትመት ባለቸው ብሮሸሮች ላይ ወይም በከተማ መሀል ላይ ባለ አደባባይ ማየት እጅግ የተለመደ ስህተት ነው፡፡
ቀለማት መልእክትን፣ ስሜትን ያስተላልፋሉ፡፡ ድባብን፣ ሁኔታን ይገልጻሉ፡፡ ብለን የምናምን ከሆነ ለተፈለገው ዓላማ የተዘጋጀ ማስታወቂያ ሊኖረን ግድ ነው፡፡ ለ ‘A4’ ወረቀት ተሰናድቶ ስናየው ማራኪ እና መልእክቱንም በተገቢው መንገድ ያስተላለፈ ማስታወቂያ እጅግ ግዙፍ በሆነ ቢልቦርድ ላይ ሲቀመጥ ሳቢነቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ በውስጡ ያሉት ምስሎች አለመጠን ይገዝፋሉ፡፡ በባለ ሙሉ ቀለም ሆኖ አምሮ የታየን ማስታወቂያም ጥቁር እና ነጭ ቀለም ብቻ ሲሆን መልእክቱን ሙሉ ለሙሉ ሊያጣ የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ጋዜጣ እና መጽሄት ላይ ወጥተው ለማንበብ አበሳችንን ያየንባቸው ማስታወቂያዎችን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በአብዛኛው የሀገርኛ ፊልም ማስታወቂያዎች የዚህ ችግር ሰለባዎች ናቸው፡፡ ከታሰቡበት ቀለም ውጪ በመታተማቸው  ምክንያት ከዋናው ርዕስ በቀር አብዛኛው ጽሁፋቸው የማይነበብ በጋዜጣ እና በመጽሄት የውስጥ ገፅ የታተሙ የፊልም ማስታወቂያዎች ቁጥር ከጥቂት ያልፋል፡፡
2) ለቴሌቪዥን አገልግሎት ተብለው የተሰሩ ማስታወቂያዎችን በቀጥታ ለሬዲዮ መጠቀም ሌላው ችግር ነው፡፡ ምስል እያገዘው ከእይታ ጋር ተዳምሮ የሚቀርብን መልእክት በድምጽ ብቻ ለሚተላለፍ ሚዲያ ስናመጣው የሚያጎድለው ነገር በርካታ ነው፡፡ በቴሊቪዥን የተላለፈን የመኪና ማስታወቂያ በሬዲዮ ሲለቁት አስተዋዋቂው ‹‹አሁን ለዚህ 300ሺ ብር አያንሰውም?›› ሲለን ‹‹ለየቱ?›› ማለታችን ተፈጥሯዊ ነው፡፡ አላየነውማ! የምስል እና ድምጽ ቅንብር ማስታወቂያው ሬዲዮ ላይ ሲመጣ ምንም ጉድለት አያመጣም ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ ደግሞ ቀድሞውኑ ቴሌቪዥን ላይ መቅረብ አልነበረበትም ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል፡፡ የማሳየት በዓይን የመናገር እና የማስደመጥ በጆሮ የመናገር ሚድያዎች ናቸውና

ያልተገባ ንፅፅር
ለዚህ ርዕስ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ማስታወቂያ የሚታየው በቴሌቺዥን ነው፡፡ ኳስ በመጫወት ላይ ሳለ በዘግናኝ ጉኔታ ከጉልበቱ በታች ያለው አካሉ የሚሰበር የእግርኳስ ተጫዋች ያሳየናል፡፡ ምስሉ በብዙዎች የዕጅ ስልክ ላይ የሚገኝ የተሰለቸ ከመሆኑም በተጨማሪ ጣቢያው በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ያሉ ሰዎች የሚያዩት ነውና እንዲተላለፍ መፈቀዱ አስገራሚ ነው፡፡ ያንን አጭር ግን ዘግናኝ ስብራት ተመልክተን ስናበቃ ምን ነክቶት እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ አንድ ብርጭቆ ሲሰበር ይታያል፡፡ ቀጥሎ የመልእክቱ ነጋሪ ባማረ ድምጹ እንዲህ ይለናል፡፡
‹‹ብርጭቆ ቢሰበር ይጣሉት፡፡ እግርዎ ቢሰበር ግን ወደኛ ይምጡ፡፡ ምናምን የአጥንት ህክምና ክሊኒክ››
ጉድ በሉ እንግዲህ ይሄንን መካሪ! እግሬ ቢሰበር እንደብርጭቆው ከቤት አውጥቼ እንዳልወረውረው ሰግቶ ወደሱ እንድመጣ ሲነግረኝ፤ ሆስፒታሉን እንድጠቀም ሲያግባባኝ፡፡ እግሩ ተሰብሮበት የጣለ ሰው አለ እንዴ? ማናልባት ይህ ባለሙያ ‹‹ስብርብር አለልሽ ጉልበቴ›› የሚለው የሸዋንዳኝ ዘፈን ላይ ብርጭቆ ‘’ከሽ’’ ሲል ያሰማን አቀናባሪ ይሆን እንዴ? ወይስ ዘፈኑን ሲሰማ ተጽእኖ አሳድሮበት ይሆን? 

