Thursday, August 14, 2014

አጣብቂኝ



ላለው ይጨመርለታል። ብር ላለው ወርቅ፤ ጠገራ ላለው ማርትሬዛ፤ መከራ ላለው ፍዳ ይጨመርለታል። ትላንት የተጨመሩለትን አሰበ። በዲግሪ ላይ ስራ፤ በስራ ላይ ረብጣ፤ በገንዘብ ላይ ቆንጆ ሚስት፤ በሚስት ላይ ውብ ልጅ ተጨምረውለታል። ደስታቸውን እያጣጣመ አልፏቸዋል። በሚገባ ተጠቅሞባቸዋል። ኖሯቸዋል።

ሁለተኛውን ምዕራፍ ግን በአግባቡ ማስተናገድ አቃተው። ሳቅን የሚያውቅ የልቅሶን ጣዕም ለመረዳት ከሳቁ መንፈስ በሀሳብም በምግባርም መውጣት እንዳለበት ዘነጋ። እሱ መከራ፣ ፈተና . . . ብሎ የገለጸውን የህይወት ክፍል በብቃት መተወን ተሳነው። ቀድሞ በበጎ ገጹ ሳለ“ተጨመረልኝ” ሲል በ ‘ለኔ’ የገለጸውን አሁን“ ተጨመረብኝ” በማለት በ ‘እኔ ላይ’ አደረገው።

በትላንትናው ውስጥ የገነባው የኑሮ ግንብ የእንቧይ ካብ የሚሆንባቸውን ምክንያቶች በቅደም ተከተል ደረደረ።
*ውብ ፍሬው ካለማወቅ ብርሀን ታመልጥ ዘንድ፤ ክፉውን እና በጎውን በሚያስለየው የዕውቀት ጠበል ትጠመቅ ዘንድ እንዳትችል ኪሱ ከስቷል።


*የኪራይ ህይወቱን ለማኖር የተኮናተረው ጎጆ፤ ያጠላበት ዋርካ ከተገበረበት በቀናት ስሌት ሁለት ሰላሳ ተቆጥሯል። የጎጆው ሙቀት፣ የቅልሱ ሳቅ፣ የዋርካው ዕረፍትና ሰላም በተቃራኒዎቻቸው ተወርሰዋል። የተቃርኖን ውበት ያደነቀበት ምሳሱ ጠጥሮ አልንቀሳቀስ አለው። “ ‘ብርሀን ባትኖር የጨለማ ክፋት አይታወቅም ነበር’ ይሉት ብሂል ጨለማ ውስጥ ላለነው አይሰራ ይሆን?” አቅማማ . . . 

ብርሀንም ጨለማም አንፃራዊ ናቸው። ከጨለማ የባሰ ድቅድቅ መኖሩን ሲረዳ ‘ኧረ...ተመስገን ነው!’ ለማለት ቃጥቶ ተወው። በእርሱ እውቀት የመጨረሻው የችግር ጫፍ አሁን ያለበት ነው።

ግማሽ፣ ሩብ፣ የሩብ ግማሽ ሁሉም ‘ጎዶሎ’ በሚል ተፀውኦ መሰየማቸው ፍትህ አልባ ሆነበት። በጨለማም እንደዛው። የውሳኔ ሰው መሆን ከሚያጎናፅፈው ፀጋ ይልቅ የውሳኔው ስህተትነት የሚያሳድረውን ፀፀት አመነዠከ።

ከዛሬ በፊት፡- “ አንቺ ማለት እኔ ነኝ። የኔ ማለት ያንቺ ነው። በስራ መደቡ ክፍፍል ውስጥ ሄዋንነትሽን አጥብቂ። አርሼ፣ ኮትኩቼ፣ አድኜ በማመጣው ሌማታችንን ሞልቼ አዳምነቴን አስመሰክራለሁ።” ብሎ ጥንካሬዋን፣ መነሳሳቷን . . . ያከሸፈባትን ያቺን የውሳኔ ዕለት ዛሬ ላይ ሆኖ መርገሙ እርባና እንደሌለው ቢረዳም ከመውቀስ አልቦዘነም።
ለወትሮው ከሚያወጣው ትንፋሽ በዘለገ የሳንባውን ትኩስ አየር ተፋ። በራድ የሆዱ ግለት ሲበረታ እንደሚትጎለጎል ሁሉ. . .
* * *
ጭንቀቱን ከመለከፉ በፊት እንዲህ ነበር፡- 

