(ንዑስርዕስ ) ወደብርሀን
የምንገኘው ብርሀን
ከሚታደልበት ብርሀን ውስጥ ነው። የብርሀን ማነስ ድንግዝግዝን ካወፈረበት ዓለም። ብርሐን ማለት ዕውቀት ነው። ዕውቀት ማለት እውነት፣
እውነት ማለት ውበት ማለት ነው። ሐቀኛ ውበት ከልከኛ እና ከቀና እውነት ይወለዳል። ውበት ሁሉ እውነት አይደለም። እውነት ሁሉ
ውበት አይደለም። በሀቅ ካባ የተጀቦነ - በበግ ለምድ የተሸሸገ ተኩላዊ እውነት አለ። በሽንገላ ከንፈር ማንነቱን የተነጠቀ እውነት
አለ። ብልጭልጭ የጋረደው። አርቴፊሻል ውበት አለ በብልጭልጭ ብዛት፣ በወከባ ብዛት፣ በግርግር ብዛት ውበት ማማ ላይ የተሰቀለ።
የድንጋሪው ማጥሪያ ወንፊት ማስተዋል ነው። ማስተዋል። በመገለጡ ውስጥ ያለውን ቅኔ መፍታት።
ግስጋሴው ወደፊት ነው።
ፈትለፊቱ ድንበር የለውም። ጫፉ መሻት ነው። ዕውቀትን መሻት። ጥልቀትን፣ ምጥቀትን፣ ስፋትን፣ ርዝመትን መሻት . . . ሁሉም በፍላጎት
ነጻ ፈቃድ የሚወለዱ፤ በጥረት እልህ አስጨራሽ ትጋት የሚያድጉ እና የሚጎለምሱ ነገዎች ናቸው። የዕውቀት ኬላ ማማዎች . . . ያልደረሱበትን፣
ያመረመሩትን እየጓጉ የሚናፍቁበት፤ የያዙትን አጣጥመው የተሻለ የሚማትሩበት፤ እንደመሰላል ያለ የከፍታ አጋዥ። ተንጠራርተው እየጨበጡ።
የጨበጡትን ሳይረግጡ ይልቁንም ባለው ላይ እየደመሩ። የመንገዱ መቋጫ እርካታ ነው። ደረስኩ፣ በቃሁ፣ ነቃሁ፣ በሰልኩ፣ ባሉበት ቅጽበት
የጉዞው ምዕራፍ ይዘጋል። ‘ብርሀናማ ጨለማ’ን ‘ወርቃማብርሀን’ ነው ብሎ በማምለክ ቅያስ ውስጥ መዳከር ይጀመራል። . . .
ለልግመኝነት እጅ ካልሰጡ
በቀር መቆም ክልክል ነው። አለመንቀሳቀስ አይቻልም።መጣር፣ መጋር፣ መቆፈር ያስፈልጋል። ከባህር የተወረወረወረ ካልተወራጨ፣ ካልተንቀሳቀሰ
/ከፈዘዘ/ እንደሚሰጥም- በህያውነት መስመር ላይ ያለም ካልመረመረ፣ ካልጨመረ ህይመት አልባ እስትንፋስ ይኖረዋል።
አሪስቶትል ‹‹የሰው
ልጅ የመኖር አላማ ማወቅ ነው!›› እንዲል ወደፊት መሄድን የሚሻ የሚረግጠውን ማወቅ አለበት። መመልከት አለበት። ከባቢውን መቃኘት
አለበት። እዚህ ሰፈር ተሁኖ በዚህ መንደር እየተመላለሱ ማየት ለሚሹ ዓይን ብቻ አይበቃም። ድፍረትም አይበቃም። ማስተዋልም አይበቃም።
ብርሀንም አይበቃም። በልኩ እና በመጠኑ መሰፋት አለበት። የተመልካቹን የዕይታ ብቃት ከመንገዱ ርቀት (ርዝመት)እና ርቀት (መርቀቅ)
ጋር ያመጣጠነ ብርሀን በነፍስ ወከፍ መሸከፍ አስገዳጅ ቅድመሁኔታ ነው።
እያንዳንዱ ጥርጊያውን
የሚያበጀው በልክ እና መበጠኑ በተሰናዳ ሽንቁር ነው። በብርሀን ሽንቁር። የአንዱ ፋኖስ ለአንዷ፤ የሌላው ጧፍ ለዛኛው፤ የከሌ አባበለው