ግጥም በግድ
እነዚህ ማስታወቂያ ነጋሪዎች /አስነጋሪዎች አላልኩም/ ግጥም ይወዳሉ፡፡ ግን አይችሉም፡፡ መውደድ እና መቻል እንደሚለያይ ደግሞ አልተረዱም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ይሉናል፡፡
ቤኮ
   ምርጥ ነውኮ

‹‹ነው›› የሚለውን ቃል ተከትላ የመጣችው ኮ ጉሮሮን ከማዳለጧ በተጨማሪ እቃው ቤኮ መሆኑ ቀርቶ ‹ቤቃ› ቢሆን በ ‹በቃ› ከመተካት አታመልጥም ‹‹ምርጥ ነው በቃ!›› በመባል
በወንድና በሴት የበባህል አልባሳቶች
እምር ብሎ ከች
ይህም በግድ በግጥም ለማስተዋወቅ ከመጓጓት የመጣ በመሆኑ ለባለሙያዎቻችን ሳይገጥሙ ማስተዋወቅ እንደሚቻል ምክር ቢጤ ጣል አርገን ወደሌላው እንለፍ

የሙያዊ ቃላት ናዳ
በዚህ ዘርፍ በቀዳሚነት የሚሰለፉት የጥርስ ህክምና ክሊኒኮች ናቸው፡፡ ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ‹ኦርቶዴንቲክ አፕሊያንስ› ‹ማግዝለሪ አፕሊያንስ› እያሉ እንኳን እኛ እነሱም ባልገባቸው ነገር ያደርቁናል፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ በተለይ እሁድ ከሰዓት በኋላ በኢቢሲ ሁሉም የጥርስ ማስታወቂያዎች በተከታታይ ነው የሚታዩት፡፡ ‘’ምን ለውጥ አለው የአንድ ሰው ናቸው:: በተለያየ ስም መጡ እንጂ፤’’ ብለውም እንደሆን እንጃ፡፡

መልእክቱ የሚነገረው ከተራ ሰው እስከ ተራ ያልሆነ ሰው ድረስ ነውና የግድ እነሱን ለመረዳት ‹‹ምን አለ?›› ‹‹ምን ማለቱ ነው?›› መባባል አይኖርብንም የማስታወቂያ ዓላማ ግራ ማጋባት ዓይደለምና እና ኳስ በመሬት ቢያደርጉ ከኛ ይልቅ እነርሱ ይጠቀማሉ፡፡ 

አልተገናኝቶ
በአልተገናኝቶ ቡድን ውስጥ የሚካተቱት የማስታወቂያ ዓይነቶች የሚያስተዋቀወቁት እና የሚተዋወቀው ነገር የተምታታባቸው ናቸው፡፡ እንደመግቢያ የሚጠቀሙበት ዓረፍተነገር ዋናውን ሀሳብ ከያዘው ዓረፍተነገር ጋር የማይግባቡ፣ ፈጽሞ የተፋለሱ ይሆናሉ፡፡ ወይም ምርቱ ጥሩ እንደሆነ የሚጠቅሱት ምሳሌ ከነገሩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖረውም፡፡ በምሳሌ እንመልከተው፡
Ø  ቴሌቪዥንን ለማስተዋወቅ በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ማስታወቂያ ነው፡፡ የቴሌቪዥኑን ስም ካስተዋቀወን በኋላ ‹‹የነ ነይማር እስፖንሰር›› ይለናል፡፡ እንድንገዛው የሚገፋን እነ ነይማርን ስፖንሰር ማድረጉን ተገን በማድረግ ነው፡፡ ለገዢው የሚጠቅመው ትክክለኛ መረጃ የቱ ነው? ዋስትና ያለው መሆኑ፣ ጥራት ያለው መሆኑ፣ የተሰራበት ጥሬ እቃ ወ.ዘ.ተ ነው ወይስ እነ ነይማር . . .? የቴሌዢዥን አምራች ድርጅቱ ስፖንሰር አድራጊ ግለሰብ እና ቡድንን መጥራት ከምርቱ ጥራት ጋር ምን ያገናኘዋል? ዋናው ተዋዋቂ የተከፈለበት ቴሌቪዥኑ ነው? ክለቡ ነው? ተጫዋቹ ነው? እንደው ምን አገናኛቸው? 

