Wednesday, April 9, 2014

ለሚመለከተው ሁሉ

አዎ አንተ የተማርክ ነህ!  ከአንድም ሁለት ሶስት ተቋማት ውስጥ ገብተህ አንደኛ ፣ ሁለተኛ ፣ እያልክ ዲግሪዎችን ደርድረሀል። ‘አንቱ’’ ተብለሀል። ሀገርህ ካሏት ’ ምሁራን’ መካከል ቀዳሚዎቹ ረድፍ ላይ አለህበት።

አዎ አንተ አንባቢ ነህ! ከትምህርት ቤት ከወጣህ ማግስት ጀምሮ በአዲስ ሀሳብ ውስጥህን ለመሙላት፤ የያዝከውን ጅምር እውቀት ለማስፋት፤ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦችን ለመገንዘብ ቀን ከሌት ትታትራለህ።


አዎ አንተ ፀሀፊ ነህ! ተመራምሬአለሁ ብለህ . . . ጠቃሚ ሀሳብ ነው ብለህ . . . የድርሻዬን ለሀገሬ ልወጣ ብለህ . . . መጻኅፍትን አሳትመሀል። ጽሑፎችን በትነሀል።

አዎ አንተ መምህር ነህ! ነገን የምትገነባ የሰው አንጥረኛ። በቃ አንተ ታዋቂ ብቻ አይደለህም አዋቂም ነህ።

ይህ ሁሉ በእንዲህ እንዳለ ግን . . . 

መማርህ ፣መመራመርህ . . . ሰብአዊ አስተውሎትህን ደፍኖብሀል። ዕውቀትህን ወገንህን ለመስደብ እንጂ ለማንቃት አልተጠቀምክበትም። ማንበብህ የራስህን ሀሳቦች አሳጥቶሀል። የኔ የምትለው አመለካከት የለህም። ‘እነሌ እንዳለው . . .” እያልክ ጥቅሶች እንድታነበንብ እንጂ በህይወትህ እንድትተረጉመው አላደረገህም። ፀሐፊነትህም ቢሆን በቀልኩበት ለምትለው ወገንህ አልበጀም። በሀገር ውስጥ ቋንቋ መጻፍህን ከማነስ ስለምትቆጥረው በፈረንጅ አፍ እንጂ በሀበሽኛ አልጻፍክም። በመምህርነት የቀረጽካቸው ተማሪዎች ስላንተ የሚያስታውሱት በሰው እድሜ ላይ የምትጫወት ጨካኝ ፍጥረት መሆንህን ብቻ ነው። የዛሬ ብዙ ዓመት ያጠናኸውን ኮርስ እንደ ቴፕ ሪከርደር ከማነብነብ በቀር አዲስ ነገር የሌለህ ቀፎ።

በቃ አንተ እንደዚህ ነህ! ብዙ ነገር እያለው ምንም ነገር የሌለው ባዶ . . .



No comments:

Post a Comment