Thursday, November 7, 2013

በጤነኝነት ስም የሚፈረጁ ጤና ማጣቶች

የአእምሮ በሽታ ነው።ይህንንስ ለኔ ባረገውየሚስብል ዓይነት . . . ምልክቶቹ በዘመነኛ አልባሳት እስካፍንጫ ድምቅ ብሎ መታየት፣ ከፍተኛ ዋጋ በሚያስከፍሉ ልብሶች መዘነጥ፣ በውድ ሽቶዎች መአዛ መታጠን ናቸው። ይህ ብቻ አያደለም ህመሙን ህመም ነው ብለው የነገሩን እንዳሉት ከሆነ ነገርየው ልዩ ችሎታ እና ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች የሚያጠቃ እንደመሆኑ ሰለባዎቹ ህመሙ በተነሳባቸው ጊዜ የፈጠራ ችሎታቸው በዕጅጉ ይጨምራል። ቀን ከሌት በትጋት አዲስ ነገር ሲያስሱ ሲፈጥሩና ሲመራመሩ ውጤታማ ጊዜን ያሳልፋሉ። በጤነኝነት ጊዜያቸው ወራትን ይፈጁባቸው የነበሩ ስራዎች በህመማቸው ወቅት በቀናት ውስጥ ያጠናቅቁታል። ምስጋና ለህመማቸው። በደህንነት ዘመናቸው የሚኖራቸው አለባበስ እንደነገሩ ነው። በህመማቸው ወቅት ግን ከማንም በላይ ቂቅ ያላሉ። ምስጋና ለህመማቸው። ለፈጠራዎቻቸው መጠነኛ ትኩረት የሚሰጡት ካልታመሙ ነው የተነሳባቸው ሰሞን በሙሉ ትኩረት ብቻ ሳይሆን ብቃትም ስራቸውን ያከናውናሉ። እድሜ ለህመማቸው።
 
ይህንን ከላይ የጠቀስኩትን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ ሲሰሟቸው ህመም የማይመስሉ ባለሙያዎቹ mental disorder ብለው የሚጠሯቸው ህመሞች አሉ። ይህ አእምሮ የሚባለው ነገር ረቂቅነቱ ረቆ ተራቀናል ለሚሉት ተመራማሪዎችም ርቆባቸው ሙሉ ለሙሉ አልደረሱበትም።

/ይህ ጽሁፍ በራዲዮ የሚነበብ ቢሆን ኖሮ <<ይገርማል ይደንቃል ይገርማል የሰውልጅ ተጥሮ፣ ዘመኑ ሲያበቃ ሲኖር ተሰውሮ አንዳች ነገር የለም በምድር ላይ፣ የሚያስገርም ከሰው በላይ>> በሚለው ዜማ ይታጀብ ነበር /
ስለዚህ ማንም ሰው መገመት መብቱ ነው። ግምቱ ፍሬ ካለው ለምርምር መነሻ ይሆናል። ፍሬ ከሌለው ደግሞ ለሌላ ፍሬ ላለው ግምት በር ይከፍታል። እነሆ እኔም ልገምት ነው።
አለቃዬ። መንግስት ሾሞት። በኔ እና በስራዬ ላይ የነገሰው። 10 ክፍልን እንደነገሩ አጠናቆ ዲግሪ ነኝ የሚለው። በሆነ የስራ ቀን ስራ ገበታዬ ላይ እንደማልገኝ ስነግረው ሂድ ይቅናህ ብሎኝ ሲያበቃ ምክንያቴ የትምህርት ጉዳይ መሆኑን ሲያውቅ ፈቃድ የሚከለክለኝ ሰው . . . የበታች ሰራተኛ የሚያመጣውን ማንኛውንም ሀሳብ አለመቀበል። ትክክልም ቢሆን. . . በሚል የአስተሳሰብ ደዌ ተለክፎ ቢሆንስ?

በማህበራዊ ድረገፆች ተከልላ ዕድሜዬን ሙሉ የገነባሁትን የስም ካብ ድማሚት የምትጥልበት፣ ጥሩ ሰው ቅብ የሆነችዋ - ቅቧ ሲለቅ እውነተኛው መጥፎነትዋ የሚጎላው ያቺ ልጅስ ብትሆን . . . ጭር ሲል አለመውደድ፣ በጸብ ካባ በክርክር ሸማ ተጀቡኖ መኖር የሚባል እያገረሸ በሚዳፈን ህመም ስላለመለከፍዋ ምን ማረጋገጫ አለ?
ያቺ ደግሞ ፀሀፊዋ ፀባይዋን በአንድ ዘርፍ መመደብ የማይቻለዋ ልጅ . . . ሰዎች ዘና ብላለች ቀልድ ነገረችኝ ብለው ለመሳቅ ከንፈሮቻቸውን ማላቀቅ ሊጀምሩ ሲሉ ፊትዋን ከስክሳው ህዝብ የምታስደነግጠው። ልታናግረኝ አንደበትዋ ተላወሰ ብለው ለመመለስ ሲሰናዱ በግልምጫ አፈር ከድሜ የምትደባልቀው። በፀሐፊነት ብትቀጠርም ፃፊልን ሲሏት የሰደቧት የሚመስላት . . . በሰላም እና በፍቅር ያለጭቅጭቅ ያለመኖር ወይም በማሸበር እና በማጭበርበር መኖር በሚባል ክፉ ህመም በመሰቃየት ላይ ትሆን እንዴ?

ያም አለ ደግሞ ባልደረባዬ የሚያውቀውን ሲያካፍል እድሜው የሚያጥር የሚመስለው። ሊስሙት ሲቀርት በመነከስ የሚረዳው። በሌላው ማጣት ከሱ ማግኘት እኩል የሚዝናናው . . . መረጃን ማቆር ወይም ኢንፎርሜሽንን ጠብቆ እና ደብቆ ማኖር በሚባል ካልተኛ በቀር በየደቂቃው እየተመላለሰ በሚያሰቃየው ህመም ተጠቅቶ ይሆን እንዴ?
በራድዮ ሞገድ እየፈሰሰ በየቀኑ አንብቡ ቢልም ካነበበ ወር ዕንዳለፈው አንደበቱ የሚያሳብቅበት። አዋቂነቱን የሚለካው በተማረው መጠን ባወቀው ልክ ሳይሆን አብሯቸው ማኪያቶ በጠጣው ፕሮፌሰሮች ልክ የሆነው ያኛው ደግሞ . . . ሙገሳ አጠር ዘለፋ መር በተባለ የአመለካከት ነቀርሳ በመንገላታት ላይ ቢሆንስ?

ወዳጄ መጠርጠር ደግ ነው።

No comments:

Post a Comment