Ø  የሚተዋወቀው ድርጅት የጥርስ ህክምና ክሊኒክ ነው፡፡ የማሽኖቹን እና የህክምናውን አይነት ከዘረዘረ በኋላ ለየት የሚያደርገን ነገር ብሎ
‹‹ለየት የሚያደርገን ነገር የታካሚውን ታማሚ ጥርስ ቀርጸን በሲዲ ኮቲ መስጠታችን ነው››ይላል፡፡
 አሁን ማን ይሙት የበሰበሰ ጥርሱ ከምላሱ እና ከመንጋጋው ጋር የሰሩትን ተዓምራዊ ፊልም ለመመልከት የሚጓጓ የዋህ በዚህ ዘመን አለ? ከታካሚው የትርስ ጤንተት ጋር በቀጥታ የሚገናኝበት መንገድስ በየት በኩል ነው? ወዳጅ ዘመድ ቤታችንን ሲጎበኝ ‹‹ውይ የጥርሴን ሲዲ ሳላሳይህማ አትወጣም!›› ስንባባል አይታያችሁም?

የተዛባ መረጃ የሚያስተላልፉ

አንዲት ጠና ያለች የምትመስል ሴት ከህንጻ ስር ያለ በሚመስል የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ወደመኪናዋ (ግምት ነው) በመሄድ ላይ ሳለች ጥቂት ሰዎች መኪና ሲዘርፉ (ግምት ነው) ትመለከትና ሞባይሏን በማውጣት እንደሽጉጥ ደግና ‹‹ዞርበል! ወሮበላ ሁላ! እዘረጋሃለሁ፡፡›› በማለት አስፈራርታ ታባርራቸዋለች፡፡ በድንገት ሞባይሏ ሲጠራ ፈገግ ትላለች፡፡ /በሌላኛው የማስታወቂያው ዓይነት ሞባይሉ በአነስተኛ አጣና መሰል ቱቦ ብረት ይተካል/ ከዚያ ወደመኪናው ገብታ ስትረጋጋ ‹‹እንዴ? የሰው መኪና!›› ትላለች፡፡ ከዚያም ‹‹ግላኮማ በድንገት የዓይንን ብርሃን ይነጥቃል›› ይለናል የማይታየው አስተዋዋቂ

ጥያቄ 1 ግላኮማ በድንገት የዓይንን ብርሃን ይነጥቃል፡፡ ይነጥቃል ማለት ሙሉ ለሙሉ ከማየት ወደ አለማየት ያሸጋግራል ማለት ነው እንጂ ያልተከሰተን ነገር ያሳያል ማለት ነው ?

ጥያቄ 2 የማይታየውን ሳይሆን ትክክለኛውን ነገር ነው ያየችው ያልን እንደሆነ ደግሞ የሰው መኪና ሲዘረፍ ዝም ማለት ነበረባት ማለት ነው? ያስብላል:: ዘራፊን በማባረሯ ከመደሰት የሰው መኪና በመሆኑ ደንግጣለችና

ጥያቄ 3 ያየችው ነገር የማይታየውን ነው ዓይኗ ነው ያሳሳታት ካልን ደግሞ መኪናውን ማን ከፍቶላት ገባች ከሚለው ጥያቄ በተጨማሪ ይህ ታዲያ ‹‹ስቴዚዮ ፍሪንያ›› የተባለ ያልታየን ነገር እንደታየ የሌሉ ድምጾችን፣ ምስሎችን እና ንግግሮችን እንዳሉ አድርጎ የሚያሳይ የዓዕምሮ ህመም እንጂ የዓይን ህመም ነው እንዴ? ያስብላል፡፡

የቃላት ድረታ
‹‹ምግብ ማብሰል ትችያለሽ ?›› ብሎ የሚጀምር ማስታወቂያ ደግሞ አለላችሁ፡፡ የምግብ ማብሰል ውድድር የሚያደርግ ፕሮግራም ማስታወቂያ ነው፡፡ የምስል ቅንብሩ ጥሩ የሚባል ማስታወቂያ ቢሆንም የአስተዋዋቂው ድርቅና ይገርማል፡፡ ‹‹ምግብ ማብሰል ትችያለሽ ? አንተስ ? ›› ካለ በኋላ ‹‹የእውነት ግን ምግብ ማብሰል ትችላላችሁ?›› ብሎን እርፍ፡፡ መጀመሪያ የጠየቀን የውሸቱን ነበር ወይስ አላመነንም? ወይስ አየር ሰዓት መሙያ ቃላት ቸገረው? ያስብላል፡፡