ከቆንጆው ጋር ውሎውን አወራ። ውጣ ውረዷን ነገረችው። የዋህ ናትና፣ ልታጣው አትሻምና
“አስታወስክ? ያንቺ ምግባር ከጓሮ አይዘልም። መስክ የኔ መቦረቂ ያናት። ያልክባትን ያኔህን አሰታወስክ?” አላለችውም።
ለዘመመው ጎጆዋ፣ ለመውቅ በመንደርደር ላይ ላለው ቅልሷ ማገር ፍለጋ ከሱ እኩል ተሰማራች። 
በመስኩ መሀል ያጋጠሟትን አሜኬላዎች ስለምታራግፍበት ዘዴ መላው ቢቸግራት ለአጋሯ አቀበለችው።
ጭንቀቱን ባትመኝም - ህሊናዋን ሸጣ ቡቃያዋን ማርጠብ፣ መንፈሷን ረስታ ምጣዷን ማሰስ አታውቅምና ጭንቀቷን አጋባችበት።

 እነሆ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ የአስተሳሰቡን ደረጃ የፈተነ፣ የአመለካከቱን ዳራ የመተረ የውሳኔ ስጥበት ውሳኔ አንጎሉን ወጥሮታል።

ያዘዘውን ሻይ ቀመሰ። መቀዝቀዙን ሲያረጋግጥ ሲያስብና ሲተክዝ ረዥም ደቂቃ መፍጀቱን ብቻ ሳይሆን . . . የአፍላ ኑሮው ንግርት እንደሆነ የገባው መሰለው። ጥፍጥናውን አጣጣመ - ጉድለት አለበት። 

የትንቢት ተናጋሪው ቃል አስደሳችም ይሁን አሳዛኝ ሲተገበር ማየት ዕምነትን ያጎናጽፋል። እናም ጓጓ። ቅዝቀቃዜን  ከስክነት፤ ጉምዘዛውን ከልኬት ጋር አቆራኝቶ በጎውንና ጥሩውንም አብሰለሰለ።

“እንዴት?” ያላል ደጋግሞ
“እንዴት ልትነግረኝ ቻለች?  .  .  .  እንዴት በጎ ውሳኔ ላይ እደርሳለሁ?  .  .  .  እንዴት ደፍሬ እነግራታለሁ?  .  .  .  ያ መርዛም ገመሬስ እንዴት ቢንቀኝ እንዴት ቢደፍራት ሀሳቡ በልቡናው አደረ?  .  .  . እንዴት? እንዴት?” በርካታእንዴቶችንአፈለቀ።

ለአንዱም በቂ ምላሽ አልነበረውም። 

የቆንጆው ጥያቄ ግልጽ ነው። ግልጽ መልስ ሊያገኝለት ግን አልቻለም። ሊኖሩ የሚችሉት ሁለት ምላሾች ናቸው።
“አድርጊውና ችግርን እንግደል። በውበትሽ መኖርን እናርዝም” አለያም
“ ሁሉም ይቅርብንና በጉስቁልናችን እንቀጥል።”

ምርጫ ለሰነፍ በጎ መንገድ ነው። ደመነፍሱ ያዘዘውን ይመርጣል። ብልህ ግን ግራቀኙን ያገናዝባል። ሁለት ምርጫ ያለው ሰው ሁለቱም ምርጫዎች ላይዋጡለት ይችላሉ። መፍትሄው ሦስተኛ ምርጫ ማዘጋጀት አይደለም። የተሻለ አራተኛ ምርጫ ቢኖርም የተሻለ የጎን ጠንቅ አስከትሎ እንጂ ብቻውን አይመጣም። መፍትሄው ጥያቄውን አለመጠየቅ ነው። ለዚህ ደግሞ ረፍዷል።

ቆንጆው ወይን ነው ስሟ። በፍቅራቸው ማገርነት፣ በዋርካቸው ከለላነት፣ እርሱ ግንዷ ሆኖላት በርሱ ትከሻ የቆመች። እርሷ ግርማ ሆናለት ማስጠላቱን የጋረደች። እርሱ ያለርሷ ተራእንጨት እርሷም ያለርሱ ትቢያ ናቸው።

ወይን እልፍ ቅርንጫፎች እጅግ ብዙ ቅጠሎች አሉት። ቢሆንም እያንዳንዷ ቅርንጫፍ እያንዳንዷ ቅጠል የአንዱ ግንድ ብቻ ናት። ለሁለት ዓይን ሁለት ራስ እንደማያስፈልገው ሁሉ ለእልፍ ውበት ለእልፍ ጥፍጥና ባለቤቷ ወይን ሁለት ግንድ ሊኖራት አይችልም። በአንድ ግንድ ተንጠልጥላ በርሱ ኖራ እርሱን አድምቃ ታልፋለች እንጂ . . .
“ውሳኔ! ውሳኔ! ውሳኔ!” 

