Tuesday, December 3, 2013

ሰው ዋጋው ስንት ነው?



አንድ ወዳጅ ነበረኝእግዚአብሄር የሚወድህ ከሆነ ገንዘብ አይሰጥህም !” የሚለኝ። ዝና አይሰጥህም፤ ስልጣን አይሰጥህም፤ ይላል። እነዚህ ሁሉ ሲመነዘሩ ሰውን አይተኩማ፣ ሰውን ከማግኘት ጋር አይተካከሉማ፣ እግዚአብሄር የሚወድህ ከሆነ ሰው ይሰጥሀል። በጎደለ የምትሞላው፣ ክፍተትህን የምትዘጋበት፣ ዕውቀትም ገንዘብም የሆነ . . . ስልጣንም ዝናም የሚሰጥህ ሰው።

ዲዮጋንን በጠራራ ፀሀይ ፋኖስ አስይዞ ያስፈለገው ሰው። ባለቅኔውየሰው ያለህ የሰውብሎ እንዲቀኝ ያስገደደው ሰው። ለዘመናት ድሮ ቀረ . . .ድሮ አልቀረ እያስባለ እልባት አልባ ክርክር ያከራከረው ሰው። ኢየሱስ፣ ቡድሀ፣ መሀመድ ያላቸውን ነገር ሁሉ የከፈሉለት ሰው።

እኔም እናንተ አላችሁኝ እላለሁ። የድክመቴ አበርቺ፣ የጥንካሬዬ ጠቋሚ፣ የሽንፈቴ አፅናኝ፣ የሀሴቴ አድማቂ፣ የጉዳቴ ተሟጋች . . . የሁለ ነገሬ ሁሉም ነገሮች አላችሁኝ እላለሁ። ኑሩልኝ። እደግመዋለሁ ኑሩልኝ።

Thursday, November 7, 2013

በጤነኝነት ስም የሚፈረጁ ጤና ማጣቶች

የአእምሮ በሽታ ነው።ይህንንስ ለኔ ባረገውየሚስብል ዓይነት . . . ምልክቶቹ በዘመነኛ አልባሳት እስካፍንጫ ድምቅ ብሎ መታየት፣ ከፍተኛ ዋጋ በሚያስከፍሉ ልብሶች መዘነጥ፣ በውድ ሽቶዎች መአዛ መታጠን ናቸው። ይህ ብቻ አያደለም ህመሙን ህመም ነው ብለው የነገሩን እንዳሉት ከሆነ ነገርየው ልዩ ችሎታ እና ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች የሚያጠቃ እንደመሆኑ ሰለባዎቹ ህመሙ በተነሳባቸው ጊዜ የፈጠራ ችሎታቸው በዕጅጉ ይጨምራል። ቀን ከሌት በትጋት አዲስ ነገር ሲያስሱ ሲፈጥሩና ሲመራመሩ ውጤታማ ጊዜን ያሳልፋሉ። በጤነኝነት ጊዜያቸው ወራትን ይፈጁባቸው የነበሩ ስራዎች በህመማቸው ወቅት በቀናት ውስጥ ያጠናቅቁታል። ምስጋና ለህመማቸው። በደህንነት ዘመናቸው የሚኖራቸው አለባበስ እንደነገሩ ነው። በህመማቸው ወቅት ግን ከማንም በላይ ቂቅ ያላሉ። ምስጋና ለህመማቸው። ለፈጠራዎቻቸው መጠነኛ ትኩረት የሚሰጡት ካልታመሙ ነው የተነሳባቸው ሰሞን በሙሉ ትኩረት ብቻ ሳይሆን ብቃትም ስራቸውን ያከናውናሉ። እድሜ ለህመማቸው።

Friday, October 11, 2013

ፍተላ

በአንድ ቲያትርን በሚያስተምር መንግስታዊ ተቋም የሚሰለጥን ሰው ነው። ፒሪሪም ፓራራም ለተባለ ፊልም በተዋናይነት ይታጫል። ታጭቶም አልቀረም ስክሪን ቴስት አድርጎ ያልፋል። ይተውናልም . . . 

የተሰጠችው ቦታ አጠር ያለች ብትመስልም ረዘም ላሉ ደቂቃዎች አንድ ለበለጡ ቀናት ይቀረጻል። ፊልሙ የዝግጅት ጣጣውን ጨርሶ ለእይታ ሲበቃ ሰዎችን እንዲጋብዝ የተሰጠው ወረቀት ፊልሙ ላይ ካለው ቦታ የበለጠ ነበር። የቀረው ዘመድ አዝማድ የለም። አብረውት የሚማሩ በሙሉ ታዳሚዎች ናቸው።
 
ለአብዛኞቹ እሱ ለጋበዛቸው እድምተኞች አንድ ቀን ከምናምን ሙሉ ያሳለፈውን አድካሚ የቀረፃ ጊዜ ተርኳል። ስክሪፕቱን ለመያዝ የፈጀበትን ጊዜ አውርቷል። የዳይሬክተሩን ቁጡነት ለፍፏል። ስለተዋንያን፣ ስለካሜራ ደስኩሯል።
አሁን ፊልሙ በመታየት ላይ ነው።  አጋማሹ ላይ የደረሰ ቢሆንም ተዋናዩ እስካሁን አልታየም። ከግማሽ አልፎ ወደመጠናቀቁ ሲቃረብ ተዋናዩ ውልብ ብሎ ጭልም ቢልም፣ ጥቂት ቃላትን ተናግሮ ድምጹን ቢያሰማም ያላስተዋሉት በዙ።   
               
                    ‘’ታይቷል!’’ ‘’አልታየም!’’ እያሉ የሚከራከሩ በረከቱ።

በበነጋው የተቀረጸው ብዙ እንደነበር ነገር ግን ሰዓት ለማሳጠር እና በአናዳንድ የኤዲቲንግ ስህተቶች ምክንያት በዚህ መልኩ እንዳጠረ . . . ይህ በመሆኑም ፕሮሪውሰሩን እና ዳይሬክተሩን ጨምሮ በርካታ የፊልሙ አባላት እንዳዘኑ ለወዳጆቹ ለማስረዳት እያሰበ ወደሚማርበት ቦታ ሲደርስ- ምክንያቱን ከመግለፁ በፊት፣ ችግሩን ከማስረዳቱ በፊት፣ ምንም ከማለቱ ምንም ነገር ከማድረጉ በፊት ጥቁር ሰሌዳው ላይ የተፃፈውን ሲያነብ ቅስሙ የተሰበረው - የተበሳጨውና የተናደደው - ነገርየው የተባለው እሱ ለይ በመሆኑ እንጂ ባይሆን ኖሮ ከተከት ብሎ በሳቀ ነበር። ጥቁሩ ግድግዳ ላይ በነጭ የተነቀሰው ጽሁፍ እንዲህ የሚል ነው።

የአፋልጉኝ ማስታወቂያ

ወዳጃችን እከሌ እከሌ ፒሪሪም ፓራራም የተባለ ፊልም ላይ ገብቶ የገባበት ስለጠፋብን ያለበትን የሚያውቅ ካለ ቢጠቁመን ወሮታውን የምንከፍል መሆኑን እንገልጻለን።