በኪነ-ጥበብ ስራዎች ላይ ያጠላው መጥፎ ጥላ
 ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበሩ በአማርኛ የሚሰሩ ፊልሞች ሬስቶራንቶች ውስጥ ካፌ እና ባር በሚቀረፁበት ጊዜ ካፌውን ወይም የቤቱን ስም የሚገልጽ ታፔላ ወይም ፖስተር በተዋናዮች አስታከው በማሳየት ሳሳ ያለ ማስታወቂያ የመስራት አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜዎቹ ፍልሞች ‹‹ላምባ›› የተሰኘው ፊልም የአንባሳደር ልብስ ስፌትን እና ወጋገን ባንክን የማስተዋወቅ ተግባሩን በስሱ አከናውኗል፡፡ ‹‹ሰው ለሰው›› በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ‹‹የሆቴሌን ግቢ እና መናፈሻ ተጠቅማችሁ መኝታክፍሌ ውስጥ ስላልተቀረጻችሁ ኢሜጄ ተበላሸ›› አይነት ክርክሮች አድምጠን ነበር፡፡ እከሌ ሄቴል እንገናኝ፡፡ እንትን ባር፣ክለብ፣ካፌ እጠብቅሀለሁ፡፡ የሚሉት ደግሞ ደፈር ያሉት አስነጋሪዎች እና ነጋሪዎች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ምስጋና በሚለው የፊልሙ የመጨረሻ ክፍል ላይ በጽሁፍ ምስጋናቸውን በማስፈር ነው ቦታው የት እንደነበር የሚነግሩን አሁን አሁን እየታዩ ያሉ ጅምሮች ግን አደገኝነታቸው የከፋ ይመስላል፡፡

 ‹‹ሞጋቾቹ›› የተሰኘው በ EBS የሚተላለፈው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ስፖንሰሩ የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማስተዋወቅ ሲል ብቻ የኤቲኤም እና የሞባይል ባንኪንግን አገልግሎቶችን የታሪኩ አካል ለማድረግ በከፍተኛ መጠን ሲለፋ ተመልተነዋል፡፡ ‹‹በቃ ብር ካልያዝሽ በሞባይሌ ትራንስፈር አደርግልሻለሁ›› ሲባባሉ ‹‹እንዴ! አታውቂም እንዴ? በኤቲኤም ካርድ ተጠቅመሽ ዘመናዊ ሁኚ እንጂ፤›› እየተባባሉ ማስታወቂያ የተጫነው ዲስኩር ድራማ ነው ብለው ሰጥተውናል፡፡

 ‹‹አዲናስ›› የተሰኘው ፊልምም ‹‹እኔማ አብሮኝ ያረጀው ቅዱስ ጊዎርጊስ ቢራ ነው ምርጫዬ›› በማለት የስፖንሰራቸውን ስም የቃለ ተውኔቱ አንድ አካል ሲያደርጉ አስተውለን ታዝበናል፡፡ ምናልባት ስፖንሰር ባይደረጉ ኖሮ ወይም ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቱ ሌላ ቢሆን ዲያሎጋቸውም ትቀየር ነበር ማለት ነው?

ይበልጥ የሚያሳፍረው ደግሞ ‹‹ወርቅ በወርቅ›› የተሰኘው የሰራዊት ፍቅሬ ፊልም ላይ ያለው ነው፡፡ ከፊልሙ ጋር ግንኑነት የሌለው ማስታወቂያ ያለምንም መቆራረጥ የፊልሙ አንድ አካል ሆኖ ይተላለፋል፡፡ አንዱ ገፀባህሪ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲመለከት ያሳየን እና በቴሌቪዥኑ ውስጥ የሚታየውን ማስታወቂያ እኛም አንድ ሳናስቀር እንኮመኩማለን፡፡ ከአንድም ሁለት ማስታወቂያ እንመለከታለን፡፡ ፊልሙን አቋርጦ ገብቶ ቢሆን ይቅርታ እንድናደርግለት እንኳን እድል በሰጠን ነበር፡፡ የሆነው ግን የታሪኩ አንድ አካል በመሆን ነው፡፡ አስቂኙ ነገር የፊልሙ ዋና ገጸባህሪ ሰራዊት ሽማግሌውን አሰልጣኝ ሆኖ ሲተውን ይቆይና ወጣቱን የማስታወቂያ ባለሙያ በመሆን ደግሞ እዚያው ላይ ይታያል፡፡ ይቺናት ንቀት አትሉም? የተመልካች ንቀት፡፡

