Friday, April 11, 2014

መናጆ


በርካታ በጎች ያሉት ሰው አለ እንበል። ካሉት በጎች መካከል አንዷን ነጥሎ መሸጥ ፈልጓል። ለመሸጥ ያሰባትን በግ ከመንጋዋ ነጥሎ ለመውሰድ ግን አይቻለውም፤የበግ ተፈጥሮ እንዲያ አይደለማ . . .በግ ተከታትሎ ነው መንገድ የሚወጣው - በግ በደቦ ነው የሚጓዘው። በግን በአዲስ ጎዳና ለማራመድ የከጀለ ማንም ሰው የሚጠበቅበት ከመካከላቸው አንዷን ጎተት አድርጎ በታቀደው ቦታ እንድታልፍ ማድረግ በቂ ነው። ከዚያ የተቀሩት ተግተልትለው ያልፋሉ። ተከታትለው ያዘግማሉ። 

ስለዚህ ያ ሰው  - ያ በግ ነጋዴው ግለሰብ - የሚሸጠው አንዷን በግ ብቻ እንደሆነ እያወቀ . . .  ቀሪዎቹን ይዞ እንደሚመለስ እያወቀ . . . ሌሎች ሶስት አራት አጃቢዎችን (መናጆ) ይዞ ገበያ ይወጣል።  የምትሸጠው በግ የታለመላትን ተግባር እስክታከናውን የተቀረው ጀሌ የገባችበት ሲገባ የወረደች የወጣችውን ሲመላለስ ይውላል። ተሻጯ ፈላጊ እስክታገኝ ይከተላል። ይህ ተግባር የሚያቆመው መናጆ አስከታይዋ አላማዋን ከግብ እስክታደርስ ነው። ሌላ ተሻጭ - ሌላ መናጆ አስከታይ እስኪፈጠር የተቀረው በግ ወደ በረቱ ይመለሳል።

Wednesday, April 9, 2014

ለሚመለከተው ሁሉ

አዎ አንተ የተማርክ ነህ!  ከአንድም ሁለት ሶስት ተቋማት ውስጥ ገብተህ አንደኛ ፣ ሁለተኛ ፣ እያልክ ዲግሪዎችን ደርድረሀል። ‘አንቱ’’ ተብለሀል። ሀገርህ ካሏት ’ ምሁራን’ መካከል ቀዳሚዎቹ ረድፍ ላይ አለህበት።

አዎ አንተ አንባቢ ነህ! ከትምህርት ቤት ከወጣህ ማግስት ጀምሮ በአዲስ ሀሳብ ውስጥህን ለመሙላት፤ የያዝከውን ጅምር እውቀት ለማስፋት፤ ልዩ ልዩ አስተሳሰቦችን ለመገንዘብ ቀን ከሌት ትታትራለህ።