ከዳዊት ዓርአያ
/አጭር ልቦለድ /
ብርሀን ባለበት የጨለማ ግርማ ይገፈፋል። ጨለማ ሲኖርም የብርሀን ጸጋ ስፍራውን ያስረክባል። ይህ ክፍል እንደዚያ አይደለም
፡፡ ብርሃንም ጨለማም ነግሰውበታል። ሠሃራም ሳይቤሪያም፣ ወተትም ቡናም ያልሆነ ማኪያቶ ክፍል ነው።
ጡንቻውን በስፖርት ያደለበ፣ አንጎሉን በዕውቀት ያጣበበ፣ የሰውን ልጅ ከትንኝ ነፍስ የሚያስተካክል፣ ራሱን ከትቢያ በላይ የሚያበክት፣ አማኝ ከሀዲ ተጠራጣሪ… ከያይነቱ ተውጣጥቶ የተጠራቀመ የ’ሰው’ ዓይነት አለበት።
ከጥፋታቸው እንዲማሩ ወይንም በወንጀላቸው እንዲማረሩ የሚታሸጉት ይህ ስፍራ ከአንስታይ ፆታ በቀር የእድሜ ገደብ የለበትም። የትምህርት፣ የኑሮ፣ የዕውቀት፣ የእምነት፣ የአስተሳሰብ ልዩነት ቢኖርም ኗሪዎችን ከመግባባት አያግድም። ባለመግባባት ከሚፈጠር ግጭት በላይ በመመሳሰል የሚፈጠረውን ’ሰላም’ ሁሉም ተገንዝቧል። መስሎ አስመስሎ ቀን ይገፋል። በተመሳሳይ ወግ ተመስጦ ተመሳሳይ ሳቅ ይስቃል።