ድረጊቱ ምናልባት ገንዘብ ለመሰብሰብ ይጠቅም ይሆናል፡፡ ምናልባት ተመልካችን ጉሮሮውን አንቆ ማስታወቂያን ለማስተላለፍ ይጠቅም ይሆናል አዝማሚያው ግን አደገኛ ነው፡፡

‹‹መረዋ›› የተባለው የድምታዊያን ውድድር ፕሮግራም ላይ ስፖንሰር የሆነውን ድርጅት በተደጋጋሚ ማስታወቂያዎች ደጋግሞ መንገሩ አልበቃ ይልና አስተዋዋቂዋ ልትሰናበተን ስትመጣ ፍጹም ጥበባዊ ባልሆነ ሙያዊ ስነምግባርን በጣሰ መልኩ ‹ከሽ› ስታደርገው እንመለከታለን፡፡

 ‹እስማማለሁ፣ አልስማማም› የተሰኘው ፕሮግራምም ለታዳሚዎች ይዞ የሚመጣው ብቸኛ ቁምነገር የስፖንሰር ድርጅቶችን ታሪክ ብቻና ብቻነው፡፡ የሚጋበዙት ሰዎች በጣም ታዋቂ በመሆናቸው ምንም አዲስ ነገር ፕሮግራሙ  አይነግረንም፡፡ በጣም ባይታወቁ እንኳን ለማስተዋወቅ የሚሆን ጊዜ የለውም ማስታወቂያው ይሻማበታል፡፡

ይህ ሲያድግ፣ ይህ ሲለመድ፣ ይህ ቢዝነስ እየሆነ ሲመጣ፣ የጥበብ ስራዎች የንግድ ድርጅቶችን ታሪክ ወደሚሰራ ሸቃጭነት የመቀየር ከባድ አዝማሚያ አለው፡፡ እናም ሀይ ሊባል ይገባዋል፡፡ የኪነጥበብ ስራ እና የማስታወቂያ ድንበር ይለይልን፡፡

ISO
በ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ኦርጋናይዜሽን የሚሰጥ የምስክር ወረቀት ነው፡፡ በተለይ በዓለማቀፍ ገበያዎች ላይ ለመግባት ለሚያስቡ ኩባንያዎች ምስክር ወረቀቱን መያዛቸው ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላቸዋል፡፡ ምክንያም አብረዋቸው የሚሰሩት ሌሎች አለማቀፍ ካንፓኒዎች ዛሬ ያዩትን ምርት በተደጋጋሚ መልሰው ለማግኘታቸው መተማመኛ ይፈልጋሉ፡፡
በማስታወቂያዎቻችን ላይ እየተሰራ ያለው ስህተት ግን እውነታውን አዛብተው ማቅረባቸው ነው ‹‹የ ISO
የጥራት ደረጃ ተሸላሚ›› በማለት በተደጋጋሚ ሲያስተዋውቁ ይስተዋላል፡፡ ISO ሽልማት ነው እንዴ? ለምሳሌ አንድ ሰው በአንድ የትምህርት መስክ ተምሮ ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ ቢቀበል ዲግሪ ተሸለመ ይባላል? ዲግሪው የሚያሳየው ያለፈባቸውን የትምህርቶች ዓይነቶች እና የወሰዳቸውን ኮርሶች ብሎም አሁን ያለበትን ደረጃ ነው፡፡ ስለዚህ ISO ሽልማት አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን አይጠቅምም ወይም አያስፈልግም ማለት እንዳልሆነ ይሰመርበት፡፡ ISO የጥራት ደረጃ የተሰጠው አንድ የቢራ ፋብሪካ ቢኖር ሁሉም የቢራ ጠርሙሶች ውስጥ ያለው ንጥረነገር ተመሳሳይ ነው አይዋዥቅም ማለት ነው፡፡ ISO ከሌለው አይረባም ማለት አይደለም፡፡ ቦይንግን የመሰለ ድርጅት ISO ሰርቲፋድ አይደለም፡፡ ቦይንግ የራሱ መለኪያ አለው፡፡ የመኪና ማምረቻው ፊያት ISO ጎብኝቶት አያውቅም፡፡ እና እንደነዚህ ማስታወቂያዎቻችን አባባል ድርጅቶቹ ጥራት የላቸውም ማለት ነው?