ሻማ ለነከሊት አያገለግልም። የነገርየው ተፈጥሮ ለግል አገልግለሎት ብቻ እንዲሆን ነው።
አንድ ሰው ባጠለቀው
መነፅር ሌሎች እሱን መስለው እሱኑ አህለው ማየት እንደማይችሉ እዚህም እንዲያ ነው። ቦታው የሚሰጠው ነጻነት የማካፈል ምቾት ነው።
በቅን ልቡና የመለገስ ጸጋ።
ወርውር የጅህን ዘገር፣
በትን ያሻራህን ዘር፤ እንዲል
ባለቅኔው።
ስትሰጥ ዋናህ አይነካም።
ስትዘከር አይጎድልብህም። እየበራ ካለ ሻማ ላይ ሌላ ሻማ ብትለኩስ ሁለቱንም እንደምታበራ - ይህ ሲሆን የአንዱ ብርሀን ከአንዱ
እንደማይበልጥ እንደማያንስ- ተለጋሹ ሲሞላ ታያለህ፤ የለጋሹ ሙሉነትም አይቀንስም።
ልብ በል! መስጠት
እና አምሳያን መቅረጽ ለየቅል ናቸው፡፡ ተማሪህን ራስህን ውስጡ በመቅረፅ ራሱን አታሳጣው፡፡ የሰጠከውን ከተቀበለው ቀይጦ ከራሱም
ቀላቅሎ አዲስ ማንነት እንዲያበጅ ነፃነት ስጠው፡፡
አሁን ያሉበትን ርካብ
በከፍተኛ እልህ አስጨራሽ ትግል የተቆናጠጡ ይበረክታሉ። ሳያስቡት የትላንትናው ነፋስ እዚህ የጣላቸውም አሉ። የጉዞውን ህግ ፈጽሞ
ዘንግተው። የዛሬ ኑሯቸውን ተላምደው። ያለኝ ይበቃኛል ብለው። በድንግዝግዛቸው ላይ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠሩ
‘ያለኔ ማን ’ ባዮችም አሉ። ከፍ ወዳለው ብርሀን ጠለቅ ወዳለው ፍካት ያልተሸጋገሩ።
ሁሉም ከብርሀን ነው
የመጡት። የሚሄዱትም ወደ ብርሀን … የጉዞው አላማ ወደፊት መገስገስ ነው። ወደ ላይ መምጠቅ። ወደ ጥልቁ መስረግ። ቆም ብሎ ላስተዋለ
የትላንትናው ብርሀን ከነገው አምሳያው ያንሳል፣ ይጠባል፣ ያጥራል። ጥቂት ቆራጦች የፊተኛውን ብርሀን ለመጨበጥ፣ ያሉበትን ድንግዝግዝ
ለማፍካት እንደገና ቁፈራ ይጀምራሉ። ለትጋት ታጥቀው ይነሳሉ። ‹‹ወደ ፊት ሂድ!!›› ከ40 እና 20 ዋት ወደ 80 እና 60 ዋት
ለማደግ ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ . . . ጽኑዎቹ ይደርሳሉ። ሲደርሱ በርካታ ጨረቃዎች የጸሀይን ምግባር ሲከውኑ . .
. ጥቂት የማይባሉ ጸሀዮች በጨረቃ ሙቀት ሲመሰጡ ያስተውላሉ። በመርዛማ ጨረር ተመተው የተጎዱትን ይመለከታሉ።
በማይቆመው የህይወት
መስመር በማያቋርጠው የመኖር ጎዞ ደረስኩ ያለ ፌርማታው ላይ ይወርዳል፡፡ ልቀጥል ያለ እንዳዲስ ይሳፈራል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም
ተጓዥ ይቀንስ እንደሆን ነው እንጂ ጉዞው አይቆምም። አያልቅም፡፡ ወደ ምጡቁ ወደ ጥልቁ ጉዞ!
No comments:
Post a Comment