Wednesday, September 6, 2017

ከ ‹ፍቅር እስከመቃብር› የተነሱ ሌሎች ኪነ-ጥበባዊ ሥራዎች



በዘመን እና ጥበብ መጽሔታችን የሰኔ ወር እትም ‹ተወራራሽ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች› በሚል ርዕስ ሥር መጨዋወታችን ይታወሳል፡፡ መነሻቸውን አስቀድሞ ለታዳሚ በደረሰ የኪነ- ጥበብ ውጤት ላይ ያደረጉ ሥራዎችን በወፍ በረር ቃኝተናል፡፡ ያነሱትን የጥበብ ውጤት፤ ቀድሞ የነበረውን እንደነበረ በሌላ የጥበብ ዘውግ፤ ወይም ነባሩን ይዘው በሌላ ዓዲስ የሀሳብ መንገድ የተገለፁትን ዘርዝረናል፡፡ በእግረመንገድ ያስተዋልነውን፣ በትውስታ ማህደራችን ቀድመው የተከሰቱልንን ብቻ አነሳስተናል፡፡

ወጋችንን ስናሳርግ ‹ፍቅር እስከ መቃብር› የተሰኘው ረዥም ልብወለድ ላይ ተመስርተው የተሠሩትን ለማነሳሳት ቃል ገብተን ነበር፡፡ ቃል አክባሪ ሆነን የዛሬውን ዋና ርዕሰጉዳይ ከመጀመራችን በፊት ግን ሳንጠቅስ ያስተረፍናቸውን እና በሰኔው እትም ያዛነፍናቸውን እውነታዎች እናክም፡፡ በዚያውም ሐምሌ ጠብቁን ብለን ነሐሴ ላይ ስላመጣነው ክፍል2 ጽሁፍ እና ስለተፈጠረው ስህተት እኔ እና የመጽሔቱ አዘጋጆች የየድርሻችንን አንባቢዎቻችንን ይቅርታ እንለምናለን፡፡