ስለምንም የማያወሩ ማስታወቂያዎች
አንዲት ሴት ጸሀይ እንዳቃጠላት፣ ሙቀት እንዳደከማት ሆና ስትጓዝ እናያለን፡፡ ከዚያም አንድ በቀጭኑ የሚፈስ ወንዝ ትመለከትና በደስታ ፊቷን አብርታ እየሮጠች ወደወንዙ ትሄዳለች፡፡ በምትሮጥበት ወቅት ልብሷን እያወላለቀች ነው፡፡ እዚያ ወራጅ ፏፏቴ ላይ ስትደርስ ትጠመቃለች (ትታጠባለች) ይህንን ትእይንት ሲመለከት የነበረ ሰው ፈገግ ብሎ ያጨበጭባል፡፡ አለቀ፡፡ ብታምኑም ባታምኑም ማስታወቂያው ተጠናቀቀ፡፡ የባንክ ማስታወቂያ ነው፡፡ ስለምን ማውራት ፈልገው እንደቀረጹት ምኑን ዳይሬክት እንዳደረጉት ኤዲተሩ ምን እንደገባው ፈጣሪ ይወቅ፡፡ መልዕክቱ እንዲተላለፍለት የፈለገው ድርጅት እና መልዕክቱን ያስተላለፈው ጣቢያ ምኑን እንደገመገሙት ግን እነርሱ ይወቁ፡፡

ትውፊትን የሚያበላሹ ማስታወቂያዎች
ከንግግር ይልቅ በዜማ እና በግጥም ተውቦ በሙዚቃ መሳሪያ ታጅቦ የሚቀርብ ስራ በታዳሚው ህሊና ውስጥ ዘለግ ላለ ጊዜ የመቆየት ዕድል እንዳለው ሁሉም ይስማማበታል፡፡ ነገር ግን የዚህ የማስታወቂያ ዘርፍ ዋና አላማ የድምጻዊውን ችሎታ የቅንብሩን ጥበብ አለያም የገጣሚውን የቅኔ ብቃት ማሳየት አይደለም፡፡ የብዙዎቹ አዘፋኝ ማስታወቂያዎች ችግርም ይኸው ነው፡፡ በአብዛኛው በድምጻዊው ችሎታ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ የግጥም ይዘታቸውም የቀለለ ከመሆን አልፎ የተቃለለ የሚሆንበት ጊዜ ይበዛል፡፡
ከሁሉ የሚብሰው ግን ‹‹የህዝብ›› በመባል የሚታወቁትን፤ ‹እከሌ› የተባለ ባለቤት ሊጠራላቸው የማይችልን፤ ባህላዊ ዜማዎች  እያነሱ በዘፈቀደ የመጠቀማቸው ነገር ነው፡፡ ትንሽ ቀደም ባሉት ጊዜያት የወቅቱን ገናና ዘፈን ማንንም ሳያስፈቅዱ ብድግ አድርጎ የማስታወቂያ ማድመቂያ ማድረግ ትክክል የሚመስልበት ጊዜ ነበር፡፡ የስራው ባለቤቶች ‹‹አልበዛም እንዴ?›› ማለት ሲጀምሩ፤ ስራችንን ተጠቅማችኋልና ከጥቅማችሁ አካፍሉን ማለት ሲጀምሩ ቀስበቀስ በመቀነስ ላይ ነው፡፡ አሁን አሁን የቀደመ በሚመስል አኳኋን እየተረባረቡባቸው የሚገኙት ትውፊታዊ የህዝብ ዜማዎችን ነው፡፡ ‹‹አሲና በል አሲና ገናዬ፣ አበባየሆሽ፣ ሆያዬ፣ አሸንዳ›› ሌሎችም የህዝባዊ በዓላት ማድመቂያ የባህል እሴቶች በተለይ የቢራ ፋብሪካዎቹ የግል ንብረት እየሆኑ ከመጡ ጥቂት እንቁጣጣሾች አልፈዋል፡፡ የባህል ወታደር፣ የትውፊት ዘበኛ በሌላት ሀገር ነገሩ ተጠባቂ ቢሆንም እባካችሁ አትበርዙብን እውነታን ከሸቀጥ አትቀይጡብን ብለን ልንለማመናቸው ግድ ይላል፡፡ ተደጋጋሚ ውሸት እውነት ይመስላልና ‹‹አበባየሆሽ›› የሚለውን የሰማ ታዳጊ ህጻን ‹‹ዜማው የጊዮርጊስ ቢራን ማስታወቂያ አይመስልም?›› ሳይለን በፊት ሁሉም ነገር ወደነበረበት ቢመለስ ደግ አይለለምን? ‹የህዝብ ነው› ማለት፡- ‹የሁላችንም ነው፡፡› ማለት ነው እንጂ፤ ‹የማንም አይደለም› ማለት አይደም፡፡ 

