Thursday, July 18, 2013

ክር ባጭር

በድሮ ጊዜ ነው። በሀገር ወግ በህግና በስርዓትያሳደጓትን ልጃቸውን ላግባ ባይ ጠያቂ የበዛባቸው አባወራ ማንን ከማን ለይተው ለማን እነደሚድሯት ግራ ቢገባቸው ፈተና አዘጋጁ

ፈተናው ጋቢ መስፋት ነው። አስፈላጊው መሳሪያ ሁሉ ተሟልቷል። ጋቢ፣ ክር. መርፌ ሁሉም ቀርቧል።

ያፈቀራትን ሴት በእጁ ለማስገባት የጓጓው የአዳም ዘር ውድድሩን ጀመረ። ሁሉም ጥድፊያ ላይ ነው። ማንም ማንንም አያይም። አባት እና ልጅ ብቻ ሁኔታውን ያታዘባሉ።


ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች ውስጥ አይኗ ያረፈበትን ጉብል የግሏ እንዲሆን የሻተችው ልጃገረድ የወጣቱ አያያዝ ባያምራት፤ ክሩን አንከርፎ ሲጎትት ሊውል መሆኑ፣ በዚህ ከቀጠለ ደግሞ እንደሚሸነፍ እና ለሌላ ልትሰጥ መሆኑ ቢገባት፤ እቃ ላነሳሳ በሚል ሰበብ ወደ ጉብሉ ተጠጋች። ጉድ ጉድ የምትል አስመስላም እንዲህ አለችው።

 ''ሰውየው! ክር ባጭር።''

ወጣቱም ምክሯን ሰምቶ ክሩን አሳጠረ። ቶሎ ቶሎ ሰፍቶም አሸናፊ ሆነ።

እኛም እንድናሸንፍ ክር አሳጣሪዎች ይብዙልንማ! የምንገነባው ካሰብነው በላይ እንዳያስወጣን፣ የምናወራው እንዳያሰለቸን፣ የምንጽፈው እንዳይዛዛ ክር ባጭር አያሻንም?

No comments:

Post a Comment