አእምሮውም ልቡናውም በጋራ ዘምረውታል። ቆንጆውም
“ግንዱ ከዋርካው ያለው ዝምድና ከተቆራረጠ፤ ከማገሩ ከተላቀቀ . . .  ጥንካሬው ይሸረሸርና ውብነታቸው ይጠፋል። ትቢያ ልብሳቸው ይሆናል። ስለዚህ ወስን!” ብላዋለች። 

ትዕዛዝ መስጠት የመቀበልን ያህል አይከብድምና፣ ትዕዛዝ መቀበል የመስጠትን ያህል አይቀልምና አልቻለም። የመደምደሚያ ውሳኔ እስካሁን አላገኘም።

በኋላስ? በርካታ በኋላዎች ቢኖሩትም ምርጫዎቹን ማስተናገድ የሚችል አልመሰለውም። 

***
አሁን ፊትለፊትዋ ነው። ማንንም ፈርቶ በማያውቀው መልኩ ፈራት። ‘ፍርሀት የማይፈልጉትን መሸሽነው!’ ሊሸሻት አይሻም፣ ልሸሻት አይችልም፣ ጥያቄዋን ሊሸሽ አይቻለውም። ፍርሀት ብቻ ነው የፈራት። በዚች ሰዓት ፍርሀቱ መርበትበቱ ነገሰበት።

ወንዞች - “ያቺን ወይን አርሻለሁ” በመባባል የተጣሉባት። 
አትክልተኞች - እርሷን የመንከባከባቸውን ዜና የደነፉባት። 
ፀሀይ - “ምቾት የመሆኔ ምስክር” ስንል የኮራችባት። 
አፈር - “ሁሉን ነገሬን ሰጠኋት” ያለቻት። 
ከመሰሎቿ እስከ የበላዮቿ፤ ከታናሾቿ እስከ የታናሽ ታናሾቿ የቀኑባት ወይን ከስማለች። ጠይምነቷ ደምቆ ጨለማ ለብሳለች። ፈርጦቿ በሀዘን ወይበዋል።

“ምን ብዬ ልንገራት?” ጨነቀው። 

ሁሉም ነገር ሀ እና ፐ አለው። የሁላችን ባለንብረት ከሆነው ገዢ በስተቀር አልፋ ካለው ኦሜጋው ከእለታት በአንዱ ቀን ነው። የጭንቀቱ የፍጻሜ ሰዓት ከዘለአለም ረዘመበት

“ሁሉን በቁጥጥርህ ስር አድርጌልሀለሁ። ግዛ። ንዳ።” ያለውን ገዢ ትክክለኛነቱን መጠራጠር ቃጣው። 
“እኔ ራሱ የርሱ ሆኜ እንዴት?” እያለ ሲፈላሰፍ ሹክሹክታዋ አባነነው።

“ምን ትላለህ?” አለችው።

“እ!” ተደናገረው

ሌማቷን ለመሙላት፤ ውቧን ለመንከባከብ ስትል በዱር በገደሉ በዘለለች ጊዜ
“ወይንነትሽ ማርኮኛልና ያጣጣምኩሽ እንደሆን አዱኛ በጎጆሽ ይሞላል።”
ያላትን መረን ገመሬ ምላሽ ብታጣለት። እሺታዋን እምነቷ እንቢታዋን ችግሯ ቢወጥሩባት
“ወስን! ከቃልህ እንዳልወጣ ማተቤ፣ ተሸሽጌህ እንዳልፈቅድ ተፈጥሮዬ ስለሞገተኝ ወስንልንና ንገረኝ?”
ላለችው ጥያቄ የሚሆን ምንም ምላሽ የለውም። ምንም . . .

No comments:

Post a Comment