Monday, December 7, 2015

ያለመግባባታችን ምንጭ በጣም መግባባታችን ነው!

አየሽ እኔ እና አንቺ በጣም ተግባብተናል፡፡ ተገባብተናል፡፡ እኔ አንቺ ውስጥ. . . አንቺም እኔ ውስጥ. . . አሳምረሽ ገብተሸኛል፡፡ በትክክል ገብቼሻለሁ፡፡ ዘላቂ መግባባታችን የወለደው አለመግባባት እዚህ ጋር ይፀነሳል፡፡

ሀሳቤን ብቻ ሳይሆን የሀሳብ መንገዴን አግኝሽዋል፡፡ የውሸቴን መነሾ እስከ መድረሻና ውጤቱ መናገር ሳልጀምር አውቀሽዋል፡፡ ፊቴ ላይ የሚሯሯጠው ደም ካዘለው ስሜት በላቀ በልቦናዬ
ያፈንኩትን ሀቅ መገንዘብ ችለሻል፡፡

Wednesday, August 12, 2015

የማስታወቂያዎቻችን ነገር

‹ሱዛን ፎርማን› የተባሉ ጸሐፊ ‹‹The Media of Advertising›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ ማስታወቂያ አጀማመር ሲገልጹ 

‹‹ማስታወቂያ ስረ መሰረቱ በጥንታዊት ሮም መኳንንቶችን ለማስደሰት የሚደረጉ ድብድቦች /Gladiators/ በታላላቅ አደባባዮች የሚካሄዱ መሆኑን የሚያስተዋውቁ፤ በመካከለኛው ዘመን የሞት ፍርድ በአደባባይ የሚፈፀም መሆኑን የሚያመላክቱ፤ በአሜሪካ ጠረፍ በትልቁ ተፅፈው የሚንጠለጠሉ የ ’ወንጀለኛ ይፈለጋል’ ማሳሰቢያዎች ናቸው፡፡›› ይላሉ፡፡

በግብጽ በ 3200 ዓ.ዓ አካባቢ በተሰሩ የማምለኪያ ህንፃዎች ላይ ማንኛው ንጉስ እንዳስገነባው የሚጠቁሙት ጽሁፎች ከማስታወቂያ ይመደባሉ የሚሉ ምሁራንም አሉ፡፡

በታሪክ የመጀመሪያው ተብሎ በ (Encyclopedia Britanica,Vol 1 ,180) የተመዘገበው የጽሁፍ ማስታወቂያ 

‹‹ሼም የተባለው ባሪያ ሃፑ ከተሰኘው አሳዳሪ ተሰውሯል፡፡ ሃፑ የቴቢስ መልካም ዜጎች ሁሉ ይህን የጠፋ ባሪያ ቢመልሱለት ይወዳል፡፡ ባሪያው ባለቡናማ ዓይን ነው፡፡ ያለበትን አካባቢ ዜና ላመጣ ግማሽ የወርቅ ሳንቲም ይሰጠዋል፡፡ ሼምን ወደአሳዳሪው ለሚመልስ ደግሞ እንደፍላጎቱ ልብስ የሚደሸመንለት ሲሆን ሙሉ የወርቅ ሳንቲምም ይሰጠዋል፡፡››

የሚል ሲሆን ከ 3ሺህ ዓመት በፊት በፓፒረስ ላይ የተጻፈ መሆኑ ተገልጧዋል፡፡
በዘመናዊና በተደራጀ መልኩ ከቀረቡት ማስታወቂያዎች በፊት ግን ሰዎች ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ ማስታወቂያቸውን ይናገራሉ፡፡ በሐገራችንም ይህ ተግባር የተለመደ ነበር

Tuesday, July 14, 2015

‹ስለ ኢትዮጵያ ስል ተኮላሽቻለሁ፡፡›

‹‹ፍቅር ይዞህ ያውቃል ለመሆኑ?››
‹‹አዎን››
‹‹ከማን ጋር?››
‹‹ከኢትዮጵያ››
‹‹አሃ! የፍቅረኛህ ስም ኢትዮጵያ ነበር?››
‹‹አዎን!››
‹‹ለምን ከኢትዮጵያ ጋር ተለያያችሁ?››
‹‹መንግስቱ ሃይለማርያም እና ድርጅቱ ትግላችንን እና ኢትዮጵያ ሀገራችንን ገደሏት››
‹‹ዋለልኝ! ለምን ታሾፍብኛለህ? ምንድነው የምትቀባጥረው?››


ከጭምትነቱ ወጥቶ ጣራው እስኪሰነጠቅ ድረስ ሳቀ፡፡ ቲያትር የሚሰራ ነው የሚመስለው፡፡ ለደቂቃዎች ሳቁን አላቆመም፡፡ ሳቁ ግን የደስታ ሳይሆን የንዴት እንደነበር ያስታውቃል፡፡ አይኖቹ እና ፊቱ ቀሉ፡፡ ደምስሮቹ በአንገቱ እና በፊት ገጹ ላይ ተገታተሩ፡፡ የመጨረሻ ጥያቄዬ በጣም እንዳበሳጨው ተረዳሁ፤