Friday, April 11, 2014

መናጆ


በርካታ በጎች ያሉት ሰው አለ እንበል። ካሉት በጎች መካከል አንዷን ነጥሎ መሸጥ ፈልጓል። ለመሸጥ ያሰባትን በግ ከመንጋዋ ነጥሎ ለመውሰድ ግን አይቻለውም፤የበግ ተፈጥሮ እንዲያ አይደለማ . . .በግ ተከታትሎ ነው መንገድ የሚወጣው - በግ በደቦ ነው የሚጓዘው። በግን በአዲስ ጎዳና ለማራመድ የከጀለ ማንም ሰው የሚጠበቅበት ከመካከላቸው አንዷን ጎተት አድርጎ በታቀደው ቦታ እንድታልፍ ማድረግ በቂ ነው። ከዚያ የተቀሩት ተግተልትለው ያልፋሉ። ተከታትለው ያዘግማሉ። 

ስለዚህ ያ ሰው  - ያ በግ ነጋዴው ግለሰብ - የሚሸጠው አንዷን በግ ብቻ እንደሆነ እያወቀ . . .  ቀሪዎቹን ይዞ እንደሚመለስ እያወቀ . . . ሌሎች ሶስት አራት አጃቢዎችን (መናጆ) ይዞ ገበያ ይወጣል።  የምትሸጠው በግ የታለመላትን ተግባር እስክታከናውን የተቀረው ጀሌ የገባችበት ሲገባ የወረደች የወጣችውን ሲመላለስ ይውላል። ተሻጯ ፈላጊ እስክታገኝ ይከተላል። ይህ ተግባር የሚያቆመው መናጆ አስከታይዋ አላማዋን ከግብ እስክታደርስ ነው። ሌላ ተሻጭ - ሌላ መናጆ አስከታይ እስኪፈጠር የተቀረው በግ ወደ በረቱ ይመለሳል።


ይህንን ተግባር በኑሯችን ላይ እያስተዋልነው ያለን እየመሰለኝ ነው። በሰው ሀሳብ እየተወዘወዝን፣ በሰው ኑሮ አቅል እያጣን፣ በሰው ጌጥ እየተሽቀረቀርን፣ . . . እየመሰለኝ . . .  ከትላንት በስትያ በሰሜን፣ ትላንት በምእራብ፣ ዛሬን በደቡብ ሀሳብ የምንናጥ አቅጣጫችንን የእለቱ ንፋስ የሚወስንብን . . . እየመሰለኝ . . .  በፖለቲካ ማዕበል ተንጠን እፎይ ሳንል የሀይማኖት ሱናሚ ጠራርጎ አቅጣጫ የሚያስቀይረን፤ በዘረኝነት ትብትብ ስንተበተብ ከርመን የዘለፋ፣ የስም ማጥፋት፣ ነፋስ የሚጠራርገን . . . እየመሰለኝ . . . አንዱ አላማውን እስኪያሳካ ጉዳይ አስፈጻሚ የሚያደርገን በራሱ ቦይ የሚያፈሰን . . .እየመሰለኝ . . .


1 comment: