Monday, November 17, 2014

ከብዙ ዓመታት በኋላ የሚነገር የከብዙ ዓመት በፊት ታሪክ



መግቢያ


ጥቂት የማይባሉ አያሌ ዘመናትን ወደፊት ተሻግረን ከቀናቶች መካከል ባለ የተለመደች አዘቦት ቀን ላይ ነን፡፡ ተንጠራርተን እያስተዋልናት ባለችው በዚህች ተራ ቀን  ድሮ ምን ይመስል እንደነበር ልንቃኝ ነው፡፡ በአሁን የጊዜ ፈረስ ተፈናጠን ነገን በዛሬ ልናነፃፅር . . .


ትዝታ አይደለም፡፡ ትዝታ የኖሩትን በምናብ መድገም ነው፡፡ ከትውስታ ጓዳም ከህልውና መድረክም ሊሰርዙት አይቻልም፡፡ መከሰቱም ማለፉም የተረጋገጠ ነው፡፡

 
ትንቢት አይደለም፡፡ ትንቢት ያልኖሩትን መገመት ነው፡፡ ስምረቱንም ክሽፈቱንም ማረጋገ ከባድ ነው፡፡
ይህ ከሁለቱም ይለያል፡፡ ሁለቱንም መሳይ ገፅ አለው፡፡



 
በህይወት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ እየተገፋን ከዓመታት በኋላ ደርሰን ስለ ታሪክ ከደሰኮርን የንግግራችን ኬላ ዛሬ ነው፡፡ ነገም ነው፡፡
ከሰፊው የህይወት ባህር በማድጋችን ጠልቀን ያስቀረነውን ናሙና ቤተ - ሙከራ እንዲሁም ቤተ - ምርመራ እንዲሁም ቤተ - ትንተና ውስጥ ጨምረን የተሸከማቸውን ንጠረ ውህዶች የገለጥንበት ጦማር እንዲህ ይነበባል፡፡

ዝርዝር መግቢያ
እንቅልፍ፣ ጭንብል፣ __________፣_______________

እንቅልፍ- ሁሉም አንቀላፍቷል፡፡ ምሁሩም መሀይሙም ትንሹም ትልቁም፤ ወንዱም  ሴቱም ተኝቷል፡፡ ሲበላም ሲሰራም ሲዝናናም በእንቅልፍ ልቡ ነው፡፡

ከፊሉ እንደተኛ አያውቅም፡፡ የወለዱት ተኝተው ነበር፡፡ ያዋለዱት ተኝተው ነበር፡፡ ያሳደጉት ተኛተው ነው፡፡ መምህሮቹ ተኛተው ነው ያስተማሩት፡፡ ስለዚህ መንቃትን አያውቅም፡፡

ገሚሱ ለመንቃት የማይሻው ሆነ ብሎ ነው፡፡ ከነቃ እንደሞተ ያውቃል፡፡ ከነቃ ህይወት አልባ እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ እናም ‹‹መሞቴን አልሰማሁም አሉ . . .›› ብሎ ራሱን ለመሸንገል እንቅልፉ ውስጥ ይቀበራል፡፡

ጭንብል- አልፎ ሂያጁ ሁሉ ባለመነጽር ነው፡፡ ዓይኑ ላይ የሰካው እይታን የሚያደበዝዝ መሳሪያ አለው፡፡ ደማቁን የማያፈካ ብራን የሚያደነግዝ ግዑዝ ቁስ . . . የውጭ እይታውን የቀነሰው የውስጥ እይታውን ለመጨመር አይደለም፡፡ ወደውስጥም ወደውጭም አያይም፡፡

አይኑ ላይ ብቻ ሳይሆን አእምሮው ላይ የሰካው ሀሳብን የሚያስጥል፣ ተመስጦን የሚያጎድል፣ ጥሞናን የሚያናጥብ መሳሪያም አለው፡፡ ቴክኖሎጂ ይባላል፡፡

 (  .  .  . ይቀጥላል)









No comments:

Post a Comment