Monday, August 26, 2013

አበል ለዘላለም ትኑር!


የሀይስኩል ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ነው። በእድሜ ገፋ ያሉት መምህር እጃቸው በቾክ ተጨማልቆ - ብላክቦርዱን መለየት በማይቻሉ እና በተዘበራረቁ መስመሮች፣ ቅርጾች፣ ቁጥሮች፣ ፊደላት አጨማልቀው እያስተማሩ ነው። እያስረዱ ነው። የተማሪው ፊት ላይ የተመከቱት ሁኔታ ግን እንዲቀጥሉ የሚገፋፋ አልነበረም። ተማሪው ፊት ላይ ድብርት ይነበባል። መምህሩ በድንገት ማስረዳታቸውን አቁመው ያልተለመደ ጥያቄ ጠየቁ

“ይህንን ትምህርት መማራችሁ ለምን ይጠቅማችኋል?” ጉዳዩ በክፍሉ መነቃቃትን ፈጠረ። “ግን ይሄ ሳብጀክት ለምን ይጠቅማል?”

መምህሩ እጅ ያወጣን ተማሪ ብቻ ሳይሆን አርፎ የተቀመጠንም ማፋጠጥ ይዘዋል።
“ይህንን ሳብጀክት ለምን ትወስዳላችሁ? ህይወታችሁ ላይ ምን ይጨምራል?”
ነገርየው አሳፋሪ ቢሆንም ከ50 የሚበልጠው እና ደብተሩ ላይ እየጻፈ፣ መፅሀፍ እያነበበ፣ ሰዓት ጠብቆ እየገባ፣ እያጠናና እየተፈተነ የሚወስደውን ኮርስ ምን እንደሚጠቅመው አያውቅም።
መምህሩ ንዴት፣ ብስጭት፣ መገረም እጠየተነበበባቸው ይዘውት የመጡትን ጓዝ ሸክፈው ወደመውጫው በር አመሩ። 



ክፍሉን ሙሉ ለሙሉ ከመልቀቃቸው በፊት ፊታቸውን ወደኛ መልሰው . . .     “ቢያንስ ‘ላንተ ደሞዝ እንዲከፈልህ’ አትሉም?” አሉ።        ንግግራቸውን ተከትሎ የተሰማው የተሜ ሳቅና ሁካታ አጅቦ ሸኛቸው። ከክፍሉ ወጡ።

ይህ ነገር ትዝ ያለኝ አንድ ስብሰባ ወይም ስልጠና ወይም ስብሰባዊ ስልጠና ላይ ተቀምጬ ነው። አሰልጣኙ ይናገራል ግን ከልቡ አይደለም። ሰልጣኑ ቦታ ቦታውን ይዞ አሰልጣኙን ይሰማል ግን አያደምጥም። አሰልጣኙ ሀሳቡን ሰዎች ላይ ለማጋባት ይጥራል ግን የሚያምንበት አይመስልም። ሰልጣኙ አስተያየት ይሰጣል ልቡናው ግን ከቤቱ ውስጥ የለም።

በዚህ ጊዜ ነው አንድ ጥያቄ ራሴን የጠየኩት “ይህ ስልጠና ለምን ይጠቅማል?” መልሱ ብዙ አልከበደኝም የ10ኛ ክፍል መምህሬ እንዳሉት ስልጠናው የሚጠቅመው <<አበል ለማግኘት ነው!>> የዚህኛው የሚለየው  አበሉን የሚያገኙት መምህሩም ተማሪውም ናቸው ። ስለዚህ  ማንም ሰልጣኝ በምክንያትም ያለምክያትም አይቀርም። ያኛውን ግን መቅረት ባይፈቀድ እንኳን መምህሩን አውኮ በረባሽነት ስም ነፃነትን ማወጅ ይቻላል። እዚህ እንደዛ የለም ምክንያቱም ተከፋዩ መምህሩም ተማሪውም ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ሰልጣኝ። ባይሰማም ይመጣል። ባይስማማም ይቀመጣል። መጨረሻ ላይ የሚሰጠውን ‘ተስማሚ ነገር’ (አሞሌ) እያሰበ . . . . ባያነብም ይጽፋል።  የአለቆችን ትኩረት እየሻተ . . . ባይገባውም፣ ባይገባውም ሀሳብ ይሰጣል። በአንደበቱ ደላይነት ‘ጭንቀወላቱን’ (ብቃቱን) ለማሳየት እየጣረ፤ ሹመት እየሻተ፤ ክብር እያሸተተ  . . . የሚያነበው እንደሌለ ቢያውቅም ሪፖርት ይጽፋል።  እንደማይተገበር ቢያውቅም እቅድ ያወጣል። ነገ ‘ይሻር’ ብሎ ድምጽ እንደሚሰጥ ቢረዳም ዛሬ ‘ይተግበር’ ብሎ እጁን ያወጣል። የ’ይገንባም’ የ’ይናድም’ ባለታሪክ ይሆናል። ዜማው ቢጎረብጠውም፣ ስንኙ ለነፍሱ ባይደርስም ይዘምራል። ገብቶት የሚያቀነቅነው ግን “አበል ለዘላለም ትኑር” የሚለውን ዜማ ነው።

ተጠባባቂ አትሌት ለማጓጓዝ በጀት የሚያንሰው ፌዴሬሽን ከ30 በላይ የስራ ሀላፊዎችን ምግብ፣ መኝታ፣ አበል ችሎ ባህር ማዶ ይልካል።

ለዓመታዊ ክብረበአሉ መደገሻ መቶሺች የሚመድብ ፋብሪካ የሰራተኞች ደሞዝ ለመጨመር አሰራሩ አይፈቅድለትም።

የተበላሹ መንገዶችን ጠግኖ ለመንቀሳቀስ ምቹ እንዲሆኑ ለማስቻል በጀት ያልጸደቀለት የሚመለከተው አካል /’የሚመለከተው አካል’ የምትለዋ ቃል ግን ላለመነካካት እንዴት አሪፍ ናት/ ብዙ ሺህ ብሮች መድቦ በመንገድ አጠቃቀም ምርጥ የተባለች አውሮፓዊት ሀገር ላይ ልምድ ልውውጥ ያዘጋጃል። ለአዘጋጅ ኮሚቴው፣ አዘጋጅ ኮሚቴው ያዘጋጀውን ለሚቆጣጠረው የቁጥጥር ኮሚቴ፣ እንዲሁም ነገሮች ሁሉ በስርአት መከናወናቸውን ለሚታዘበው የስነስርዓት ኮሚቴ አበል የሚሆን በጀት ከየትም ብሎ ይከፍላል። ብቻ ‘አበል ለዘላለም ይኑር!’

በወጣቶች ጉዳይ ላይ ልስራ ያለ ተቋምም ‘ወጣቱና የንባብ ልምድ’ የሚል አውደጥናት 3 አነስተኛ ቤተመፃህፍት በሚገነባ ገንዘብ ያዘጋጃል።

በመጨረሻም ፡- የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ እሱ ስለጻፈ ብቻ የሚመጣ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሌለ እያወቀ ወረቀት ብእር እና የአንባቢን ጊዜ ያባክናል።አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጣ

No comments:

Post a Comment