ቀጥታ ትርጉም ማስታወቂያዎች
የተወሰኑ ምርቶች ለውጪው ማህበረሰብ አገልግሎት ተብለው ይዘጋጁና ተንቀሳቃሽ ምስላቸው እና መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉበት መንገድ እንዳለ ሆኖ ቋንቋቸው ብቻ በኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ሲቀርብ ዕናስተውላለን፡፡ ይህ መሆኑ ብቻውን ክፋት የለውም፡፡ አስቸጋሪው ነገር ከኛ ማንነት፣ አስተሳሰብ እና አኗኗር ጋር የሚሄዱ እና የማይሄዱ መሆኑን በጥሞና አስተውሎ መምረጡ ላይ ነው፡፡
የአንድ ዶድራንት ማስታወቂያን መመልከት ለዚህ መልካም ማሳያ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ሁለት ወንዶች በግራና ቀኝ ከሁለት አቅጣጫ ዶድራንት እየነፉ ወደአንድ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ ሽታው የጠራቸው ሴቶች ሸታውን ተከትለው ወደስፍራው ይሄዳሉ፡፡ አንድ ሰው ከወገብ በላይ ራቁቱን ሆኖ የተንኳኳውን በር ይከፍታል፡፡ ዶድራንት የያዙት ሰዎች ሰውነቱ ላይ ይነፉበታል፡፡ ሴቶቹ ሲደርሱ በቀጥታ ዶድራንት የተነፋበት ወንድ ላይ ይንጠላጠላሉ፡፡ ‹ሀፒ በርዝደይ› የሚል ዘፈን የማስታወቂያው ማጀቢያ ነው፡፡
ይህንን ማስታወቂያ ለኛ እንዲያገለግል በቀጥታ ወደኛ ስናመጣው ምን መልዕክት እንዲያስተላልፍልን አስበን ነው? ሊባል የተፈለገው ነገር ከኛ የስነ- ማህበረሰብ አስተሳሰብ ጋር የሰመረ ነው? ይህንን ማስታወቂያ የተመለከተ ‹‹ሴቶች የራሳቸው መንገድ የላቸውም፤ ቅጽበቱ የፈጠረላቸውን አጋጣሚ የሚጠቀሙ አቅጣጫ አልባዎች ናቸው!››› የሚል ግንዛቤ ከፊልሙ ወስጃለሁ፡፡ ብሎ ሊሞግተን ቢከጅል ምን ማስተባበያ አለን፡፡

የሞዴስ ማስታወቂያ ደግሞ አለላችሁ፡፡ የተሰራው በአፍሪካዊያን ነው፡፡ ለኛ የሚተላለፈው በትርጉም ነው፡፡ ተርጓሚዋ ሴት ናት፡፡ የምትተረጉመው በዜማ እና በግጥም የተባለውን ነው፡፡ ይሁን እጂ እርስዋም አማርኛ አትችልም፡፡ በኮልታፋ አንደበቷነው የምትንተባተብብን፡፡ ‹‹ማዬት ዬሌም፣ ማዬት ዬሌም›› እምትለን፡፡ ምንጉድ ነው! ጭራሽ አማርኛም ከውጪ እናስመጣ እንዴ? አሁን እኮ ለምን ለሚለው ጥያቄአችን ፡- አንዳንድ ፊልሞች ላይ ጣል እንደሚደረጉት ‹‹ፈረንጆች›› ሁሉ ለማስታወቂያው የተለየ ከለር ለመስጠት ብለን ነው፡፡ ይሉን ይሆናል ሳያፍሩ

ተማዐኒ ያልሆኑ ማስታወቂያዎች
ግነት አንዱ የማስታወቂያ ባህርይ ነው፡፡ ታዳሚው ለነገሩ ጉጉት ኖሮት የተባውን እንዲያደርግ የማድረግ ብቃት እንዲኖረው ሲባል ያልበዛ ግነት እንደቅመም ጣል ይደረግበታል፡፡ አለመታመን ጫፍ ላይ ያልደረሰ፣ ከመታመን ቅጥር ያልወጣ ሚዛናዊ ግነት- ግነቱ የበዛ እንደሆነ ግን ኩሸት ይሆናል፡፡ ምን ነካቸው ያስብላል፡፡

የሳሙናን ማስታወቂያ ለመስራት ቤተሰቦቿን በፊሽካ ጠርታ እንደወታደር ካሰለፈች በኋላ አፍንጫዋን በመጠቀም የጥራት ደረጃ ፍተሻ የምታደርገውን እናት አይተን ‹ምን ነካቸው› ያላልን እጅግ ጥቂቶች ነን፡፡
‹‹አይዞሽ አትጨነቂ ማሬ ይሄኮ ምንም ማለት አይደለም›› የምትባለውን ታዳጊ ተመልክተን ያስጨነቃት ምንድነው? ብለን ያልተገረምን ጥቂቶች ነን፡፡ ጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተባት ህጻን ትሆን? የሞዴስ ምርጫ የተምታታባት ሞልቃቃ ትሆን? ወይስ ምን ትሆን? ያላልን ጥቂቶች ነን፡፡

