Monday, December 7, 2015

ያለመግባባታችን ምንጭ በጣም መግባባታችን ነው!

አየሽ እኔ እና አንቺ በጣም ተግባብተናል፡፡ ተገባብተናል፡፡ እኔ አንቺ ውስጥ. . . አንቺም እኔ ውስጥ. . . አሳምረሽ ገብተሸኛል፡፡ በትክክል ገብቼሻለሁ፡፡ ዘላቂ መግባባታችን የወለደው አለመግባባት እዚህ ጋር ይፀነሳል፡፡

ሀሳቤን ብቻ ሳይሆን የሀሳብ መንገዴን አግኝሽዋል፡፡ የውሸቴን መነሾ እስከ መድረሻና ውጤቱ መናገር ሳልጀምር አውቀሽዋል፡፡ ፊቴ ላይ የሚሯሯጠው ደም ካዘለው ስሜት በላቀ በልቦናዬ
ያፈንኩትን ሀቅ መገንዘብ ችለሻል፡፡


እና እንደምን እንግባባ?!

ዝምታሽ ውስጥ ያለውን ንግግር አሳምሬ አደምጠዋለሁ፡፡ ቅዠትሽ መሀል ያለውን ቅኔ ነጥብ በነጥብ እፈታለሁ፡፡ የትንፋሽሽ ግለት እና ርጥበት፤ የገላሽ ትኩሳት፤ ላቦትሽ እና ጠረንሽ ሳይቀሩ ሚስጥርሽን ያካፍሉኛል፡፡

እና እንደምን እንግባባ?!

አንዳንድ እውነቶች ካልተዳፈኑ፤ አንዳንድ ስሜቶች ካልታፈኑ፤ አንዳንድ ምስጢሮች ካልተከደኑ . . . መሸዋወድ እንደምን ይሆናል? ህይወትስ ምኑ ደስ ይላል?

No comments:

Post a Comment