(ንዑስርዕስ ) ወደብርሀን
የምንገኘው ብርሀን
ከሚታደልበት ብርሀን ውስጥ ነው። የብርሀን ማነስ ድንግዝግዝን ካወፈረበት ዓለም። ብርሐን ማለት ዕውቀት ነው። ዕውቀት ማለት እውነት፣
እውነት ማለት ውበት ማለት ነው። ሐቀኛ ውበት ከልከኛ እና ከቀና እውነት ይወለዳል። ውበት ሁሉ እውነት አይደለም። እውነት ሁሉ
ውበት አይደለም። በሀቅ ካባ የተጀቦነ - በበግ ለምድ የተሸሸገ ተኩላዊ እውነት አለ። በሽንገላ ከንፈር ማንነቱን የተነጠቀ እውነት
አለ። ብልጭልጭ የጋረደው። አርቴፊሻል ውበት አለ በብልጭልጭ ብዛት፣ በወከባ ብዛት፣ በግርግር ብዛት ውበት ማማ ላይ የተሰቀለ።
የድንጋሪው ማጥሪያ ወንፊት ማስተዋል ነው። ማስተዋል። በመገለጡ ውስጥ ያለውን ቅኔ መፍታት።
ግስጋሴው ወደፊት ነው።
ፈትለፊቱ ድንበር የለውም። ጫፉ መሻት ነው። ዕውቀትን መሻት። ጥልቀትን፣ ምጥቀትን፣ ስፋትን፣ ርዝመትን መሻት . . . ሁሉም በፍላጎት
ነጻ ፈቃድ የሚወለዱ፤ በጥረት እልህ አስጨራሽ ትጋት የሚያድጉ እና የሚጎለምሱ ነገዎች ናቸው። የዕውቀት ኬላ ማማዎች . . . ያልደረሱበትን፣
ያመረመሩትን እየጓጉ የሚናፍቁበት፤ የያዙትን አጣጥመው የተሻለ የሚማትሩበት፤ እንደመሰላል ያለ የከፍታ አጋዥ። ተንጠራርተው እየጨበጡ።
የጨበጡትን ሳይረግጡ ይልቁንም ባለው ላይ እየደመሩ። የመንገዱ መቋጫ እርካታ ነው። ደረስኩ፣ በቃሁ፣ ነቃሁ፣ በሰልኩ፣ ባሉበት ቅጽበት
የጉዞው ምዕራፍ ይዘጋል። ‘ብርሀናማ ጨለማ’ን ‘ወርቃማብርሀን’ ነው ብሎ በማምለክ ቅያስ ውስጥ መዳከር ይጀመራል። . . .