‹‹ከቁጥሮች መካከል የመጨረሻውን ባዶ ደረጃ የያዘችው ‘0’ ናት፡፡ አንተም በሰው ልጆች የዕውቀት፣ የዐስተሳሰብና የዐመለካከት መስፈርቆች ስትገመገም ማርክህ ዜሮ ቢሆን ’ዋጋ የለኝም’ አትበል፡፡
ያቺ . . . የቁጥሮች ሁሉ አናሳ ዜሮ በሙሉ ቁጥሮች ስሌት ወቅት ቀዳሚውን የፊት ወንበር
ትቆናጠጥ እንጂ፣ ዋጋ ባላቸው የመቁጠሪያ ቁጥር መገልገያዎች እርሷን ከፊትለፊት ቦታ ያስቀደመ ትርጉም አልባ ድምሮችን ከማንኳተቱ
በተጓዳኝ አላዋቂነቱን ያሳብቃል፡፡ ታዲያ . . . አንተና መሰሎችህ አጠቃላይ ሰዋዊ ውጤታችሁ ዜሮ ሆኖ ሳለ ከሁሉም ፊት መቆማችሁ፣
ሙሴነትን መተግበራችሁ ይቅርና ለማሰብ መነሳሳታችሁ ራሱ ከስህተት በላይ ነው፡፡
ዜሮ ከፍ ካሉ ቁጥሮች መካከል አለያም ከበስተኋላ በተከታይነት ስትቆም የምታሳየውን ትርጉም
አዘል ለውጥ አስተውል፡፡ ራስ በመሆን ብቻ ሳይሆን ጭራ በመሆንም ግዙፍ ለውጥ አምጪ ታሪክ መስራት ይቻላል፡፡ ራስህን ሁን፡፡ ››