‹‹ከቁጥሮች መካከል የመጨረሻውን ባዶ ደረጃ የያዘችው ‘0’ ናት፡፡ አንተም በሰው ልጆች የዕውቀት፣ የዐስተሳሰብና የዐመለካከት መስፈርቆች ስትገመገም ማርክህ ዜሮ ቢሆን ’ዋጋ የለኝም’ አትበል፡፡
ያቺ . . . የቁጥሮች ሁሉ አናሳ ዜሮ በሙሉ ቁጥሮች ስሌት ወቅት ቀዳሚውን የፊት ወንበር
ትቆናጠጥ እንጂ፣ ዋጋ ባላቸው የመቁጠሪያ ቁጥር መገልገያዎች እርሷን ከፊትለፊት ቦታ ያስቀደመ ትርጉም አልባ ድምሮችን ከማንኳተቱ
በተጓዳኝ አላዋቂነቱን ያሳብቃል፡፡ ታዲያ . . . አንተና መሰሎችህ አጠቃላይ ሰዋዊ ውጤታችሁ ዜሮ ሆኖ ሳለ ከሁሉም ፊት መቆማችሁ፣
ሙሴነትን መተግበራችሁ ይቅርና ለማሰብ መነሳሳታችሁ ራሱ ከስህተት በላይ ነው፡፡
ዜሮ ከፍ ካሉ ቁጥሮች መካከል አለያም ከበስተኋላ በተከታይነት ስትቆም የምታሳየውን ትርጉም
አዘል ለውጥ አስተውል፡፡ ራስ በመሆን ብቻ ሳይሆን ጭራ በመሆንም ግዙፍ ለውጥ አምጪ ታሪክ መስራት ይቻላል፡፡ ራስህን ሁን፡፡ ››
በተጨማደደው እራፊ ወረቀት ላይ በግዴለሽነት የተጫጫሩት
ፊደላት ባፈጠጠበት መስታወት ላይ የተነቀሱ ያህል ደጋግሞ ያነባቸዋል፡፡ ያስባቸዋል፡፡
‘ኳ - ኳኳ- ኳኳኳ’ ድንገተኛ የበር ኳኳታ ጉልህ
ምልከታውን እንዲያቆም ፈረደበት፡፡ ‘’ሰው አለ’’ አለ፡፡
ድምጹ መደንገጡን ያሳብቃል፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት
እዚሁ ቦታ ላይ ቆሻሻ ታብሶበት - ከቆሻሻዎች ጋር ተጥሎ ያገነው ብጫቂ ወረቀት ያሰፈረውን ርዕሰ ጉዳይ እያሰላሰለ ነበር፡፡
ፍጥነት በተሞላበት ሁኔታ እጆቹን ተጣጠበ፡፡ አብሮት የከረመ ሀሳቡን እያመነዠከ
የበሩን መሸጎሪያ አላቀቀ፡፡ መፀዳጃ ቤቱን ለሌላ ተረኛ ለቀቀ . . .
No comments:
Post a Comment