እንዲህ እንዲህ እያልን ርዕስ እየፈለግን ምሳሌ እያስከተልን ብንቀጥል የምናስተርፋቸው እጅግ ጥቂት ይሆኑብናል፡፡ ጊዜና ወረቀትም ይባክንብናል፡፡ እናም እዚህ ላይ ገታ አድርገን የትንታኔውን፣ የትዝብቱን እና የጥያቄውን የቤትስራ ለታዛቢዎች ሰጥተን መልካሞቹን፣ እንዲበዙልን የምንሻውን ደግሞ እናድንቅ፡-

  የዚህ ማስታወቂያ ዓላማ ማሳየት ነው፡፡ የሚያሳየውን ደግሞ በትክክል አውቋል፡፡ ጫማ፡፡ የጫማ ማስታወቂያ ነው፡፡ መደርደሪያ ላይ ቁጭ ብሎ ያሳየናል፡፡ የወንድ እና የሴት፡፡ ሰዎች መጥተው ያነሱታል፡፡ ከዚያ ሲራመዱ እናያለን፡፡ የካሜራው ትኩረት ከጉልበት በታች ያለው አካል ላይ ብቻ ነው፡፡ ባስፋልት በኮብል ስቶን በደረጃ ይሄዱበታል፡፡ አሁን ተቀመጡ ቢሮ ውስጥ ናቸው፡፡ ደግሞ መንገድ ላይ ሲሄዱ፡፡ ሴቷ ቆማ እየጠበቀችው ነው፡፡ አብረው መጓዝ ጀመሩ፡፡ ካፌ ተቀመጡ የተመቻቸው ይመስላል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ‹ጠንካራ፣ ምቹ፣ አስተማማኝ› የሚል የሰው ንግግር አንሰማም፡፡ ማጀቢያ ሚዚቃ ብቻ! ሳር ላይ ናቸው፡፡ ጫማውን አውልቀው አስቀምጠውታል፡፡ ቀጥሎ እየደነሱ ነው፡፡ መለያያቸው ደረሰ ሴቷ እግሯን ከፍ አደረገች እየሳመችው ነው መሰል፡፡ ማሰታወቂያው ከማብቃቱ ጥቂት ሰከንዶች በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ የንግግር ድምጽ መጣ ‹‹አንበሳ ጫማ›› በቃ! ምንም ግር ግር የሌለው፤ ፋብፊካ ለፋብሪካ ያላንከራተተን፣ ቆነጃጅት ‹ሲያምር› ‹ስወደው› ያላሉበት፣ ራሳቸውን ነው ወይስ ምርቱን ነው የሚያስተዋውቁት ያላስባለን፣ የሚሰራውን የሚያውቅ ሰው ያሰናዳው፤ ማሳየት ያለበትን ነገር ጠንቅቆ ያሳየ የተሳካ ማስታወቂያ፡፡

በመጨረሻም
ማስታወቂያ የድምር ችሎታዎች ውጤት እንጂ፤ የድምጽ ማማር ብቻ፣ ወይም ቃላትን አሳክቶ መናገር የመቻል ብቻ፣ ወይም በካሜራና ኤዲቲንግ የመራቀቅ ብቻ ውጤት አይደለም! ብንልስ? አንድ ታዋቂ የሀገራችን የማስታወቂያ ባለሙያ ቆየት ባለ ቃለ መጠይቁ እዲህ ብሎ ነበር 

‹‹ማስታወቂያዎቼን እንዲያዩልኝ የምፈልገው ቴሌቪዥናቸውን ከፍተው ብቻ ሳይሆን ከሸጡትም በኋላ ነው ! ›› 

ጥበባዊ ደጀጃቸው ከፍ ሲል፡፡ የይድረስ ይድረስ እና ሁሉም አያምልጠኝ አይነት አሰራሮች ሲወገዱ ይህንን ማድረግ ይቻላል፡፡ ወደዚህ ጫፍ ከመድረሳችን በፊት ቢያንስ ሬዲዮናችንን ሳንዘጋው በፊት ቴሌቪዥናችን ላይ አፍጥጠን ባለንበት ቅፅበት እንኳን የምናደምጣቸውና የምንመለከታቸው ማስታወቂያዎች እንዲበዙልን ይሁን፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጣ

No comments:

Post a Comment